በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተከፈለው ግብር 83 በመቶ ያህሉ በፍቃደኝነት የተከፈለ ነው

88አዲስ አበባ፡በ2016 በጀት ዓመት ከተከፈለው ግብር 83 በመቶ የሚሆነው በፍቃደኝነት የተከፈለ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በገቢዎች ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት እና ከግብር ከፋዮች ጋር በግብር አሰባሰብ ዙሪያ በትናንናው ዕለት ተወያይቷል።

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር እንደገለፁት፤ እንደ ሀገር በፍቃደኝነት የሚሰበሰበው ግብር እየጨመረ መጥቷል። በ2016 በጀት ዓመት 83 በመቶ የሚሆነው ግብር በፍቃደኝነት የተከፈለ ነው።

በቀጣይም የግብር አከፋፈል ሥርዓቱ ምቹ እንዲሆን በቴክኖሎጂ በማዘመን የፍቃደኛ ግብር ከፋይ ዜጋ መጨመር ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማህበረሰቡ ምን ያህል ግብር እንደተጣለበት ከማወቅ እስከ ክፍያ ያለው ሂደት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አማራጭ በቤቱ ሆኖ እንዲከፍል የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ግብርን በአግባቡ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይም የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

የግብር ከፋይ ኦዲት የማድረግ አቅምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪሮስ ደበሱ በበኩላቸው፤ በጽህፈት ቤቱ በፍቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህል እየተሻሻለ መጥቷል።

በ2016 በጀት ዓመት በጽህፈት ቤቱ 65 በመቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በፍቃደኝነት የከፈሉ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ኪሮስ፤ የተቀረው ግብር በተደረገ የሕግ ማስከበር ሥራ የተከፈለ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ፍቃደኝነት ግብር የሚከፍሉ ዜጎችን ቁጥር መጨመር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የሕግ ማስከበር ሥራውም በፍቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህሉን የሚያበረታታ መሆን ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኪሮስ ገለጻ፤ ለእቅዱ መሳካት ለግብር ከፋዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መከናወን ይኖርባቸዋል። የግብር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን መክፈል የሚችሉበት ኢ-ፋይል የተሰኘ ሥርዓት ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህም 96 በመቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በሥርዓቱ እንዲከፍሉ መደረጉን ተናግረዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም

Recommended For You