የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ – የ24 ሺህ ሰዎች እንጀራ

ወጣት እመቤት ለማ ትባላለች። የተወለደችው በዲላ ከተማ ሲሆን የ10ኛ ክፍል ትምህርቷንም ያጠናቀቀችው በዚሁ ከተማ ነው። እመቤት ለአራት ዓመታት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሠርታለች። አሁን የምትኖረውም በሀዋሳ ከተማ ነው።

በዲላ ከተማ ሆና የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በርካታ ሠራተኞችን መቅጠር እንደሚፈልግ ከቀበሌ ሰምታ ደስተኛ ሆና ሥራ መጀመሯን ገልፃ፤ በፓርኩ የመጀመሪያ የወር ደመወዟ 750 ብር ነበር። አሁን ላይ ግን የሦስት ሺህ ብር ተከፋይ መሆኗን ትናግራለች።

በፓርኩ የሥራ ዕድል ከማግኘቷ በፊት ምንም አይነት የሥራ ልምድ እንዳልነበራት እና አሁን ላይ የልብስ ስፌት ባለሙያ መሆኗን ተናግራ፤ ይህንን ሙያ ለመቅሰም በፓርኩ ከሁለት ወር በላይ ሥልጠና የወሰደች ቢሆንም አሁን ላይ ሱሪ መሥራት እንደማትችል ገልፃለች።

አንድ ሙሉ ሱሪ ለመሥራት 74 ማሽኖች መጠቀም እንደሚያስፈልግ እና ከዚህ ውስጥ ስድስት ማሽኖች ላይ በሚገባ መሥራት እንደምትችል የገለጸችው ወጣት እመቤት፤ ወደፊት ከፓርኩ ባገኘችው ሙያና ልምድም የራሷን ድርጅት መክፈት እንደምትመኝ ተናግራለች።

አባቷ መምህር እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው። ቤተሰቦቿ ራሷን እንድትችል እንጂ እነሱን እንድትረዳ አይፈልጉም። ሆኖም በአቅሟ ልክ ቤተሰቦቿን እንደምትደግፍ ተናግራለች።

እንደ ወጣት እመቤት ገለፃ፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር አለ። ማንኛውንም የተገኘውን ሥራ በመሥራት ራስን ለማሻሻል መሞከር ይገባል። ወጣቶች አላስፈላጊ ተግባራትን እና አልባሌ ቦታዎች ከመዋል ሥራ ለመሥራት መታተር አለባቸው። “እኔም አሁን ካለሁበት የተሻለ ሥራ እስካገኝ ድረስ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እሠራለሁ” ብላለች።

በፓርኩ ቁርስና ምሳ አለ። እራትና የቤት ኪራይ ግን በወርሐዊ ደመወዟ እየከፈለች እንደምትጠቀም ተናግራ፤ በፓርኩ የምንሠራው ሥራና የሚከፈለው ደመወዝ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ተናግራለች። የሚመለከተው አካል ይህንን ጉዳይ እንደራሱ ሊመለከተው ይገባል ብላለች።

ወጣት ወይንሸት እንድራሠም ልክ እንደ እመቤት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ ዕድል የተፈጠረላት ሲሆን አሁን ላይ የአሥር ወር ልምድ አላት። አባቷ ሽማግሌ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው። እነሱን ለመደገፍ ሥራ መጀመሯን ገልፃ አሁን ላይ ባለትዳርና የልጅ እናት መሆኗን ገልፃለች።

ወደ ሥራ ስትሄድ የአራት ዓመት ልጇን እናቷ ጋር እንደምታቆይ ተናግራ፤ በምታገኘው ወርሐዊ ገቢ ኑሮን መምራት እንደከበዳት ተናግራለች። ነገር ግን በፓርኩ ቁርስ እና ምሳ መኖሩ ሕይወቷን በትንሹም ቢሆን ማቅለሉን ገልፃ በፓርኩ ያገኘችው የሥራ ዕድል የሰው እጅ ከመጠበቅ እንዳላቀቃት ተናግራለች።

በወር የምታገኘው ደመወዝ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር መሆኑን ገልፃ ብሩ ትንሽ ቢሆንም ሕይወቴን ግን ደግፎኛል ብላለች። የወርሐዊ ደመወዙ መጠን ሊሻሻል እንደሚገባው ተናግራ ይህ መገኘቱ ራሱ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ገልፃለች።

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመስክ ምልከታ አድርገዋል። በእለቱ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሠላማዊት ካሣ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ ፕሮሞሽን እና የኢንቨስትመት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ተገኝተዋል።

አቶ ዘመን ጁነዲን በወቅቱ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፈር-ቀዳጅ የሆነው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት ዓመታት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማምጣት፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም ተኪ ምርትን በማምረትና ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የእውቀት ሽግግርን በመፍጠር በኩል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በፓርኩ ከ24 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የአንድ ዓመት አፈፃፀሙን እንኳን ብንመለከት በአውሮፓ እና በአሜሪካ ገበያዎች ላይ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የሆኑ አልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን በማምረት ከ44 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገኝቷል ብለዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኮርፖሬሽኑ ሀብቶች እንደሆኑ ሁሉ በፓርኮቹ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞቹም ሀብቶቹ ናቸው ያሉት አቶ ዘመን፤ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንዲስተካከል ማድረግ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊነት ባይሆንም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅርርብ እየሠራንበት እንገኛለን ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You