አንድ ወዳጄ ከሀገር ውጪ ሄዶ ለአንድ ሁለት ዓመታት ቆይቶ መጣና ተገናኘን። እንዴት ነበር ቆይታ? ሀገሩን እንዴት አገኘኸው? እያሉክ ጥያቄ ደረደርኩ። “ቆይታ ጥሩ ነበር” እያለ ወጉን ቀጠለ፤ እኔም ማድመጤን። “የሀገሩን ነገር አታንሺው” ሲል በቁጭት መንፈስ አወጋኝ ።
“በሙቀት ወቅት ልብ የሚያጠፋ፣ መተንፈስን የሚከለክል የት ልድረስ? የት ልግባ? የሚያሰኝ ወበቅ ነው። ኤሲ ካለበት ቦታ ወጣ ሲባል ወላፈኑ ነው የሚጋረፈው። እምነግርሽ የአንገት መጣመም ድረስ ነው አደጋው በክረምቱም በበጋውም። ክረምቱ ደግሞ ሌላ ተዓምር የሚያሰኝ ነው ።
እጅን ሳይቀር በጓንት፣ ቤቱ፣ መኪናው፣ መኝታ ክፍሉ … የሰው ልጅ ባለባቸው ቦታ ሁሉ በኤሌክትሪክ ማሞቂያ (ሂተር) ነው ነፍስ የሚዘራው። ምን አለፋሽ በዚህ ሁሉ የአየር ንብረት መቃወስ ውስጥ እነሱ ’ገሀነምን ገነት አድርገው እየኖሩ ነው።
እኛ ደግሞ ገነቱን…” አለ። በውስጤ በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ አልኩ። ሁሉም ሰው በዚህ ልክ ቢያየውና ቢሰማው ምንኛ ሀገራችን የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለማሳካት ግንባር ቀደም በሆንን ኖሮ፤ የዓለምን የአየር ንብረት ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖው ከፍተኛ መሆኑን በተረዳነው ነበር።
አረንጓዴ ዐሻራ የሚለው ቃል በሁሉም ሰው አዕምሮ ውስጥ አለ። አረንጓዴ ዐሻራ ሲባልም ከፊት ድቅን የሚለው በየዓመቱ የዓለምን ክብረወሰን ለመስበር የሚደረገው የአንድ ጀምበር ብዙ ችግኞችን የመትከል የዘመቻ ቀን ሊሆን ይችላል። አረንጓዴ ዐሻራ ከዛ ያለፈ ነው ትልቅ መልዕክት አለው። ከዓላማው ጎን ለጎን አቅዶ የማሳካት ትርጉሙም ከፍ ያለ ነው። ከሀገር አልፎ ለዓለም የሚተርፍ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት አንድ ሁለት ትዝ የሚሉኝ ነገሮች ነበሩ። ችግኝ መትከል እና የደን ጥበቃ፤ በወቅቱ ቅጥረኛ የደን ጠባቂዎች ነበሩ። ደኑ ውስጥ ገብቶ ዛፍ ሲቆርጥ የተገኘ ሰው ይቀጣል። ይታሰራል። ሌላው ደግሞ ማንኛውም ሰው በመኖሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛፍ ወይም ፅድ ለመቁረጥ ከፈለገ ለቀበሌው ማመልከቻ ጽፎ ስንት ዛፎችን እንደሚቆረጥ አሳውቆ ፍቃድ ይጠይቃል።
ያን ጊዜ ከቀበሌው የሚሰጠው ፈቃድ አንድ ዛፍ ስትቆርጥ ሦስት ዛፍ መትከል ግዴታ ነው የሚል አስገዳጅነት ያለው ፈቃድ ነው። በዚሁ መሠረት በቆረጠው ዛፍ ምትክ ችግኞችን ይተክላል፤ ውሀ እያጠጣ ይንከባከባል። ይሄ የዛፎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው፤ በወቅቱም የዛፎቹ ደኅንነት የተጠበቀ ነበር ማለት ይቻላል ከሞላ ጎደል።
ይሁን እንጂ የሥርዓት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ብዙ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ ችግኝ መትከል ቀረ ይባስ ብሎም የነበሩ ደኖች ሁሉ ተጨፈጨፉ፤ የደን ሽፋኑም ከነበረበት አዘቅዝቆ ወደ ሦስት በመቶ ደረሰ። ይሄ ያሳሰበውና የአየር ንብረት ለውጥ ምን ይዞብን እንደመጣ የተረዳው የብልፅግና መንግሥት ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ታሪክ ሠርቶ ዐሻራ አስቀምጦ ለማለፍ በመላ ሀገሪቱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ዘረጋ።
ዛሬ ቁጭት በተሞላው መልኩ በአረንጓዴ ዐሻራ ደኖችን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። 200 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር ተብሎ በ2011 ዓ.ም በወርሐ ሐምሌ የተጀመረው የዓለምን ክብረወሰን የመስበር እቅድ በአንድ ጀምበር እውን ሆኖ ዓለምን አስደምሟል። እያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ መከላከያ ሠራዊት፣ የመንግስት ባለሥልጣን … ሁሉ በቆራጥነት እጃችን ጭቃ ሲነካው ነው ሀገራችን የአረንጓዴ ዐሻራ ተምሳሌት የምትሆነው፤ የተፈጥሮ አደጋን የምንቆጣጠረው፤ የአፈር መሸርሸርን የምናቆመው፣ ከከርሰምድር ውሃ ማግኘት የምንችለው … ብሎ ክተቱን ተቀላቀለ።
አረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ይሆናል ብሎ ስጋት የገባው ግን አልጠፋም። ቢተከልም ዞር ብሎ የሚያየው ተንከባካቢ አይኖርም የሚል ግምትም ነበር። ይሁን እንጂ ይህንን ስጋት በገፈፈና በተጠናከረ መልኩ እስካሁን ተከላውም እንክብካቤውም ቀጥሏል። የደን ሽፋኑንም ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ 15 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሠራው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ ታዲያ ሀገራችንን ማንም ሳይጎተጉታት፣ ከማንም ድጋፍና ርዳታን ሳትጠብቅና ሳታገኝ ነበር። አሁንም የሯሷን አስተዋፅዖ ለዓለም እያበረከተች ያለችው ከነበራት አቋሟ ዝንፍ ሳትል ነው። ዘንድሮም ልክ እንደተከታታዮቹ ዓመታት ሁሉ በቀነ ቀጠሮ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ቀን 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዕቅድን ማሳካት ተችሏል።
ኢትዮጵያውያን ፀሐይ፣ ዝናብ፣ ውርጭ፤ ዳገት መውጣትና መውረድ ሳይፈትናቸው ነው 600 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀንበር እንትከል ብለው ወስነው ከዚያ በላይ ማሳካት እንደሚችሉ ያሳዩት። ይህን ያክል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በአንድ ጀንበር መትከል ቀላል ሥራ አይደለም። ለኢትዮጵያ ልማት እና እድገት መሠረት መጣል መሆኑን በመገንዘብ ነው።
በአንድነትና በቆራጥነት ለአንድ ዓላማ የገቡበት ባይሆን ኑሮ 600 ሚሊዮን ችግኝ መትከል አይችሉም ነበር። ነገር ግን ካለንበት ድህነት ለመውጣት፣ ካለንበት ሁኔታ ተሻግሮ የሚቀጥለውን የብልፅግና ምዕራፍ ለመጨበጥ እንደዚህ ያሉ ሀገራዊ እቅዶችን ማሳካት፤ እንደዚህ ያሉ ልማቶችን መደገፍ የግድ በመሆኑ ጭምር ነው። ምክንያቱም ዛሬ በዚህ መልኩ ካለፋን፣ ዛሬ በዚህ መልኩ ለሀገራችን አስተዋፅዖ ማድረግ ካልቻልን ነገ ለልጆቻችን የምናስቀምጠው ሀገር አይኖርም። ከታሪክ ተወቃሽነትም አንድንም ።
በ2016 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ነው የታቀደው። በጥቅሉ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል ። ይሄ የሚያሳየው መተባበር ካለ ምንም ነገር መሥራት እንደሚቻል ነው። ምንም ነገርን አቅደን ማሳካት እንደምንችል ነው። ዛሬ 40 ቢሊዮን ችግኝ ተከልን ስንል ለዚህ ምን ያህል ሀብት አወጣን ብለን ማስላት ደግሞ ያስፈልጋል።
ምን ያህል ጉልበት አፈሰስን? ምን ያህል ጊዜያችንን ለሥራ አዋልን? ብለን ሂሳብ መሥራት አለብን። የዚህ ሂሳብ ስሌቱ ሀገራችን ካላት የሀብት መጠን በጣም ብዙ ነው። በጣም ብዙ ሀብት አፍስሰን እጅግ በጣም ብዙ ሀብት ማፈስ ደግሞ ብልጥነት ነው፤ አዋቂነት ነው። ነገን ማሰብና ለነገ የተስተካከለ የአየር ንብረት ለመጪው ትውልድ ማኖር ነው። ይህንን እያሰብን የምንሠራው ሥራም ውጤታማ ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ የጀመርነው ጠንከራ ተነሳሽነት ደግሞ ችግኞችን በመንከባከብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ችግኝ ማለት ሕጻን ልጅ ነው። ሕጻን ልጅ ምግብ ውሀ እንክብካቤ ይፈልጋል፤ ችግኝም ይሄው ነው። የተከልናቸውን ችግኞች በፕሮግራም መንከባከብ ውሀ ማጠጣት፣ መኮትኮት ያስፈልጋል። እንደ ችግኝ ተከላ ቀን የችግኝ እንክብካቤ ቀንም ያስፈልጋል። የዚህ ሁሉ ሥራ ልፋትና ጥረት ውጤቱ የሚለካው በሚበቅለው የችግኝ መጠን ነው። ለአየር ንብረት ለውጥ በሚያደርገው አስተዋፅዖ ነው። እንደ አረንጋዴ ዐሻራ ቀን ሁሉ የችግኝ እንክብካቤ ቀንም ይኑር።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም