ዜና ትንታኔ
ምድረ ቀደምት፣ የወርቃማ ድሎች ባለቤት፣ የጥቁር አርበኞች መኖሪያና በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችን የታደለችው ኢትዮጵያ በታሪኳ የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ ወጥታለች፣ በቁልቁለት ጉዞም ወርዳ የድህነትን ወለል ረግጣለች፡፡ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተጫናት ድህነት ለመላቀቅ፣ ወደኋላ ከሚጎትቷት አለመግባባቶችና ግጭቶች ጥሳ ለመውጣት በትጋት ላይ ናት፡፡
በክብርም በቁጥርም ትልቅ የሆነው፤ ሰፊና ሰጪ ምድርን የታደለው ሕዝቧ፣ ሀገሩ ከእጦትና ከችግር የተላቀቀች፣ በኢኮኖሚ አቅሟም የበለጸገች ውብና ለኑሮ ምቹ ሀገር ሆና ማየትን ይሻል፡፡ መሻት በጥረት እንጂ በተስፋ ብቻ እውን አይሆንምና፣ ነገ ላይ የበለጸገችውን ኢትዮጵያ ማየት ይቻለን ዘንድ መንግሥትና ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ ዛሬ ላይ ያሉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች፣ የፖለቲካ መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ነገ ልናያት የምንሻትን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ያደርጉልን ይሆን? የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ ማየት ይቻለን ዘንድ ከእያንዳንዱ ዜጋስ ምን ይጠበቃል?
የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ የአንድ ሀገር ነገ የሚመሠረተው በትናንት ታሪኩና ዛሬ ላይ በሚሠራ ሥራ ነው ይላሉ፡፡ በሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን ለማምጣት በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም ያወሳሉ፡፡ በለውጡ መንግሥት ደግሞ እንደ ሀገር ግባችንን “ብልጽግና” አድርገን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ያሉት ምሁሩ፣ የጀመርነው ጉዞ ወደ በለጸገች ኢትዮጵያ የምንሸጋገርበት ጊዜ ላይ ለመሆናችን ማሳያ ነው በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
የፖሊሲና የሕዝብ አስተዳደር ምሁሩ ዶ/ር ገመቹ አራርሳ በበኩላቸው፣ በሀገራችን ካለፉት 5 እና 6 ዓመታት ወዲህ “ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማምጣት” የሚል ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ተቀምጦ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ በቀደሙት ሥርዓተ መንግሥታት የተከናወኑ መልካም ተግባራትን እንደ ሀብት በመውሰድ፣ ቀድሞ በነበረን ጉዞ የሀገራችን እድገት ብዙ ርቀት መጓዝ የተሳነው ለምንድነው የሚለው ጥያቄ በጥናት የተደገፈ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ግኝቶችን መነሻ ያደረጉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተሠራባቸው እንደሚገኙም ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶ/ር ገመቹ ማብራሪያ፣ ተጨባጭ ኢኮኖሚዊ ለውጥን ለማምጣት ከዚህ ቀደም ሲሠራበት የነበረውን የኢኮኖሚ አቅጣጫ መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ባገናዘበ መልኩ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ”ን በመንደፍ ወደ ሥራ መግባት ተችሏል፡፡ በዚህም በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ግብርና መር ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ግብርናው ላይ ብቻ የተመረኮዘ መሆኑ የታሰበውን ያህል ለውጥ ማስመዝገብ፣ የኢኮኖሚ ሽግግርንም ማምጣት አልተቻለውም ነበር፡፡ ስለሆነም ይህን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ወደ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መቀየሩ አስፈላጊነቱ ታምኖበት በተወሰደው ርምጃ ግብርናውን በተሻለ ትኩረትና ጥንካሬ በመያዝ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጣቸው እንደ ማዕድንና ቱሪዝም ያሉ በርካታ ዘርፎች ትኩረት ማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህም በርካታ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት፣ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችንም በማበረታታትና በብዛትና በጥራት በማሳደግ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል፡፡
እየተተገበረ ያለው የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አንስቶ የውጪ ኢንቨስተሮችን አሳታፊ በሆነ መልኩ መመራቱ ከዚህ ቀደም ሀብት በጥቂቶች እጅ ብቻ እንዲሆን ሲያደርግ የነበረውን የኢኮኖሚ አካሄድ መቀየር የቻለ ነው ያሉት ዶክተር ገመቹ፤ እየተከተልን ያለነው አካታችና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በጣም ትልቅ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑ በየዘርፉ እየመጡ ያሉ ለውጦች ጉልህ ማሳያ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ በተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጪ ምንዛሪ ምጣኔው በገበያ ዋጋ መወሰኑ አሁን ላይ ይህን ለውጥ አምጥቷል ለማለት ባይቻልም፣ በሂደት ግን በተለይ በውጪ ምንዛሪ እጦትና እጥረት ሳቢያ የተሳሰሩ ዘርፎች የሚፈልጉትን ውጪ ምንዛሪ እንዲያገኙ እድል የሚሰጥ በመሆኑ በሂደት ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ እሙን ነው ብለዋል፡፡
በሀገራችን ለሁሉም ዘርፍ የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማምጣት ብሩህ ተስፋን እንድንሰንቅ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ዶክተር ገመቹ ብልጽግናችን እውን የሚሆነው በሕዝብ ጥረት ነው ይላሉ፡፡ ሀገር ብትለወጥና ብታድግ ተጠቃሚው ሕዝብ፣ ፍሬውን የሚበላው የነገው ትውልድ ነው ያሉት ምሁሩ ይህን እውን ለማድረግ እንደ ሕዝብ የሥራና የጊዜ አጠቃቀም ባህላችንን መቀየር፣ ትኩረታችንን ልማት ላይ ማድረግ፣ እውቀትን ለበጎ ተግባር ማዋል ይጠበቃል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ አልመን የተነሳንበትን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሀገር ሰላም ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ላይ ያሰምራሉ፡፡
የተበላሹ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኑነትን ለማስተካከል በተለያየ መልኩ የሚደረጉ ጥረቶችና የሀገር አንድነትን ለማጽናት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ነባር ጣጣዎቻችንን ቋጭተን ወደ አዲስ ምዕራፍ ልንሻገር ጉዞ መጀመራችንን አመላካች ናቸው ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፣ በልማትም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ እየተደረጉ የብልጽግና ጎዳናን የማቅናት ጥረቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥረቶቹ እንዲሳኩ ሁሉም የበኩሉን ከተወጣ፣ መወያየትን መርጠን በጠረጴዛ ዙሪያ ከተቀመጥን የልማት ሥራዎቻችን የበለጠ ፍሬያማ፣ የበለጸገችዋን ኢትዮጵያ እውን ማድረግም ሩቅ አይሆንም በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም