
ምቹ የእግረኛ መንገዶችን፣ የሞተር አልባ (ብስክሌት) መንገዶችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የመንገድ ዳርቻ ማረፊያ መቀመጫዎችን፣ የሕዝብ መናፈሻዎችን፣ የዘመናዊ ከተማ ደረጃን የሚመጥኑ መብራቶችና ፋውንቴኖችን ባጠረ ጊዜ ለመገንባት የሚያስችል ሥራ በሐዋሳ ከተማ እየተከናወነ ይገኛል።
የኮሪደር ልማት ሥራው ቀን ከሌሊት እየተሠራ ነው፤ በዚህም ለበርካቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በሥራ ላይ ያገኘነው ወጣት ፍቃዱ ሹቴ የሴራሚክና የቴራዞ ባለሙያ ነው። በሙያው የሰባት ዓመታት ልምድ አለው። ያካበተው ልምድ በሐዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ተቀጥሮ እንዲሠራ ዕድል ሰጥቶታል።
ወጣት ፍቃዱ የተወለደው በሲዳማ ክልል ይርጋለም አካባቢ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በኮንስትራክሽን ፐሮጀክቶች ውስጥ በረዳትነት ሲሠራ መቆየቱን አይዘነጋውም።
የኮሪደር ሥራው ላይ ከመግባቱ በፊት ከኮንትራክተሮች ጋር በካሬ 75 ብር እየተከፈለው ይሠራ እንደነበር አስታውሷል። አሁን ግን በኮሪደር ሥራው በካሬ 120 እና 150 ብር ይከፈለዋል። በዚህም ራሱን ከመቻል አልፎ እናትና አባቱን በመርዳት ማስደሰት እንደቻለ ተናግሯል።
የሐዋሳ የኮሪደር ሥራ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ የቱሪስት ቁጥርን ይጨምራል። ከዚህም በላይ ለትውልድ ውብ ከተማን ማስተላለፍ ያስችላል ያለው ወጣት ፍቃዱ፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የሥራ ዕድል የፈጠረ ብቻ ሳይሆን የሥራ ባሕልና አስተሳሰብን የቀየረ መሆኑን ይገልጻል።
የሀዋሳ ከተማም ከአዲስ አበባ ተሞክሮ በመውሰድ አዲስ የሥራ ባሕልን በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ለማስረጽ የኮሪደር ልማት ተጀምሯል ያለው ወጣት ፍቃዱ፤ በዚህም ተጨማሪ ሰዓት በመሥራት የወር ገቢውን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።
ሐዋሳን የሚመጥን የልማት ሥራ ላይ መሳተፋቸው በውስጣቸው ልዩ ስሜት እንዲፈጠር ማድረጉን የገለጸው ወጣት ፍቃዱ፤ በልማቱ በሚሠራው የሴራሚክና የቴራዞ ሥራ ላይ ነዋሪዎች ሲመላለሱና ሥራውን ሲያደንቁ ሲሰማ ደስታው እጥፍ ድርብ እንደሚሆን ተናግሯል።
የሲቪል መሐንዲስ ባለሙያ ወጣት ጌታቸው አታራ በበኩሉ፤ የኮሪደር ልማቱ ላይ የተሳተፈው በመደበኛነት ከሚሠራው ሥራ እረፍት በመውጣት መሆኑን ገልጾ፤ የእረፍት ጊዜው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከኮሪደር ልማቱ በርካታ ልምዶችንና ክህሎቶችን እንደሚያገኝ ተናግሯል። ይህም ወደፊት ሙያውን እንደሚያሳድግ አስረድቷል።
ጊዜውን በመዝናናትና ቤት ውስጥ ቁጭ ከማለት ወደኮሪደር ልማት ሥራው መግባቱን ገልጾ፤ በዚህም ተጨማሪ ሰዓት በመሥራት የተሻለ ገቢ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል። ጠንክሮ ከተሠራ ከራስ አልፎ የቤተሰብንና የአካባቢን ኑሮ ለመለወጥ ወደሚያበቃ ደረጃ እንደሚሸጋገር ተስፋው መሆኑን አመላክቷል።
እያንዳንዱ የሥራ አይነት ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይባል ትኩረት አግኝቶ ከተሠራ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ዛሬ ትንሽ ነው የሚባል አንድ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ካገኘ ነገ የሚሠራውን ሰው ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል ብሏል።
የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ገጽታ ከሚያበረክተው ጉልህ ሚና አንፃር ያለደመወዝ ቢሠራ እንኳን ቅር እንደማይሰኝ የገለጸው ወጣት ጌታቸው፤ ከሙያው አንፃር ሲመለከተው ለኮሪደር ልማቱ የተሰጠው ትኩረትና እየቀረቡ ያሉት ግብዓቶች ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን እንዲሁም ሥራው በብቁ ባለሙያዎች እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገረው።
የምሕንድስና ሳይንስን መሠረት አድርጎ እየተገነባ በመሆኑ በጥራት የሚሠራ የኮሪደር ልማት መሆኑን በልበ ሙሉነት እንደሚናገር ገልጿል።
በሀዋሳ የኮሪደር ልማት በምሽት ሥራውን መሥራታቸው ፕሮጀክቱን በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ እንደሚያደርግ እና ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉን የተናገረው ደግሞ የሴራሚክ ባለሙያው ወጣት ኢሳያስ የቴ ነው። በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጿል።
በኮሪደር ልማቱ ተግባራዊ የሆነው የሥራ ባሕል በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋለውን የጊዜ መዘግየት ችግር እንደሚቀርፍ ተናግሯል። በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎች ቀንና ሌሊት በመሥራት የሥራ ባሕል ለውጥ ማድረግና ለሀገራቸው ዕድገት መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፏል። ትውልዱ ያገኘውን ዘመናዊ ትምህርትና ክህሎት በመጠቀም የሥራ ባሕሉን ማጠናከር እንዳለበትም ተናግሯል።
የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻ በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ሙሉ በሙሉ የሥራ ባሕልን የለወጠ፤ ጀምሮ መጨረስን ያስተማረ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ወቅቱ የከተሞች ትንሳኤ እንደመሆኑ ቀድሞ በቂ ትኩረት ያልተሰጠው የከተሞች ዕድገት አሁን ላይ በመሻሻሉ ዕድገታቸው እየጎለበተ መሆኑን አንስተዋል።
የሐዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ ቀን ከሌሊት እየተሠራ መሆኑንና ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻነትዋ የበለጠ ሳቢና ማራኪ ይሆናል ብለዋል።
የሐዋሳ ከተማ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ምሕረቱ ገብሬ (ኢ/ር)፤ በበኩላቸው በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት በሁለት ዘርፎች ተከፍሎ እየተካሄደ እንደሆነና ይህም በከተማ ውስጥና በማስፋፊያ ቦታዎች ላይ የሚከናወንን መሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ብዙ ልምዶች የተገኙበት መሆኑን ያነሱት ኢንጅነሩ፤ የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ ፋውንቴን፣ የማረፊያ ቦታዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎችን አሟልቶ የሚይዝ እንደሆነም ያመላክታሉ።
በሐምሌ ወር የተጀመረው የሐዋሳ ከተማ የአንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ መጠናቀቁን አንስተው፤ ሥራው በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
በማስፋፊያ ቦታዎች ለሚካሄዱት የኮሪደር ልማት ሥራዎች አንድ ሺህ 145 ተነሺዎች መለየታቸውንና ለተነሺዎች ተገቢውን ካሣ ከፍሎ የልማት ሥራውን ለማስጀመርም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው የገለጹት።
ሐዋሳ በፕላን የተሠራች ከተማ በመሆኑዋ አሁን የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ይበልጥ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጋታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኢንጂነር ምሕረቱ ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም