የጎረቤቶች ሠላምና አብሮ ማደግን ዓላማ ያነገበው ፖሊሲ

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ጋር በቋንቋን፣ በባሕል፣ ታሪክና በተፈጥሮ ሀብት የጠነከረ ትስሰር አላት። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ፤ ሶማሊያ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ጤናማ እንዳልነበረ የሚታወቅ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል አንድ ጊዜ መለስተኛ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ ጦርነት እንደተካሄደ ይታወቃል፡፡ በሶማሊያ በኩል የታላቋ ሶማሊያ መፈክር ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ሲያቃቅራት የነበረ ጉዳይ ነው ይላል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሶማሊያ ሁልጊዜም ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆኑ ወገኖች ጋር ስትሰለፍና የኢትዮጵያን ሠላም ስታውክ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከሶማሊያም ሆነ ከሌሎች ለሚመነጭ ስጋት የተጋለጠች ሆና ኖራለች። በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች ተቀያይረዋል የሚለው ሰነዱ፤ የታላቋ ሶማሊያ ርዕዮተ-ዓለም ከስሯል። ሶማሊያ ከአስር ዓመት በላይ መንግሥት አልባ ሆናለች፡፡ ይሁን እንጂ የሶማሊያ መዳከም የፈጠረው ስጋት መኖሩን ያብራራል፡፡

በተፈጠረው ስጋት ምክንያት በሶማሊያ ውስጥ አክራሪነት እየተጠናከረ መጥቷል ያለው ሰነዱ፤ ለአክራሪዎችና ሽብርተኞች በመነኻሪያነት ልታገለግል የምትችልበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የተለያዩ የፀረ-ሠላም ኃይሎች ሶማሊያን እንደመነሻና መመላለሻ ማዕከል እየተጠቀሙ የኢትዮጵያን ሠላም ለማወክ የሚጣጣሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በሶማሊያ መበታተንና ቀውስ በሀገራችን ሠላም ላይ ቀጥተኛ አደጋ ሆኖ መገኘቱን ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ሶማሊያ ሠላሟ የተረጋገጠ፣ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጤናማ የሆነ ትብብር እንዲኖርና የሕግ ልዕልና እንዲረጋገጥ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የፖለቲካ ትስስር እንዲኖር ትሠራለች ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ፤ ይሁን እንጂ ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው፤ የሶማሊያ ሠላምና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ጥረት ብቻ እውን ሊሆን አይችልም። በሶማሊያ ሠላምና ዴሞክራሲ ቢሰፍን በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የራሷን አስተዋፅዖ ለማበርከት ባላት አቅም የምትሠራ ቢሆንም በሶማሊያ ሠላም የማስፈን ኃላፊነት በዋነኛነት የሶማሊያ ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎች መሆኑን ይገልጻል፡፡

በሶማሊያ ሠላምና ዴሞክራሲ እስካልሰፈነ ድረስ ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጣችን አይቀርም የሚለው ስትራቴጂክ ፖሊሲው፤ ከሶማሊያ የሚመነጩ የአክራሪዎችን የሽብርተኞችንና የተለያዩ የፀረ ሠላም ኃይሎችን ጥቃት ለመከላከልና ለማምከን የሚያስችል ብቃት መፍጠር ይገባል። ከዚህ አኳያ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ሆኖ መጠበቅ እንደሚገባ ሰነዱ ይጠቅሳል።

ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የሚያስገኝላትን ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩ ይታወቃል፡፡ ከሰሞኑን የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋና መሠረቱና ማጠንጠኛው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያሉ ግንኙነቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ የውጭ ፖሊሲ ትኩረትም ይሄው ነው፡፡ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያሉ ትስስሮችን ማጠናከር ዋና ዓላማው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ግጭት ከመፈጠሩ በፊት የመከላከል ሥራን በትኩረት ትሠራለች ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትሰጣለች ሲባል በዋናነት ግንኙነትን ማጠናከር መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሁሉንም ልዩነት በሠላማዊ መንገድ መፍታት ነው፤ የውጭ ፖሊሲው የሚደግፈው ይህንኑ ነው፡፡ ግጭት ዘላቂ ሠላምን አያመጣም፤ ግጭት በመጨረሻ የሚፈታው በውይይት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መርሕ ይሄው ነው፤ ከሶማሊያ ጋር በመልካምና መልካም ባልሆነ መንገድ ሊገለጹ የሚችሉ ብዙ ታሪካዊ ግንኙነቶች አሉ፡፡ ግጭቶችም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በደርግ በጦርነት የተገለጹ ናቸው ይላሉ።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ሶማሊያ እ.ኤአ. ከ1991 እስከ 2005 መንግሥት ያለው ሀገር ሆኖ ሊቆም አልቻለም። በመጀመሪያ በኢጋድ አማካኝነት በመቀጠል በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም)ና የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የሶማሊያን ሠላም ለማረጋገጥ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ እንዲሁም ከጥር እኤአ 2025 ጀምሮ ደግሞ በአዲስ መልክ የሶማሊያን ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል። በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የነበራት አስተዋፅዖም በመስዋዕትነት ብቻም ሳይሆን በሀሳብም ጭምር የሚገለጽ ነው፡፡ ሶማሊያ መተራመስና ሠላም አለመሆን ለኢትዮጵያም የሚተርፍ በመሆኑ ኢትዮጵያ ብዙ ሚና ነበራት፡፡ ሶማሊያን ያጋጠማት ውል ያለው መንግሥት ማጣት ብቻ ሳይሆን በፀረ ሽብር ኃይል መናጥ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ኃይሉ ደግሞ ከአካባቢያዊ ባለፈ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው ነው፤ ይህን ለመዋጋት ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት መታገሏን ያወሳሉ፡፡

ጎረቤቶቿ ሠላም እንዲሆኑ በተግባር አሳይታለች። ኢትዮጵያ የመጨረሻ መዳረሻዋ ሠላም በመሆኑ ለሠላም የተዘጉ በሮችን አንኳኩታ ታስከፍታለች ነው ያሉት፡፡

የሱዳን ሕዝብ በከባድ ግጭት ውስጥ ያለ ሕዝብ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ የሱዳን ሕዝብ ሠላም እንዲያገኝ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ኢትዮጵያ ትደግፋች። ኢትዮጵያ ከራሷ ልምድ ተነስታ ምክሯን ትለግሳለች። ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ በየደረጃው የሱዳንን ሠላም መሆን እንደዋና ተግባር ይዘው እየሠሩ መሆኑንም አንስተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ለሠላምና ለዘላቂ ትብብር ሁሌም በሯ ክፍት ቢሆንም በጎረቤት ሀገራት በኩል የሚመጡ ስጋቶችንም ለማስቀረት በትኩረት እየሠራች ነው። ለቀጠናው ዘላቂ ሠላም እና የሁሉም የጎረቤት ቀና ትብብርና አብሮ እጅ ለእጅ ተያይዞ የመልማት ፍላጎት መዳበር ይኖርበታል፡፡

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You