
አዲስ አበባ፡– መከላከያ ሠራዊት የተስፋፊዎችን የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ትናንት በ47ኛው የምስራቅ ዕዝ ምሥረታ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የእዙን የምሥረታ በዓል ከሰላም ወዳዱ የሶማሌ ሕዝብና ከጀግናው የእዙ አመራርና አባላት ጋር ለማክበር በመቻሌ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
እእዙ ከምሥረታው ማግስት ጀምሮም ተስፋፊውን የዚያድ ባሬ ጦር ጨምሮ የተለያዩ የሽብር ሃይሎችን በመከላከልና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት ሲመክት የቆየ አንጋፋና ጀግና እዝ መሆኑንም አንስተዋል።
እዙ የዚያድ ባሬ ጦር ወደ መሀል ሀገር ያደረገውን ወረራ በመመከት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የሀገሩን ዳር ድንበር እንዳስከበረ አስታውሰዋል።
የሀገርን ሰላም፣ ሉዓላዊነትና አንድነትን በማስጠበቅ ረገድ እዙ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉና የሠራዊቱ መመኪያ መሆኑን ገልጸው፤ ሠራዊቱ ሀገርን ለመውረር የሞከሩ ሃይሎች ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ኢትዮጵያን ለመውረር ግፊት ሲያደርጉና ግጭት ሲያባብሱ የነበሩ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አብረው የቆሙ ቢመስሉም በሽንፈት ጊዜ እንደማይገኙ ከታሪክ መማር ይገባል ብለዋል።
ሠራዊቱ በቀጣናው ያለውን የተስፋፊዎች የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነው ፊልድ ማርሻሉ የገለጹት።
ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ከሞከሩ ዳግመኛ እንዳያስቡት አድርጎ ለመመከት የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩንም ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን የመከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምስራቅ እዝ የተገነባውን የገርባሳ አምፊ ቴአትር መርቀዋል። በመቀጠልም በሀረር ከተማ ተገኝተው የምስራቅ እዝን የ47 ዓመታት ጉዞ የሚዘክር ሙዚየምን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰና ጀኔራል ጌታቸው ጉዲናን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም