መሠረታዊ ለውጥ የሚሻው የስፖርት ዘርፍ

በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት በርካታ ጉዳዮች ተከስተዋል። እነዚህ ክስተቶች የተለያዩ ቢሆኑም፤ አብዛኛዎቹ የሚያመላክቱት ግን የኢትዮጵያ ስፖርት አሁንም ለውጥ የሚያስፈልገው ነው። የየትኛውም ስፖርት ስኬትም ሆነ ውድቀት ጀርባ ታሪክ ቢጠና ሀገር አቀፍ አሠራርና መዋቅር የራሱ ሚና እንዳለው እርግጥ ነው። በመሆኑም ስፖርቱን የሚመራው አካል ከዘመኑ ጋር የሚሄድ እና ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠራ በሚችል መልኩ የተቃኘ ስርነቀል የአሠራር ሪፎርም ያስፈልገዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት በዘመናዊ መልኩ ከተደራጀ አንድ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል። ይሁንና አሁንም ድረስ ከወቅቱ ጋር መጓዝ አለመቻሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ ግልጽ የዘመኑ አካሄዶችን መከተል ባለመቻሉ ለውጥ ሳይታይበት ባረጀና ባፈጀ መንገድ መዝለቁን የስፖርት ባለሙያዎች እንዲሁም ሰነዶች ይጠቁማሉ። ሀገራት በስፖርታዊ የውድድር ተሳትፎ ውጤታማ መሆን ባይችሉም ሌሎች ስፖርታዊ ሁነቶችና ስፖርት ነክ ጉዳዮች ላይ አተኩረው በመሥራታቸው ከዘርፉ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በማግኘት ኢኮኖሚያቸውን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ስፖርት ከ100 ዓመታት በፊት እንደነበረው ዛሬም የመንግሥትን እጅ እየጠበቀ ቀጥሏል።

ስፖርቱ ላለፉት ዓመታት ሲመራበት የቆየው መዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ስልት ለስፖርቱ ውጤታማነት ያበረከተው አስተዋጽኦ እምብዛም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ ተቀርጾ በሥራ ላይ ከዋለ ወደ 27ኛ ዓመት እየተንደረደረ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ግን በትክክል ሊተገበርም ሆነ ሊሻሻል አልቻለም። ስፖርቱ በሕዝባዊ እና መንግሥታዊ አካላት የተደራጀና ኃላፊነታቸውንም በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም የሁለቱም አካላት ሥራ አሁንም ድረስ መደበላለቅና አንዱ የሌላኛው ላይ ጫና ማሳረፋቸው አልቀረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቀድሞ ይታይ የነበረው ሀገራዊ ስሜት መሸርሸርና የውጤት ቀውስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከዚሁ ጋር ሊያያዝ የሚል ነው።

በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የተከሰተው ጉዳይ ለዚህ በቂ ማሳያ ይሆናል። በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወጥ የሆነ የብሄራዊ ቡድን አሠራር አለመኖር፣ የአትሌቶችና የፌዴሬሽኑ ግንኙነት፣ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ያልተለመደው የአትሌቶች እጅ መስጠት፣ በፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መካከል ያለው ግንኙነት፣ የተጠያቂነት አካሄድ ወዘተ ለውጥ ፈላጊ ጉዳዮች መሆናቸው ታይቷል። ነገር ግን ክስተቱ የእነዚህ አካላት ብቻም ሳይሆን በሌሎች የስፖርት ማህበራትም በተለያየ መጠን መሰል አግባብነት የሌለው ሁኔታ መኖሩን የሚያንጸባርቅ ነው። ይኸውም የኢትዮጵያ ስፖርት ሁለንተናዊ ሪፎርም ግድ እንደሚለው በቂ ማሳያ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን በመጠቀም ሁሉን አቀፍ የስፖርት ልማት ምዘና በማድረግ እንዲሁም ጥናት ላይ በመመሥረት ሀገራዊ የስፖርት ሪፎርም ሰነድ ተዘጋጅቶ ነበር። ይህንን ተከትሎም በአጠቃላይ መንግሥታዊ የስፖርት አደረጃጀት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ያስችላል የሚል አሠራር ተግባራዊ ሊሆን ችሏል። በሥራ ላይ ከዋሉት መካከል አንዱ የሆነው የስፖርት ማህበራት ከመንግሥት በጀት ጠባቂነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሙከራው በአንጻራዊነት የተሻለ ቢሆንም ውጤታማ ሊያሰኘው በሚል ሁኔታ ላይ ይገኛል ለማለት ግን አያስደፍርም። በሌላ በኩል ስፖርቱን በሚመራው ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ አካል መካከል ያለው ግንኙነትና አስተዳደራዊ አቋም አሁንም ድረስ አጠያያቂ በሆነ ሁኔታ መጣረሱን ቀጥሏል።

በታዳጊና ወጣቶች ስፖርት ልማት፣ ዓለም አቀፍ የውድድር ተሳትፎ፣ የስፖርት ማህበራት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ምርጫና የአመራረጥ ሂደት፣ ስፖርቱን በሚመራው መንግሥታዊ አካል ክልሎች እና የስፖርት ማህበራት ኃላፊነት፣ ለአሠራርና አፈጻጸም ምቹ ያልሆኑ ደንቦችና መመሪያዎች፣ የበጀት እጥረትና ክፍፍል ወዘተ አሁንም ለውጥ ፈላጊ ጉዳዮች ናቸው። ስፖርቱን እንደሚፈለገው ወደፊት እንዳይጓዝ መሰናክል የሆኑ ጉዳዮችን የተዘጋጀው የሪፎርም ሰነድ አመላካች ቢሆንም በቀጥታ ሥራ ላይ አለመዋሉና የተጠያቂነት ሂደቱም ደካማ መሆኑን እንደምክንያት ማንሳት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ ውጤት እንድታስመዝገብ፣ ታላላቅ የስፖርት ሁነቶችን እንድታዘጋጅ፣ የስፖርት ማህበራት ከመንግሥት እገዛ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ከሀገር አልፎ አህጉር እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራትን የሚመሩ ሥራ አስፈጻሚዎችን እንድታፈራ፣ ኢኮኖሚውን የሚደግፍ ገቢ እንዲመነጭ፣ ለሚከሰቱ የአሠራር ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ወዘተ ዘርፉ መሠረታዊ የሆነ ሪፎርም ያስፈልገዋል። ለዚህም አስፈጻሚው አካል በትኩረት ሊሠራ ይገባዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You