መጪውን በኳለና በሳለ መልኩ ‹የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፋት› በሚል አመርቂ ሃሳብ የአዲስ ዓመት የመጨረሻ እለት የሆነውን ጳጉሜን አምስትን ዋጅተናል፡፡ እንደሚታወቀው ጳጉሜን ወር የአስራ ሶስት ወር ጸጋን የያዘ የዘመን አጭር ግን ደግሞ የታሪክ ሀብታም ወር ነው፡፡ በዚህ የአሮጌው ዓመት ማብቂያ ላይ አዲሱን ዓመት በበጎ ሃሳብና ተስፋ እንድንቀበለው በሚያደርግ የመንፈስ ንቃት ላይ እንገኛለን፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት በሃሳብ የበለጸገ፣ ለሃሳብ ቅድሚያ የሚሰጥ ሃሳባውያን ያስፈልጓታል፡፡ ሃሳብና ሃሳባውያን የሚፈጠሩት ደግሞ ዓላማ ባለው፣ ለአንድ ግብ በቆመ ብሄራዊ ጥቅም በኩል ነው፡፡ አምስቱም የጳጉሜን ቀናት ስያሜዎች ሀገር ከምትፈልገው፣ ሕዝብ ከሚሻው፣ የትውልዱ ጥያቄ ከሆነ እውነታ በኩል የመነጩ ናቸው፡፡
ነገ የተስፋ ቀን ነው፡፡ የነገ ቀን ብዙዎች ህልማችንን ያስቀመጥንበት ካዝና ነው፡፡ እንደሀገር እንደግለሰብ በሆነልን የምንለው ነገ ውስጥ ያለ ነው፡ ፡ ይሄ ቀን ደግሞ በዛሬ ትጋት፣ በዛሬ ምክክር፣ በአሁን እርቅና ሰላም የሚዳብር ነው፡፡ በወንድማማችነት፣ በትብብር፣ በድግግፍ የሚጸና ነው፡፡ የዛሬ ትጋት ለነገ ተስፋ ብለን በመሪ ሃሳብ ስንነሳ ለነገ ህልሞቻችን የዛሬን ሃላፊነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
በርካታ የሳይንስ ጥናቶች፣ እልፍ የሥነ ልቦና ምርምሮች ካለፈው ይልቅ የሚመጣው እንደሚልቅ የሚናገሩ ናቸው፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ ባለፈው ጣጣው ዛሬውን የሚኮንን ለመጪው የሚሆን ትሩፋት እንደሌለም ይናገራሉ፡፡ መጪው ካለፈው የሚልቅ ከሆነ እንደተስፈኛ ሀገር ልናደርግ የሚገባው ሶስት ወሳኝ ነገር አሉ ብዬ አምናለሁ .. ይቅርታ ፍቅርና ተስፋ ናቸው፡፡
ይቅርታ ትናትን፣ ፍቅር ዛሬን፣ ተስፋ ደግሞ ነገን እንድንኖር የሚያደርጉን የሕይወት ዋስትናዎቻችን ናቸው፡፡ ትናንት በብዙ ጣጣው ወደዛሬ መጥቶ ዛሬን አበላሽቶብናል፡፡ ዛሬ በትናንት ጣጣው ወደነገ እንዳይሄድ በቃ ብለን ዛሬ ላይ የምናቆመው ከላይ በገለጽኩት ሶስት መንገድ ነው፡፡ ይቅርታ ፍቅርና ተስፋ ከአሮጌ አስተሳሰብ ወጥተን ወደከፍታ የምንሸጋገርባቸው መንገዶቻችን ናቸው፡፡
አዲስነት ይቅርታ ፍቅርና ተስፋን የቀየጠ ሰውነትን ነው ፡፡ በአዲሱ ዓመት ወደ ከፍታና ወደላቀ ሀገራዊ በረከት ለመሄድ እኚህ ሶስት እውነቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊዎቻችን ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ስናስብና እንደሀገር እቅድ ስናወጣ እነዚህን ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባት ነው፡፡
አዲስ ዓመት ባልነጻ ልብና ባልተቀደሰ አእምሮ ቢመጣ ትርጉም የለውም፡፡ ከምንም በፊት አእምሮና ልባችንን ለሰውነት ማስገዛት ይኖርብናል፡፡ በርካታ አዲስ ዓመታትን እንዲሆንልን በምንመኘው በጎ ምኞት ተቀብለን እናውቃለን አንዳቸውም ግን ትርጉም ያለው ነገር ሳይሰጡን አልፈዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለምኞታችን የሚሆን ፍቅር ወላድ፣ አብሮነት ጸናሽ እውነት ስለሌለን ነው፡፡ ዛሬ ላይ እያደረግናቸው ያሉ ነገሮች ወደነገ ሄደው ሕይወታችን የሚሆኑ ናቸው፡፡ ሰላም ከሆነ የምንፈልገው ስለሰላም ዋጋ እንክፈል፡፡ አንድነት ከሆነ ስለኢትዮጵያዊነት እናውጋ፡፡
አዲሱ ዓመት በበጎ ሃሳብ የፍቅርን ዘር የምንዘራበት፣ የጥላቻና የጦርነትን አሜኬላ የምንነቅልበት ነው፡፡ የፍቅር ዘር አብሮነትን የሚሰ ጠን ወደምንፈልገው ወደየትኛውም አቅጣጫ በድል የምንሄድበት ነው፡፡ ሊነቀሉ የሚገቡ በጥላቻ የዘራናቸው ብዙ የጉስቁልና ዘሮች አሉ፡፡ ፍሬ መስጠት ሲገባቸው እንክርዳድ እያሳጨዱን ከክብር ሥፍራ አጉለውናል፡፡ እነዚህ አራሙቻዎች በአዲሱ ዓመት ተወግደው በሁሉን አቃፊ የጋራ ወግ መተካት አለባቸው፡፡
የዛሬ ትጋቶቻችን የነገ ትሩፋቶቻችን ናቸው። ትሩፋት በረከት፣ ጸጋ ማለት ነው፡፡ መትረፍረፍ የሚለው የጸጋ ስምም በዚህ ስያሜ የሚጠራ ነው። የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፋት የሚለው መነሻ ሃሳብ እድልና ድልን በአንድ ያስተሳሰረ፣ ከድህነት ወደ እድገት፣ ከጦርነት ወደ ሰላም የሚወስድ የጸጋ መነሻ ነው፡፡ ትሩፋት በትጋት የሚመጣ የላብ ውጤት ነው፡፡ ነገን የትሩፋት ጊዜ ለማድረግ ዛሬን መትጋትና መበርታት ያስፈልጋል፡፡
ነገን ዛሬ መሥራት የሚል የቆየና በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የተሳለ ሀገረኛ አባባል አለው፡፡ የጳጉሜን 5 መሪ ቃል አንድምታም እንዲሁ ነው። ልብ ብለን ከሆነ ዛሬ ላይ ዋጋ እየከፈልንባቸው ያሉ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሰላም፣ የደህንነት መሰል ጥያቄዎች ትናንት ላይ ያልተሰራባቸው በእንዲሁ የታለፉ ናቸው፡፡ የዛሬ ትጋት የነገ ትሩፋት ግን ከስህተቶቻችን ተምረን ያለፈውን በይቅርታ ያለውን በእርቅ መጪውን ደግሞ በፍቅርና በአብሮነት እንድንቀበለው የሚያደርግ የተሀድሶ ሃሳብ ነው፡፡
ያለመጠራጠር ተሀድሶ ያስፈልገናል፡፡ ፖለቲ ካው፣ ፖለቲከኛው፣ አክቲቪስቱ ሁላችንም የለውጥና የስክነት ተሀድሶ ያስፈልገናል፡፡ ተሀድሶ ብዙ ትርጉም ቢኖረው አሁን ባለው የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ግን አክሳሪ እና አዋራጅ ከሆነ የክሽፈት ልምምድ ወጥተን አዋጪና አትራፊ ወደሆነ አዲስ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልምምድ መሻገር የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ሰላሟን በምክክር፣ ልማቷን በትብብር፣ አንድነቷን በኢትዮጵያዊነት ለመጽናት እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ይሄ ተስፋዋ በአዲሱ ዓመት እንዲጎመራ የጋራ ምኞት አለን፡፡
ትርፍ ያለው ለሀገር እሴት የሚጨምር አስተሳሰብ ከፖለቲካው ወደፖለቲከኞቻችን ከዛም ወደማህበረሰቡና ትውልዱ እንዲሰርጽ ያረጁና ያፈጁ ጦርነት ወላድ አስተሳሰቦች መሻር አለባቸው፡ ፡ ለዚህ ደግሞ የጋራ ትርክት፣ የአብሮነት ወግ አጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህ መሸጋገሪያ የሚሆነን ደግሞ ከአሮጌው ዓመት ጋር አሮጌ አስተሳሰባችንን ጥለን ከአዲሱ ዓመት ጋር በአዲስ አእምሮና ልብ ነገን የምንሠራበትን የሀሳብ መዋጮ ማዋጣት ነው፡፡
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም