አንድ ዓመት ወደ ኋላ – የቱሪዝም ዘርፍ ስኬቶች

ጳጉሜን ሶስት ላይ እንገኛለን። የ2016 ዓ.ም መገባደጃ የአዲስ ዓመት መግቢያ ደጃፍ ላይ ነን። እንደሚታወቀው የ2016 ዓ.ም የመጨረሻው እሁድ ነው። በመሆኑም የዝግጅት ከፍላችን በተጠናቀቀው ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተመዘገቡ ውጤታማ ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ዓመታዊ ዳሰሳ ለማድረግ ወዷል። መረጃውንም የቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ክፍል ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው አድርሰውናል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው›› በማለት ከለያቸው አምስት ዘርፎች መካከል ቱሪዝምን አንዱ አድርጎታል። በዘርፉም መዋቅራዊ ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ይህ ውሳኔ የቱሪዝም ዘርፍን ነፃነት ያወጀና በቀጣይ ለሚካሄዱ የልማት፣ ማስተዋወቅና አንዲሁም የጎብኚዎችን ቁጥር የማሳደግ አቅምን እንደሚጨምር ይጠበቃል።

በአዲስ መልክ ከባህል ዘርፍ ተነጥሎ ለብቻው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ የተዋቀረው ቱሪዝም ሚኒስቴርም ይህንን ሃላፊነት በበላይነት እንዲመራ ይጠበቃል። ተቋሙ እራሱን ከማደራጀት አንስቶ በመዳረሻ ልማት፣ በገበያና ማስታወቂያ፣ በቱሪዝም ዲፕሎማሲ፣ በመረጃ ጥራት አንዲሁም በመሰል የዘርፉ ተግባርና ሃላፊነቶች ላይ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበር የስትራቴጂክ ክፍሉ የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ይናገራሉ። በ2016 ዓ.ም እነዚህን ተግባራት የሚያጎሉ ውጤታማ አፈፃፀሞች መመዝገባቸውን ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ነች። በውስጧ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፋ የያዘች የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የታሪክና የሰው ልጅ መነሻ የሆኑ የመስህብ ሀብቶች ያላት ሀገር ነች። ይህንን እሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ጎብኚዎችን የመሳብ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። በተለይ የቱሪዝም ዲፕሎማሲን ተግባራዊ በማድረግ ከሀገራትና ከሕዝብ ለሕዝብ ጋር ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል። ከዚህ አንፃር ውጤት መመዝገቡን የስትራቴጂክ ቡድን መሪው ይገልፃሉ።

ቱሪዝም ዲፕሎማሲ

በዋናነትም የቱሪዝም ሚኒስቴር በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም በቱሪዝም ዲፕሎማሲው በርካታ ተግባራት መፈፀሙን ይናገራሉ። የቱሪዝም ትስስሮችን ከሀገራት፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ጋር እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር የቱሪስት ፍሰትን ከማሳደግ እና ገፅታን ከመገንባት አኳያ መልካም ውጤቶች መመዝገባቸውን ያስረዳሉ።

እንደ ስትራቴጂክ ቡድን መሪው ገለፃ በ2016 ዓ.ም ከኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቻይና፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ጆርዳንና ሌሎች ሀገራት ጋር የቱሪዝም ትብብሮችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከእነዚህ ሀገራት ጋር በቱሪዝም ማስተዋወቅና ግብይት፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ ልውውጥ እና በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ፍሰት ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተደርገዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ሀገራት ስብስብ አዲስ አባል መሆኗን ተከትሎ በሰኔ ወር በሩሲያ ሞስኮው በተካሄደው ዓመታዊ የቱሪዝም ፎረም መርሃ ግብር ተሳትፎ ተደርጓል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ በሚኒስትሮች ስብሰባ እና በቱሪዝም የከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን (Tourism Working Group) ስብሰባ እንዲሁም በንግድ ለንግድ ትስስር መድረኮች አመርቂ ተሳትፎ መከናወኑን ይገልፃሉ። በነባር የቱሪስት አመንጭ ሀገራት የገበያ ድርሻን ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የቱሪዝም ገበያዎችን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ውጤታማ የግብይትና የማስተዋወቅ ስልት በቱሪዝም አውደ ርዕይ ላይ በመገኘት ተግባራዊ መደረጉን ይገልፃሉ። በዚህም ጠንካራና የተቀናጀ የገፅታ ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ገለፃ፤ ከቱሪዝም ዲፕሎማሲው ባሻገር በ2016 ዓ.ም ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የቱሪዝም መረጃ አስተዳደርን ማሻሻልን የሚመለከተው በቀዳሚነት ይገኝበታል። በዚህም የቱሪዝም ስታቲስቲክስ ሥርዓትን እና መረጃ አስተዳደርና አሠራርን ለማሻሻል በማሰብ ሁለት ጊዜ የቱሪዝም የዳሰሳ ጥናት (Survey) መከናወኑን ያስረዳሉ። ይህ ተግባር ዘርፉ በመረጃ እንዲደገፍ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲያድግ ያደርጋል ይላሉ።

የዘርፉ ምሁራን እና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት በልዩ ልዩ የዘርፉ ተቋማት የሚወጡት መረጃዎች ተዓማኒነትና ተመሳስሎ የሚጎድለው ነው። ይህንን ተከትሎም ተደጋጋሚ ትችቶች በእነዚሁ አካላት ሲሰነዘር ይሰማል። የቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ቡድን መሪው አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ጉዳዩን አስመልክቶ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የቱሪዝም መረጃ ጥራትን ከማሻሻል አኳያ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሰርቬይ (International Visitors’ Exit Survey) ከጃይካ (JICA) ጋር በተደረገ የሥራ ግንኙነት ተከናውኗል። በዋናነትም በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት መረጃዎችን ከውጭ ጎብኚዎች የማሰባሰብ ሥራ መጠናቀቁን ያስረዳሉ። መረጃዎችን የማደራጀትና የመተንተን ሥራ መካሄዱንም ይገልፃሉ።

አጋርነትና ትብብር

የቱሪዝም ሚኒስቴር ተግባርና ሃላፊነቶች ከሆኑት መካከል ትብብርና አጋርነት አንዱ ነው። ከዚህ አኳያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከቱሪዝም ተዋናዮች ጋር አጋርነትና ትብብርን በመፍጠር የሕዝብ ግንኙነት አሠራርንና ውጤታማነት ለማሻሻል የተለያዩ ሃላፊነቶችን እንደተወጣ አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ። ከዚህ መነሻ በመንግሥትና በግል ዘርፉ እንዲሁም አጠቃላይ በቱሪዝም ተዋንያን መካከል አምዳዊና የጎንዮሽ ትስስሮችን ለማጠናከር በማሰብ ከቱሪዝም እና ሆቴል ባለድርሻ አካላት (ከአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከሆቴሎች ማህበራት፣ ከሆቴል ባለቤቶች፣ ከአስጎብኚ ባለሙያዎች፣ ከሆኑት አስተባባሪዎች) ጋር ሰባት የምክክር መድረኮች መከናወናቸውን ይገልፃሉ። በዚህም ጥራት ያለው የቱሪዝም አገልግሎት እና የቱሪስቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ለማስተባበር በቱሪዝም ዙሪያ የተፈጠረ የጋራ ስምምነት መሆኑን ያስረዳሉ።

ቅርስ ጥገና የተፈጥሮ ጥበቃ

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የቅርስ፣ የአርኪዮሎጂና መሰል ሌሎች በርካታ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ነች። በተለይ ጥንታዊ ቅርሶች በስፋት ከሚገኝባቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች። በሰው ልጅ የኪነ ህንፃ ታሪክ ወደር የማይገኝላቸው ሀብቶችን ይዛለች። ከእነዚህ የኪነ ህንፃ ቅርሶች መካከል አብዛኛዎቹ በርካታ ዘመናትን (ምእተ ዓመታትን) የተሻገሩ ናቸው። ከቅርሶቹ ባሻገርም እንክብካቤና ጥበቃ የሚሹ የተፈጥሮ ፓርኮች፣ መልከዓ ምድሮችና የዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች በስፋት ይገኛሉ።

በጊዜ ቆይታቸው የተነሳ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥገና የሚሹ በርካታ ቅርሶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ የኪነ ህንፃ ሀብቶች መካከል የላሊበላ፣ የጅማ አባጅፋ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ገለፃ እነዚህን ቅርሶች ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። ከተግባሮቹ መካከልም ከፈረንሳይ መንግሥት ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እና ቅርስ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በላሊበላ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የባህል/ቱሪዝም ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው። በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሶስቱንም ግሩፕ የጉብኝት ማዕከሎች እርስ በእርስ የሚገናኙ ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና ድልድዮች ከፈረንሳይ መንግሥት ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እና ቅርስ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ሌላው የጥገናና ልማት ሥራ የተተገበረው በጅማ አባ ጅፋር መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ። በዚህም የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት ካለው ታሪካዊ ፋይዳ፣ ልዩ የቤተ መንግሥት ኪነ ህንፃ ግንባታና በቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ ያሉ ቱሪስቶችን መሳብ የሚችሉ በርካታ መስህቦች ምክንያት ቅጥር ጊቢው እንዲለማና አካባቢው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። ከላሊበላና ከጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት እድሳትና የልማት ሥራዎች ባሻገር በኮንሶ የዩኔስኮ አደባባይ ግንባታ ሥራዎች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በተጠሪ ተቋማት፣ በክልሎችና በልማት ትብብር ድርጅቶች መሠራቱን ተናግረዋል።

ሌላው በበጀት ዓመቱ (በ2016 ዓ/ም) ከተተገበሩ ሥራዎች መካከል የተፈጥሮ ጥበቃ እንደሚገኝበት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ይናገራሉ። በዚህም በተፈጥሮ ሀብትን ጥበቃ በኩል የስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የእንግዶች ማረፊያ የሚሆን የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ (Community Lodge)፣ መታጠቢያ ቤቶች፣ የካምፒንግ ግራውንድና የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን ያስረዳሉ። ከስንቅሌ ባሻገር በአፋር ክልል በኤርታኢሌ የእሳተ-ገሞራ ድንቅ የተፈጥሮ ትዕይንት መመልከቻ ቦታ ላይ ለጎብኚዎች መወጣጫ የሚሆን ደረጃዎች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

ቱሪዝም ኢንቨስትመንት

አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በ2016 ስኬታማ አፈፃፀም ካሳየባቸው ተግባራት መካከል የቱሪዝም ኢንቨስትመንት መሆኑን ባደረሱን መረጃ ያመለክታል። በዋናነትም በዘርፉ ምቹ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት አሠራሮችን በማጠናከር፣ ውጤታማ የማበረታቻ አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋት እና የኢንቨስትመንት መረጃዎችን በጥራት ተደራሽ በማድረግ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ቁጥር ማሳደግ ብሎም የግል ዘርፉን ሚና የበለጠ የማጎልበት ሥራ መሠራቱን ይናገራሉ።

የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስተዋወቅና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ፎረም ተካሂዷል ያሉት የስትራቴጂክ ቡድን መሪው፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲሠማሩ ለማድረግ ታቅዶ በተለያዩ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፎች 132 ባለሀብቶች ሴክተሩን መቀላቀላቸውን ይገልፃሉ። እንዲሁም 16 ባለሀብቶች በሆቴልና መሰል አገልግሎት ንግድ ዘርፎች ኢንዱስትሪውን እንደተቀላቀሉ ይናገራሉ። የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ (የተመዘገቡ) 148 የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በክልል ኢንቨስትመንት መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ይናገራሉ። ለባለሀብቶች አስፈላጊው የኢንቨስትመንት ድጋፍና ትብብር እንደተደረጋላቸውም ይገልፃሉ።

ቁጥሮች ምን ይላሉ?

አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደሚገልፁት በቱሪዝም ዘርፍ ቀጥተኛ የሆነ 117 ሺህ 579 የሥራ እድሎች ተፈጥሯል። ከዚህ መካከል 47 ሺህ 32 ቋሚ የሥራ እድሎች ሲሆኑ 70 ሺህ 547 ደግሞ ግዜያዊ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በ2016 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን 148 ሺህ 50 የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ተናግረው ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢም አራት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ያነሳሉ። የሀገር ውስጥ ጎብኚ 40 ነጥብ ሰባት ሚሊዩን ጎብኚዎች እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል። በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ገቢም 65 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ተናግረዋል።

በ2016 ዓ.ም ሀገርን የማስተዋወቂያ መድረኮች (Trade fairs, Expos & Road Shows) ላይ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በቤልጅየም፤ በፓኪስታንና በቻይና በተካሄዱ ስድስት የንግድ ትርዒቶች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ መቻሉን ያስረዱት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ በበጀት ዓመቱ ውስጥ 28 ዓለምአቀፍ ኹነቶች በኢትዮጵያ መካሄዳቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪ ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ሀብቶች ልዩታ (National Tourism Resource Mapping) በማካሄድ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ዓይነት፣ መጠንና ስብጥር በጥልቀት በመለየት በተቀናጀ መንገድ (Clustering) ለማልማት የሚያስችሉ የመዳረሻ ልማት ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ተግባራዊ መደረጉንም አስረድተዋል።

ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት መረጋገጥ ወሳኝና ደጋፊ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ በማድረግ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋትና ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ኢትዮጵያ ተመራጭ የጎብኚዎች መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ቴዎድሮስ በዚህም ዘጠኝ የቱሪስት መደራሻዎች የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎች እንደተደረገላቸው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል።

በመጨረሻም አቶ ቴዎድሮስ በሰጡን መረጃ እንዳመለከቱት፤ ከቪዛ አሰጣጥ ጀምሮ ጎብኚዎች ኢትዮጵያ ገብተው እና ጎብኝተው እስኪመለሱ ድረስ ባለው የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻል፣ አሠራሮችን ማዘመንና የአገልግሎት ልህቀትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሆቴሎች የጥራትና ደረጃ አሰጣጥ መስፈርቶች ፀድቀው ሥራ ላይ በመዋላቸው የደረጃ አሰጣጥ ሥራ ተጀምሯል። በዚህም ስልሳ አራት (64) የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደረጃ ተመድበዋል። ለ356 አገልግሎት ሰጪ ድርጀቶች ብቃታቸው ተረጋግጦ እውቅና ተሰጥቷል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You