መማር አልቻልንም እንጂ የምንማርባቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ:: በአሁኑ ጊዜ በዓለም አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ነገር የበረሃማነት መስፋፋት ነው። በቅርቡም በአውሮፓ አገራት ውስጥ በሙቀት መስፋፋት ምክንያት የተፈጠረውን አይተናል። በአገራችን ኢትዮጵያም አብዛኞቹ አካባቢዎች ሞቃት ናቸው።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን እናምናለን! ዳሩ ግን ዕድሉን አልተጠቀምነውም። በገዛ እጃችን አገሪቱን ወደበረሃማነት እየቀየርናት ነው።
ለዚህ ሃሳብ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት ወደ አንድ አካባቢ ባደረኩት ጉዞ ያስተዋልኩት ነገር ነው። ጉዞው ከአዲስ አበባ ወደ ታሪካዊቷ ጅማ ከተማ ነበር። ጅማ ለመድረስ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎችን በፈረቃ ያስጎበኛል። ከጥቂት ጉዞ በኋላ ኦሮሚያን፣ ከዚያም ደቡብን፣ ከዚያም ኦሮሚያን… እያለ ነው የሚወስደን።
ወቅቱ የክረምት መግቢያ እንደመሆኑ ዝናብ ይደጋገማል። ከረጅም ጉዞ በኋላ የጊቤ በረሃ ገባን:: አሁን እስከዛሬ ከማደርጋቸው ጉዞዎች ለየት ያለ ሆነብኝ:: እንኳን በበረሃማ ውስጥ በየትኛውም አካባቢ ቢሆን በጉዞ ላይ ጃኬት ማውለቅ የግድ ነው። በዚያን ቀን ግን እንኳንስ ጃኬት ማውለቅ ሌላም ለመደረብ ያስገድዳል::
ብርድና ዝናብ ነው። አካባቢው በረሃ ነው። የሚጠራውም ጊቤ በረሃ እየተባለ ነው። አካባቢው ከዚህ በፊትም እንደዚሁ ቀዝቃዛ ሆኖ ይሆን? ብየ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሚያውቀው አብሮኝ ያለውን ባልደረባ ጠየቅኩት። በበጋ ወቅት እንኳን ጃኬት ቲሸርትም የሚያስወልቅ ሙቀት ነው።
ይሄ በረሃ አሁን የቀዘቀዘበት ምክንያት ግልጽ ነው:: አካባቢው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው። ከርቀት ሆነው ሲያዩት ጠጠር ቢጣልበት መሬት የሚያሳርፍ አይመስልም:: አጠገቡ ሲደርሱ በዛፎች መካከል ክፍተት ቢታይም መሬቱ ደግሞ ክረምቱን ተከትለው በበቀሉ የተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎችና የሳር አይነቶች የተሸፈነ ነው።
አካባቢው እንኳን አሁን የክረምት መግቢያ ሆኖ በበጋ ወቅትም ዝናብ እንደማይለየው በተደጋጋሚ ያዩትና የሚያውቁት ሰዎች ነግረውኛል። ነገሩ እውነት መሆኑን ደግሞ ሳይንስም ያግዘናል። ደን ባለበት አካባቢ ዝናብ አለ::
ይሄ የተፈጥሮ ዑደት ነው። የደን መመናመን ድርቅ እንደሚያስከትልም ከተማሪ እስከ ተመራማሪ ይታወቃል:: ብዙ ጊዜ ‹‹እብድ እና ዝናብ ከከተማ አይጠፋም›› ሲባል እንሰማለን። ምክንያቱ ግን መለኮታዊ ሳይሆን ሳይንሳዊ ነው። በተለይም ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ገጠር አካባቢ ደን እየተመናመነ ከተማ አካባቢ ነው የሚገኘው። ከገጠር ይልቅ አዲስ አበባ ውስጥ ሆኗል የዛፍ አይነት የሚታየው::
ወደ ጊቤ በረሃ ስንመለስ አካባቢው ገና በሰኔ ወር መቀዝቀዝ ጀምሯል። ክረምት መግቢያ ላይ እኮ የትኛውም በረሃማ አካባቢ ይቀዘቅዛል! ትሉኝ ይሆናል፤ ግን አይደለም:: በክረምት ወራት ጃኬት አውልቀን የምንሄድባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው። እንግዲህ ሙቀት እንደየሁኔታው ስለሚለያይ አጋጣሚ ነው እንበል፤ ያ ጥቅጥቅ ያለ ደን እና ዶፍ ዝናብ ግን በአጋጣሚ የሆነ አይደለም፤ ሁሌም የሚከሰት ተፈጥሯዊ ክስተት ነው።
ዋናው ነገር ‹‹አሁን ከዚህ ምን እንማር?›› የሚለው ነው።
ዓይናችን እያየ አገራችንን እያበለሻሸናት ነው። ከዚህ በላይ ምን ማሳያ አለ? ደን ባለበት አካባቢ እንዲህ ዝናብ እየጣለ፤ ደን በተራቆተበት አካባቢ በሰኔ አቧራ እየጨሰ እንዴት ከዚህ አንማርም? ደን ባለበት አካባቢ የሳር አይነት፣ የዱር እንስሳት አይነት እታየ፤ ደን በሌለበት አካባቢ እንሽላሊት እንኳን ሲጠፋ እንዴት ከዚህ አንማርም? ኧረ ምን ስንሆን ነው የምንማር?
ህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ቀጥተኛ ተወቃሽ ነው:: አስታውሳለሁ፤ በ1990ዎቹ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ‹‹ማንኛውም ሰው ለሕይወቱ እንደሚያስብ ሁሉ ለደን ያስብ!›› የሚል መሪ ቃል በፓርከር ተጽፎ በአካባቢያችን የገበያ መግቢያ ላይ ተለጥፎ ነበር። መሪ ቃሉን በወቅቱ እንኳን (ልጅ ሆኜ ማለቴ ነው እንግዲህ) ትልቅ ትርጉም ሰጥቸው ነበር።
አሳዛኙ ነገር አሁን በዚያ አካባቢ የጥርስ መፋቂያ እንኳን የሚሆን ደን የለም! ለምን ቢባል ይህን ማስታወቂያ የለጠፈው የመንግስት አካል ኃላፊነቱን አልተወጣም። ደን ከሕይወት ጋር ከተነጻጸረ ጥበቃውም የሕይወት ያህል መሆን ነበረበት። ለምሳሌ በአካባቢው ሰው ገድሎ የሚቀመጥ የለም፤ ወይ ይታሰራል ወይም የሟች ቤተሰብን ስለሚፈራ ይጠፋል። አንድ ሄክታር ደን የጨፈጨፈ ግን ምንም አይሆንም! ግፋ ቢል በአካባቢ ሽማግሎች እርግማን ቢደርስበት ነው።
ለሰው ሕይወት ሲባል በየአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ተቋቁሞ ፖሊስ ይመደባል፤ በከፍተኛ ወጪ የጸጥታ አካላት በየአካባቢው እንዲመደቡ ይደረጋል። ግርግርና ግጭት ሲነሳ ቶሎ የጸጥታ አካላት ይመደባሉ። የቱንም ያህል ደን ቢጨፈጨፍ ግን እንኳን የጦር መሳሪያ ዱላ እንኳን የያዘ ሰው አይመደብም።
በመሰረቱ ደን ሕይወት ቢሆንም በታጠቁ ሃይሎች ይጠበቅ አይባልም፤ ምክንያቱም ማንም ሰው ለዚህ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባ ነበር፤ ግን ይህ ካልሆነስ? እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ ለሰው ልጅም ጦር መሳሪያ የታጠቀ ጥበቃ አያስፈልግም ነበር። ሰው ሰውን ለምን ይገላል? ለምን ይሰርቃል? ለምን ወንጀል ይሰራል? ስለዚህ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው ጥበቃም ለደን ያስፈልገዋል ማለት ነው። አልፎ አልፎ ጥበቃ የሚደርባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ዳሩ ግን በፓርክ ስም ለተመዘገቡትና እጅግ በጥቂት ቦታዎች ብቻ ነው!
ደን ሕይወት መሆኑ ምንም ማብራሪያ አያስፈልገውም፤ ደን ሕይወት ከሆነ ታዲያ መቼ ይሆን የምንማር?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ዋለልኝ አየለ