ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የምግብና የሥነ-ምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የሚያስችሏትን ሰፋፊ የግብርና ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በመንግሥት በኩል በከፍተኛ ደረጃ ቁርጠኝነት በታየበት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባመጣችው የላቀ እምርታ ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ እያደረጋት ይገኛል፡፡ በሀገሪቱ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ በግብርና ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራባቸው ሰብሎች መካከል ሩዝ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዋናነትም ካለፈው ዓመት ወዲህ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት እየተመረተ ሲሆን ፤ ይህም ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ሰብል በሀገር ውስጥ ምርት የመተካቱን እቅድ ለማሳካት እንደ ትልቅ ማሳያ እየሆነ ይገኛል፡፡
እንደ ሀገር ለሩዝ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከመታደግ ባሻገር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንደ አንድ አማራጭ ሆኖ በማገልገል ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደሚሉትም፤ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱን የሩዝ ፍጆታ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለመሸፈን ተችሏል። ኢትዮጵያ ከስንዴና ከቢራ ገብስ ቀጥሎ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሩዝ ፍጆታዋን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈንና የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ሀገራዊ ጥረት ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ሩዝ በዓለም ላይ በብዛት ከሚመረቱ ስትራቴጂካዊ ሰብሎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሩዝን እንደ ዋና ምግብ እንደሚጠቀም ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በሩዝ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት እንዳላት አንስተው፣ ሆኖም አብዛኛውን የሩዝ ፍጆታ ከውጭ እንደምታስገባ ይጠቁማሉ፡፡ አብነት አድርገውም እ.ኤ.አ እስከ 2022 ኢትዮጵያ ከሩዝ ፍጆታዋ መካከል 20 በመቶውን ብቻ በመሸፈን ቀሪውን ከውጭ ታስገባ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
ቀደም ሲል በአማራ ክልል ፎገራ ብቻ በ300 ሺ ሄክታር ከነበረው ልማት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል እስከ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ እየለማ ይገኛል፡፡ በብሔራዊ የሩዝ ፕሮግራም አማካኝነት ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የሩዝ ምርት ሙሉ ለሙሉ እንደምታስቀርም ታምኖበታል፡፡ ‹‹በስንዴ ልማት የተከናወነውን ስትራቴጂ በሩዝ ልማት እየደገምን ነው›› የሚሉት ሚኒስትሩ በዝናብ ብቻ ሳይሆን በመስኖ የማልማት ሂደት በሶማሌ ክልል የተገኘውን ተሞክሮ በቀጣይ በሌሎች ክልሎችም የማስፋፋት ሥራ እንደሚከናወን ነው የጠቆሙት፡፡
ዘንድሮ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተመረተ ባለው የሩዝ ምርትን አስመልክቶ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደተናገሩት፤ በክልሉ 149 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ እየለማ ሲሆን በዘንድሮ የመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሚሊዮን መሬት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖች የተሻለ የሩዝ ምርት ለማምረት መታቀዱን አቶ ቃልኪዳን አመልክተው፤ ከመደበኛ ሰብሎች በተጨማሪ በሩዝ ምርት ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩንም ይጠቁማሉ፡፡ በዘንድሮ የምርት ዘመን ክልሉ ልዩ እቅድ ይዞ ሩዝ ማምረት አቅም እያላቸው እስካሁን ግን የማምረት ልምምድ ያላደረጉ አካባቢዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም ሩዝ በስፋት ይመረትባቸው ከነበሩ የደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች ባለፈ በማዕከላዊ ጎንደር እና በአዊ ብሔረሰብ ዞኖች ምርቱን የማለማመድ ሥራ መሰራቱንም ያነሳሉ፡፡ ‹‹የሩዝ ምርት የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል›› ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ክልሉ ሩዝን በክላስተር ለማምረት የሚያስችል ሥራ ማከናወኑንም ያብራራሉ፡፡ በክልሉ ውሃ በብዛት በሚተኛበት ቦታ የሚመረት ሩዝ መኖሩንም ነው የጠቆሙት፡፡
እንደሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ የማልማት ሥራ በመጋቢት 2016 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ቤርአኖ ወረዳ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በክልሉ በዚህ ዓመት ሶስት ሺ ሄክታር መሬት በሩዝ የማልማት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በ2016/17 የምርት ዘመን በሶማሌ ክልል የሩዝ ምርት የማምረት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አህመድ ኑር አብዲ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከመኸር እርሻ 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በምርት ዘመኑ በክልሉ ሶስት ሺህ ሄክታር መሬትን በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ ‹‹እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ድረስ 530 ሄክታር መሬት የመሸፈን ሥራ ተከናውኗል፤ የዝናቡ ሥርጭት እስከ ጥቅምት ወር ስለሚቆይ ቀሪውን መሬት በሩዝ የመሸፈን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ የሩዝ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርምርና ዘሩን የማባዛት እንቅስቃሴ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹በክልሉ በርካታ የሰብል ዓይነቶችን ማለትም በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስና በተወሰነ ደረጃ ጤፍ እንዲሁም ሩዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የማምርት ሥራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው›› በማለትም ይጠቁማሉ፡፡ በክልሉ የታቀደውን 31 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በማግኘት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰብሎችን በሰው ኃይል የማረም፣ ኬሚካል የመርጨት፣ ተባዮችን የመከላከል፤ በሽታ እንዳያጠቃ የመከታተል ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ከፍተኛ አመራሮች በሶማሌ ክልል ሸበሌ ወንዝ ቤርአኖ ወረዳ በመስኖ የለማ የሩዝ ምርትን የመሰብሰብ ሂደትን ከሰሞኑ አስጀምረዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በሱማሌ ክልል የተጀመረው የሩዝ ልማት ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም ትሩፋት ነው፡፡ በክልሉ አሁን ላይ በመስኖ እየተመረተ ያለው የሩዝ ምርት በስፋት ማስቀጠል ከተቻለ ከአካባቢው ፍጆታ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራትም የሚተርፍ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሀገር የተጀመረውን የሩዝ ኢኒሼቲቭ ለማሳካት የሱማሌ ክልል አበረታች ሂደት ላይ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ‹‹እንደ በጋ መስኖ ስንዴ፣ አረንጓዴ ዐሻራና የኮሪደር ልማት ያሉ በርካታ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን ከትንሽ በመጀመር በግዙፍ አሳክተናል›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ፤ ለአብነትም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከውጭ የሚገባ ምርትን ሙሉ ለሙሉ በማስቀረት አመርቂ ውጤት መገኙትን ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የሱማሌ ክልል በመስኖ ሩዝ ልማት በትንሹ የተጀመረው ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹በስንዴ ያሳካነው ውጤት በሩዝ ልማትም እንደግመዋለን›› በማለትም ይናገራሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹በሶማሌ ክልል ይህ በሸበሌ ወንዝ አካባቢ የተጀመረው የሩዝ ልማት ለአካባቢው ማህረሰብ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ቆላማ ለሆኑ እና ሩዝ ተመጋቢ ሕዝብ ለሚኖርባቸው ሀገራት ትልቅ ቱሩፋት ነው›› ይላሉ፡፡ በሶማሌ ክልል አብዛኛው ማህበረሰብ አርብቶ አደር ቢሆንም በመስኖ ሩዝ ልማት የተጀመረው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም ዓመቱም ሙሉ የሚፈሰውን ሸበሌ ወንዝና በአካባቢው ያለውን አፈር ለመጠቀም የተወሰደው ቅርጠኝነት ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
አቶ ተመስገን አሁን በሩዝ ልማት የተጀመረው ሥራ ዓይን ገላጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በምግብ ራስን የመቻል ሀገራዊ ግብን ለማሳካት አርብቶ አደሩ ወደ እርሻ ሥራ እንዲሰማራ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ አርብቶ አደሩን በታታሪነት ወደ እርሻ በማሳተፍ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ሂደት ማፋጠን የሁሉም ጥረት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአን ጠቅሶ ግብርና ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አዳም ፋራህ የሶማሌ ክልልን የሩዝ ምርትን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ‹‹የሩዝ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት የጀመርናቸው ርምጃዎች ፍሬ እያፈሩ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ‹‹በፓርቲያችን የመጀመሪያው ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሠረት ስንዴን የሀገር ውስጥ ፍጆታችንን በራሳችን ከማምረት አልፈን ኤክስፖርት የማድረግ ትልማችን በተሳካ ማግስት፣ የሩዝ ምርት ፍላጎታችንን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት የጀመርናቸው ርምጃዎች ፍሬ እያፈሩ ነው›› ብለዋል።
አቶ አደም እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምትከተለው የብዝሀ- ዘርፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለሀገራዊው የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ አዳዲስ ገፅታዎችን እያሳየ በአርብቶ አደርነት የሚታወቁት አካባቢዎች በግብርና ሥራ እምርታን ይዘው ብቅ ማለት ጀምረዋል። በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የታየው በመስኖ ሩዝ የማምረት ሀገራዊ የሙከራ ፕሮግራም ሰፊ ትምህርት የተገኘበት ነው። በተጨማሪም እስከ 30 ሚሊዮን ሄክታር መልማት የሚችል ለሩዝ ተስማሚ የሆነ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳር ላላት ለሀገር አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ ጅማሮ ነው።
የሶማሌ ክልል መንግሥት ከግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር ለሩዝ ምርት ያለውን ተስማሚ ሁኔታ በማጥናት አፋጣኝ ርምጃ ወስዶ ወደ ሥራ በመግባት በአራት ዞኖች እና በሰባት ወረዳዎች ሩዝን በመስኖ ለማልማት የተደረገው ሙከራ ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል። ‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከስንዴ እና ከቢራ ገብስ ቀጥሎ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማርካት ሩዝን ኤክስፖርት ለማድረግ የያዘችው ትልም ሙሉ በሙሉ እንደምታሳካው በሸበሌ ወንዝ ላይ ተንጣሎ የተዘረጋው የሩዝ ማሳ ቅድመ ምስክር ሆኗል›› ሲሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ስንዴንም ሆነ ሩዝን በስፋት ማምረት የሚያስችላት ምቹ የአየር ፀባይና ሥነ-ምህዳር ቢኖራትም ምርታማነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሳይሰራ በመቆየቱ በመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ በየዓመቱ ከውጭ ታመጣ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይህንን የስንፍና ታሪክ ሙሉ ለሙሉ መቀየር በሚያስችል መልኩ መንግሥት ቁርጠኝነቱን አሳይቶ በልዩ ትኩረት በመሥራቱ ከፍተኛ የሚባል ስኬት በበጋ መስኖ ስንዴ ማሳየት ተችሏል፡፡
ይህንኑ የስንዴ ልማት ሥራ አብነት በማድረግና ተሞክሮውን በመቀመር እንደ ሀገር የተጀመረው ሁሉንም አቀፍ የሚበረታታ ነው፡፡ እንደ ሀገር የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ትልም ማሳካት ያስችል ዘንድ በጥቂት ክልሎች የስንዴን እግር ተከትሎ የተጀመረውን ይህ የሩዝ ልማት በሌሎችም ክልሎች በማስፋት ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም