አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ መልካም ፍሬ የሚሰጥ ምርጥ ዘር ነው

አዲስ አበባ፡– አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ መልካም ፍሬ የሚሰጥ ምርጥ ዘር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለሁለት ወራት ሲያሰለጥናቸው የቆያቸውን 200 የኤ አይ ሰመር ካምፕ ሠልጣኞች በትናንትናው እለት አስመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ መልካም ፍሬ የሚሰጥ ምርጥ ዘር ነው፡፡

የሰው ጉልበት በመቀነስ በማሽን በስፋት ማምረት እንዲቻል ቴክኖሎጂ ካልደገፈው በቀር የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ውስን ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ከግብርናው እስከ ኢንዱስትሪው ያለው ዘርፍ በቴክኖሎጂ ታግዞ ምርታማ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እቅዱም ቴክኖሎጂን የእድገት መሠረት አድርጎ መቅረጽ ቀዳሚው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሁሉም ዘርፍ ላይ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ኤ አይ የተፈጠረለትን ዓላማ እያሳካ ነው፡፡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራቂዎች ያገኙትን ሥልጠና በትጋት ሥራ ላይ በማዋል የኢትዮጵያን ገፅታ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከተመራቂዎች የሚጠበቀውም ዘላቂ ችግር የሚፈታ ፈጠራ እንድታመነጩ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዲጂታል ኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ተማሪዎቹ በሰመር ካምፕ መርሐ ግብር ከሚሰጣቸው ሥልጠና ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ” ሥልጠና ቁልፍ መሠረት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሠልጣኞች ዓላማቸው በፈጠራ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳጊዎቹ ህልማቸውን ለመኖር መድከም እንዳለባቸውም ምክራቸውን ለግሰዋል።

አምና 30 ተማሪዎች መመረቃቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ 200 ሠልጣኞች ማስመረቅ ተችሏል፤ በቀጣይም አቅምን በማሳደግ በክረምት የሚሰጡ ሥልጠናዎች የሚቀጥሉ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

በርካታ ወላጆች የተሻለ ትምህርት ለልጆቻቸው ለማግኘት ወደ ሌላ ሀገራት ልከው በጠበቁት ልክ ልጆቻቸውን አያገኙም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ሰመር ካምፕ ልጆቻችው ተምረው ለዚህ በመብቃታቸው ወላጆች ደስ ሊላችሁ ይገባልም ብለዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ለሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞችና ጽህፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ህጻናት ማዕድ አጋርተዋል፡፡

ማዕድ ማጋራት የሀገር ወዳድነት ምልክት፤ የወዳጅነት ውብ ማስታወሻ ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

ማዕድ ማጋራት አንጡራ ባህላችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለን ላይ እናጋራ፤ ደስታን እንጋራ፣ እርስ በርሳችን እንደጋገፍ፤ በዓሉን ካለችን ለሌለው እያካፈልን ልባችንን እና ነፍሳችንን የሚመግቡ ትውስታዎችን በመፍጠር እናሳልፍ ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You