የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ከየት ወዴት?

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በቅርብ ጊዜ ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በአምስተኛ ደረጃ ላይ ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጉዞ መነሻው፣ አሁናዊው ሁኔታና መጻዒ ዕድሉ ምን ይሆን?

የፐብሊክ ፖሊሲና ምጣኔ ሀብት ምሑሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ለውጥ ታጅቦ የመጣ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ኢትዮጵያ በአሰቃቂ ረሀብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ሲጠቀስ ነበር፡፡ ስሟም በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ውስጥ እንኳን ተመዝግቧል። ነገር ግን ይህ ምስል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ ሲሆን፤ በተለይም በዲያስፖራው ያላሰለሰ ጥረት

ስሙ ከመዝገበ ቃላቱ ላይ ከተወገደ በኋላ ኢትዮጵያ ከረሃብ ውጪ ረዥም ጊዜ አሳልፋለች:: ከደርግ የመጨረሻዎቹ ዘመናት ጀምሮ ኢኮኖሚዋ እያንሰራራ መጥቷል::

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳየች የቆየች ሀገር ናት የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በርካታ የዓለም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የልማት ተንታኞች እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በአርአያነት በማሳየት አንዳንዶች “የአፍሪካ ቻይና” የሚል ስያሜ ሲሰጡ እንደቆየ ጠቅሰዋል። ይህ ፈጣን እድገት በተለይ እ.ኤ.አ. በ2010 እና 2020 መካከል ጎልቶ የታየ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗን በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተከታታይ ሪፖርት መደረጉን አንስተዋል፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱት ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ እንቅፋት መፍጠራቸውን ምሁሩ ተናግረዋል:: የኮቪድ19 ወረርሽኝ፣ የውስጥ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት እና በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ጦርነት የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በማስተጓጎል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መዘናጋት ማስከተሉንም ጠቅሰዋል:: ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት ሲጨምር በኢትዮጵያ እስከ 30 በመቶ ከፍ ብሎ እንደነበር አስታውሰዋል:: ይህ አሁን ላይ ወደ ታች በመውረድ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ዕድገት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ባለፉት ሶስት ዓመታት ጦርነት ያስከተለው የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ እስከ 7 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሏ ከፍተኛ ለውጥ ነው ብለዋል::

የሀገሪቱን የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ማለትም እንደ መንገድ ግንባታ፣ ግድቦች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታዎች ለዚህ ዕድገት ወሳኝ አንቀሳቃሾች መሆናቸውንም ነው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያብራሩት:: እነዚህ እድገቶች በተለይ ለወጣቶች የሥራ እድል የፈጠሩ እና ለኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ ጉዞ መሰረት የጣሉ መሆናቸውንም ያስረዳሉ::

ምሁሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የበለጠ ማጠናከር የሚቻለው የዋጋ ንረትን፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን እና የጸጥታ ችግሮችን ጨምሮ የተለያዩ የውስጥ ጉዳዮችን በመፍታት እንደሆነ ይናገራሉ::

አንዳንዶች “አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ በአይ ኤም ኤፍ፣ በዓለም ባንክና ሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጫና እየተፈጠረብን ነው ያለው:: ጫናው እየተፈጠረ ያለው በአብዛኛው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ስላጣች ነው” የሚል ፕሮፖጋንዳ ያናፍሳሉ በማለት፤ እንደ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጫና ለኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚያሰጋ እንዳልሆነ አስምረውበታል። ይልቁንም እነዚህ በአባል ሀገራት የተመሰረቱት ተቋማት ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዋን በብቃት መተግበሯን ከቀጠለች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት ጠቃሚ አጋሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታሉ፡፡

“ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ወደፊት የኢኮኖሚ ጉዞ እድገቷን የምታስቀጥልበት፤ የንግድ ሚዛኑ ተስተካክሎ ከፍታ ላይ ሊደርስ የሚችልበት መሆን አለበት:: ለዚህ ደግሞ ዋና ዋና የሚባሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች መሬት ላይ ወርደዋል:: ይህንን በአግባቡ መተግበር ይገባል” ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የወሰደው የፖሊሲ እርምጃዎች፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀድ፣ የካፒታል ገበያ መመሥረት፣ በገበያ ዋጋ ላይ የመገበያያ ገንዘብ አወሳሰን አዎንታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሀገሪቷ ውስጥ ከተሰሩ ከፍተኛ መሰረተ ልማቶች ውስጥ ከ100ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች መሰራታቸውን፤ ይህ ደግሞ የገበያ ትስስሩን በመፍጠር ጉልህ ድርሻ እንደነበረው አስታውቀዋል:: በሀገሪቱ የሀይል ማመንጫና ግድቦች መሰራታቸውን፤ በንፋስ የሚሰሩ የኃይል ማመንጫዎችንም በሙከራ ላይ እንዳሉና ኃይል ደግሞ ለኢንዱስትሪውም ሆነ ለእርሻ እድገት ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በሌላ በኩል የንግድ ሁኔታውም መስፋፋቱን፤ የአገልግሎት ሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ ማድግ እንደቻለ፤ ይህም ሰዎች ሥራ ላይ በሰፊው መሰማራታቸውን አመላካች መሆኑንና እነዚህ መሠረተ ልማቶች በሙሉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አብራርተዋል::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ አንድ እድገት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት የሚመጣ አይደለም:: ኢትዮጵያ የጀመረችው የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ፤ ድህነት ቅነሳና ዘላቂ የልማት ግብ ፕሮግራም ተብሎ በተቀመጠው የአምስት ዓመት አቅድ፤ በሁለት ምዕራፍ በተተገበረው የእድገትና ትራንስሮርሜሽን እቅድ፣ እንዲሁም የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ተግባራዊ ባደረጋቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች አማካኝነት የተመዘገበ ነው ይላሉ::

በኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል:: ዩኒቨርሲቲዎች ተገንብተዋል:: በርካቶች የትምህርት እድል አግኝተዋል:: የትምህርትና የጤና ተደራሽነት ተስፋፍቷል:: የምዕተ ዓመቱ ግቦች የሚባሉትን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተተገበረውን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ አሟልታለች ነው ያሉት::

ሆኖም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮች በፍጥነት ካልተፈቱ እነዚህን ጥረቶች ሊያበላሹ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል:: ምሁሩ በተለይ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተጠናቀቀው የሰሜኑ ጦርነት በኋላ ለመልሶ ግንባታው ከወጣው ከፍተኛ ሀብት አንፃር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ያለውን የልማት አፈጻጸም አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመላከተው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ እመርታ በማስመዝገብ በመንግሥት የሚመራ የልማት እቅድ እና በቁልፍ ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንቶች ተንቀሳቅሳለች። ሀገሪቱ ተከታታይ እና ፈጣን የኢኮኖሚ መስፋፋት ያስገኙ ታላላቅ የልማት ስትራቴጂዎችን በመተግበር ኢትዮጵያን በአፍሪካ የዕድገት ተምሳሌት አድርጓታል። ይሁን እንጂ ጉዞው ያለ ተግዳሮቶች አልነበረም፣ እናም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የወደፊት ጉዞ እነዚህን መሰናክሎች በመቅረፍ እና ፍጥነትን በማስቀጠል ላይ የተመሰረተ ነው ይላል።

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አስደናቂ ቢሆንም ለውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ጫናዎች የተጋለጠ ነው። ለወደፊት የዕድገት ስኬት የሚወሰነው መንግሥት እነዚህን ተግዳሮቶች የሚቀርፉ ማሻሻያዎችን በመተግበር፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የዕድገት ጥቅማ ጥቅሞች በሕዝብ መካከል በስፋት እንዲካፈሉ ማድረግ ነው። በትክክለኛ ፖሊሲዎች ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት ወደ በለፀገ እና የማይበገር ኢኮኖሚ የምታደርገውን ለውጥ የማስቀጠል አቅም አላት።

ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በአምስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው አይ ኤም ኤፍ 205 ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በማስመዝገቧ እንደሆነ አመልክቷል። ይህ የኢኮኖሚ እድገቷ ከዓለም በ57ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ያሳያል።

በአፍሪካ በኢኮኖሚ ግዝፈት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሀገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ናይጄሪያ መሆናቸውን መረጃው ጠቅሷል።

ሀገሪቱ ሰላሟን ማስጠበቅ እና የዕድገት ጉዞዋን ማስቀጠል ከቻለች የወደፊት ኢኮኖሚያዊ ተስፋዋ ብሩህ ነው ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ የአካባቢ አስተዳደር አካላት በተለይም በወረዳ ደረጃ ያሉት የልማት አንቀሳቃሾች ማብቃት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህ ባለፈም ስር የሰደደ እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት እንዳያደናቅፍ ሙስና እና ሌብነትን ለማጥፋት የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You