አዲስ አበባ:- ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ያላስደፈሩትን የሀገር ነፃነት የእኛ ትውልድ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ አለበት ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ። የሉዓላዊነት ቀን “ህብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ዕለቱን በማስመልከት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የጳጉሜን ወር ስናስብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀናቱን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች በመሰየም እያከበርን እንገኛለን:: ዕለቶቹ ሀገር ለመገንባት፣ ትውልድ ለማፅናት የምንጓዝበትን መንገድ የምንፈትሽባቸው እና ለሀገር ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ዜጎቻችንን በክብር የምናስብባቸው ናቸው።
ዘንድሮም በጳጉሜን ቀናት ከሚታሰቡ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሉዓላዊነት ቀን ነው ያሉት ኢንጂነር አይሻ፤ ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ያላስደፈሩትን የሀገር ነፃነት የእኛ ትውልድ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ አለበት ብለዋል።
ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን ተብሎ “ህብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ያሉት ኢንጂነር አይሻ፤ የበዓሉ ዋና ዓላማ ፈተናዎችን ወደ መልካም እድል በመለወጥ ነፃነቷ የተጠበቀ፣ እድገቷ የተረጋገጠና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስን በተመለከተ መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የሉዓላዊነት ቀን ሲከበርም ዛሬ ማለዳ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በክብር የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ውድ ዋጋ ለከፈሉ ጀግኖች የጧፍ ማብራት፣ ምስጋና፣ መልዕክት፣ የሕሊና ጸሎት እና ቃል-ኪዳን የመግባት ሥነ-ሥርዓት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
እነዚህ ሥነ-ሥርዓቶች እንደተጠናቀቁም በሳይንስ ሙዚየም የአውደ-ርዕይ ዝግጅት፣ የሉዓላዊነት የሕፃናት መዝሙር ይፋ የማድረግና የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም አብራርተዋል።
ከቀኑ 6 ሰዓትም በመላ ኢትዮጵያ ለሁለት ደቂቃ ኢትዮጵያውያን ባሉበት በመቆም ለሉዓላዊነት ለተከፈለው ዋጋ ክብር የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በማካሄድ ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የበዓሉ አዘጋጆች የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም