“ለመንገዱ መቋረጥ ምክንያት የተሰበረ ድልድይ ጥገና እየተደረገለት ስለሆነ ነው” – የባሌ ዞን መንገዶች ቢሮ
አዲስ አበባ፡- የባሌ ሮቤ-ጋሰራ- ኒር ወረዳዎችን የሚያገናኘው ዋና መንገድ በመቋረጡ ለችግር ተዳርገናል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ። የባሌ ዞን መንገዶች ቢሮ በበኩሉ ለመንገዱ መቋረጥ ምክንያት የሆነው የተሰበረው የብረት ድልድይ ጥገና እየተደረገለት ይገኛል ብሏል፡፡
የሮቤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ባይሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የባሌ ሮቤ-ጋሰራ-ጊኒር መንገድ ግንባታ የተጓተተና ሕዝቡን ለእንግልት የዳረገ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሰሞኑን ድልድዩ በመሰበሩ ምክንያት መንገዱ ሙሉ ለሙሉ በመዘጋቱ ኅብረተሰቡ ችግር ውስጥ ይገኛል።
በደምበል ከተማ የሚገኘው ድልድዩ ከባሌ ዞን ዋና ከተማ ባሌ ሮቤ ተነስቶ የምስራቅ ባሌ ወረዳዎችን የሚያገናኝ ወሳኝ መተላለፊያ መሆኑን ተናግረዋል።
ድልድዩ በጣሊያን መንግሥት በ1934 ዓ.ም እንደተሠራ ይታወቃል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ለረዥም ዓመታት ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመላለሱ በርካታ ተሽከርካሪዎችን አስተናግዷል ብለዋል።
ነገር ግን ጥራት ያለው እድሳት ያልተደረገለት ድልድይ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ሲበላሽ መጠነኛ ጥገና ሲደረግለት ቆይቷል፡፡ በቅርቡም ከባድ የጭነት ተሳቢ ተሽከርካሪ በድልድዩ ላይ ሲያልፍ ተሰብሮ ከሮቤ ወደ ጋሰራና ጊኒር የሚወስደው መንገድ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት አቁሟል ሲሉ ችግሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜም ምንም አይነት መኪና መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ኅብረተሰቡ ወንዙን ለመሻገር ለዋናተኞች 50 ብር እየከፈለ እየተሻገረ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ተለዋጭ መንገድ ባለመኖሩም ነጋዴዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ወደ ሮቤ ከተማ ሪፈር የተባሉ ታካሚዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል ሲሉ ያስረዳሉ።
የሚመለከተው አካል ድልድዩ በአስቸኳይ ጠግኖ መንገዱ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ ይኖርበታል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የድልድዩ መልሶ መገንባት ኅብረተሰቡ ካለበት ጫና እንዲላቀቅ ያደርገዋል ብለዋል።
በመንገዱ መቋረጥም ነጋዴዎች ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ተዳርገዋል የሚሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ዓለሙ ገዛኸኝ ናቸው ፡፡
መንገዱ ከተቋረጠ ሳምንት ሆኖታል ያሉት አቶ ዓለሙ፤ አሁን ላይ ለንግድ ከጋሰራ ወደ ሮቤ ከተማ ለመጓዝ በጎሮ ወረዳ በኩል ጥምጥም በሆነ መንገድ እንድንሄድ ተገደናል። ይህም ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ዳርጎናል ብለዋል፡፡
መንገዱ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ድልድዩ በፍጥነት መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፤ የበርካታ ነጋዴዎችን ሥራ እያስተጓጎለ የሚገኘውን ችግር በአፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ይጠይቃሉ።
የባሌ ዞን መንገዶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዴከማ ቦኮሉ በበኩላቸው፤ ከረጅም ዓመታት በፊት የተሠራው የብረት ድልድይ ከአቅም በላይ የሆነ ጭነት በማስተናገዱ መሰበሩን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ቦታው ላይ በመገኘት የተሰበረውን ድልድይ በመጠገን ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ዴከማ፤ በቅርብ ጊዜም መንገዱ በጊዜያዊነት ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡ በዘላቂነት ያለውን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ኅብረተሰቡ አማራጭ መንገድ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጨምረው አብራርተዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም