በፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደማቅ ታሪክ መፃፋቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ቅዳሜ ምሽት አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒኩ የአይነስውራን ጭላንጭል ምድበ (T 13) 1500 ሜትር ውድድር 4:22:39 በማጠናቀቅ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል። በትናንትናው እለት ደግሞ አትሌት ያየሽ ጌቴ በፓራሊምፒኩ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በዓለም ክብረወሰን ጭምር ታጅባ አስመዝግባለች።
አትሌት ያየሽ ጌቴ በፓራሊምፒኩ ውድድር ከአሯሯጯ ክንዱ ሲሳይ ጋር በመሆን በ1500 ሜትር በዐይነ ሥውራን ሙሉ በሙሉ (T11) ውድድር አሸናፊ በመሆን ደማቅ ታሪክ ፅፋለች። አትሌቷ በውድድሩ ወርቅ ከማጥለቅ በተጨማሪ ቀደም ሲል በራሷ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ማሻሻሏ ተጨማሪ ታሪክ ሆኗል። ይህም በፓሪስ ፓራሊምፒክ ከትዕግስት ገዛኸኝ በመቀጠል ለኢትዮጵያ ሁለተኛው የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘች ሆና በታሪክ ማኅደር እንድትቀመጥ አድርጓታል።
አትሌቷ ትናንት የመጀመሪያ የፓራሊምፒክ ድሏን ስታሳካ ርቀቱን በ 4 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ በራሷ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በአራት ሴኮንድ ማሻሻል የቻለች ሲሆን፣ በ2024 ጃፓን ኮቤ የዓለም የፓራሊምፒክ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 ሜትር አይነስውራን ሙሉ ለሙሉ ምድብ ውድድሯን አድርጋ 4:31:77 በመሮጥ የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ እንቅስቃሴ ውስጥ በአስደናቂ ውጤት እየታጀቡ ከሚገኙ አትሌቶች መካከል አንዷ ያየሽ ጌቴ ናት። አትሌት ያየሽ ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ የተወለደችው ሲሆን እድሜዋ 27 ነው። በትውልድ መንደሯ በትምህርት ቤት ነበር ሩጫን የጀመረችው። ደብረታቦር ከተማ የፓራሊምፒክ አትሌቲክስ ፕሮጀክት ስር ታቅፋ ሥልጠናዎች መውሰድ ከጀመረችም ዓመታት ተቆጥረዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ሻምፒዮና ላይ ውጤታማ መሆኗን ተከትሎ በብሔራዊ ቡድን የመታቀፍ ዕድል ያገኘችው ያየሽ፣ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሯን ያደረገችው በ2020 ቱኒዝ ላይ ነበር። በዚህም በ200 ሜትር እና 400 ሜትር ጥምር የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። በ400 ሜትር የቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ሚኒማ በሟሟላት በቡድኑ ውስጥ ተካታ ሥልጠናውን እየወሰደች የነበረ ቢሆንም ዓለም አቀፉ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ለሴቶች በሰጠው አንድ የተሳትፎ ኮታ አትሌት ያየሽ ቅዳሜ እለት ወርቅ ካጠለቀችው ከአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ጋር ተወዳድራ በትዕግስት በመበለጧ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የመሳተፍ ዕድሏ ሳይሳካላት ቀርተዋል። በፓራሊምፒክ የመሳተፍ ሕልሟን እውን ለማድረግ ያለፉትን ሦስት ዓመታት አሯሯጯ ከሆነው ክንዱ ሲሳይ ጋር በመሆን ወደ መካከለኛ ርቀት ፊልዷን በመቀየር በርትታ ሠርታለች።
በዚህ ዓመት ዱባይ ላይ በዓይነስውራን ሙሉ ለሙሉ ምድብ T11 1500 ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን ለዓለም ሻምፒዮና የሚያሳትፋትንም ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። በ2024 ጃፓን ኮቤ የዓለም የፓራሊምፒክ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 ሜትር ዓይነስውራን ሙሉ ለሙሉ ምድብ ውድድሯን አድርጋ 4:31:77 በመሮጥ የርቀቱን የዓለም ሪከርድ በመስበር ጭምር ወርቅ አጥልቃለች። ይህም የፓሪስን ትኬት አስቆርጧታል።
አትሌት ያየሽ ጌቴ በመጀመሪያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎዋ የማጣሪያ ውድድሯን በድንቅ ብቃት ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ ነበር የፈፀመችው። ትናንት ረፋድ የፍፃሜ ውድድራን ለአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ካገኙት አትሌቶች በተለይም የቶኪዮ 2020 የርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሜክሲኳዊቷ ሮድሪጌዝ ሳቬድራ እና ቶኪዮ ላይ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም የኮቤ ዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ደቡብ አፍሪካዊቷ ኮኢትዚ ሎዛኒን ጭምር አሸንፋ የዓለም ክብረወሰኑንም የግሏ አድርጋ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ለመሥራት በቅታለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም