ትውልድ ግንባታ – ሀገር የምትድንበት መልሕቅ!

“ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ አበው፤ ቀጥታ ወደ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት ሀሳቤን በምሳሌ ለማስረዳት ወደድሁኝ። እንደሚታወቀው ያለንበት የክረምት ወራት ነው። በዚህ በክረምት ወራት አንድ ጠንካራ ገበሬ በወቅቱ ዘርቶ፣ አርሞ፣ ኮትኩቶ ሰብሉን ያሳድጋል።

ሰብሉ ሲያፈራ ደግሞ ወፍ እንዳይበላው ጠዋት፣ ማታ ይጠብቃል። በወቅቱ አጭዶ ወቅቶ ወደ ጎተራው ይከታል። በዚህም የዓመት ጉርሱንና ቀለቡን ያገኛል። ቤተሰቡን ዓመቱን ሙሉ አጥግቦ አብልቶ፣ አጠጥቶ ያሳድራል። በቤቱም ዓመቱን ሙሉ ተድላና ጥጋብ ይሆናል። እንግዳ ወደ ቤቱ ገብቶ በልቶ ጠጥቶ መርቆ ይወጣል።

በአንጻሩ በወቅቱ ያልዘራ፣ ሰብሉን ያልኮተኮተ፣ ያላረመ፣ አጭዶ ወቅቶ ወደ ጎተራው ያልከተተ ሰነፍ ገበሬ ደግሞ ማሳው ጠፍ፤ ምርቱም መናኛ መሆኑ አይቀሬ ነው። “አንድ ሰኔ የነቀለውን አስር ሰኔ አይተክለውም” እንደሚባለው በወቅቱ ተግቶ ያልሠራ ሰነፍ ገበሬ ቤቱ ይራቆታል፤ ልጆቹም ይራባሉ።

ዓመት ከዓመት ከዘር ብድር አይወጣም። ችግሩ እየበረታ ሲሄድ ትዳሩም፤ ቤቱም ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይፈርሳል። በመጨረሻም ልጆቹን ለጎበዝ ገበሬ በረኝነት አልያም በገበሬነት አሳልፎ ይሰጣል። በሰው ዘንድም ሞገስና ክብርን ያጣል።

ታዲያ አሁን ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን የገጠመን ከላይ በምሳሌነት ያነሳሁት የሰነፉ ገበሬ ዕጣ ፈንታ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ ያልዘራነውን፣ ያልኮተኮትነውን፣ ያልተንከባከብነውን አዝመራ ለማጨድ አንጋጠን የምንጠብቅ ሞኞች ወይም ግብዞች ነን። ያልደከምንበትን አዝመራ ለመክተት የምንውተረተር ፍሬ ቢስ ነን።

እስኪ እያንዳንዱ ወላጅ ዞር ብሎ ጓዳውን ይፈትሽ። ልጁን በምን አይነት ሥነ-ምግባር ነው እየኮተኮተና እየቀረጸ ያሳደገው ወይም እያሳደገ ያለው? ልጆቻችንን ሃይማኖታችን በሚያዘው፣ የሀገር ባሕልና ወግ በሚፈቅደው ፈር ሳይለቁ ቆንጥጠን ነው ያሳደግነው ወይም እያሳደግን ያለነው? ስንቱ ነው ልጁ ፈርሐ እግዚያብሔር (አላህ) አድሮበት እንዲያድግ የሚታትር? እስኪ ሁሉም ወላጅ ዞር ብሎ እራሱን ይመልከት።

መሬት ላይ ያለው ሐቅ ግን የሚያሳየው ወላጅ ልጁን ፊደል በማስቆጠር ፈንታ ዘር ቆጠራ እያስተማረ፣ ሠርቶ በላብ ማግኘትን ሳይሆን ሰርቆ በአቋራጭ መክበርን እያስጠና፣ ጎረቤቴን በምን ልደገፈው ሳይሆን በምን ልቅበረው እያለ ሴራ ማቀነባበርን እያቃመሰ፣ በጭካኔ ወንድም ከወንድም ጋር መተራረድን እያሳየ ነው።

ከሰው ይልቅ በአፍቅሮተ ነዋይና ሥልጣን ታውሮ ለጥቅም፣ ለሥልጣን ሰውን መበደልና ማስገደልን እያለማመደ …. ወዘተ ጭካኔን፣ ዘረኝነትን፣ ሌብነትን፣ ዝሙትን፣ ስካርን፣ ሥልጣን መውደድን ልጆች በልጅነት አዕምሯቸው ቀስመው እንዲያድጉ እያደረገ ያለው በዋናነት ወላጅ ወይም ቤተሰብ ነው። ያው ሉላዊ፣ ማኅበረሰባዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ።

በዚህም አሁን ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን የዘራነውን ሴራ አዝመራ እያጨድን፣ የከመርነውን የክፋት ክምር እየወቃን፣ በጎተራችን የከተትነውን የበደል አዝመራ እየተመገብን እንገኛለን። “በእንቁላሌ በቀጣሽኝ” ሆኖ ነገሩ፤ ልጆች በቅጡ ተኮትኩተው፣ ሥርዓት ይዘው፣ ፈርሐ እግዚያብሔር እንዲያድርባቸው፣ ባሕል ወጋቸውን እንዲጠብቁ ተደርጎ በወጉ ተቀርጸው ባለማደጋቸው ሁሉም የገፈቱ ቀማሽ ሆኗል።

ዛሬ ላይ ሕዝቡ ከገዛ አብራኩ በውጡ ልጆቹ እየተቀጣ ይገኛል። ከገዛ አብራኩ የወጡ ልጆች መንገድ እየዘጉ ቋንጃ ይቆርጣሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይገድላሉ፣ ያፈናቅላሉ። ሰው አግተው በሚሊዮን ገንዘብ ይቀበላሉ። ሀገር በልጆቿ የጦርነት አውድማ ሁና፤ ሕዝቡ ሠላም ወጥቶ ሠላም መግባት ናፍቆታል።

ልጆቿ አንተ ትብስ አንቺ ተባብሎ ተነፋፍቆ መኖር ተስኗቸው፤ የጦርነት አዙሪት በምድሪቱ ሰፍኖ ምድር አኬል ዳማ ሆናለች። አሁን በገሃድ እያየናቸው ያሉ ሕጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ደፍሮ የሚገሉ አረመኔዎች፣ ሙሰኞች፣ የሥልጣን ጥመኞች፣ ዘራፊዎች፣ ነፍሰ በላዎች … ወዘተ ሁሉም የወላጅና የማኅበረሰቡ ውጤቶች ናቸው።

ሆኖም የጥላቻ መርዝ እየጋትን፣ በጥላቻ መንፈስ እያጠመቅን፣ ያሳደግናቸው ልጆች ዛሬ ላይ ይህን ቢያደርጉ ምን ይደንቃል። ምንስ ይፈረድባቸዋል። ተምሮና ተመራምሮ ሀገር እንዲጠቅም ሳይሆን፤ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ ሴራ በመጎንጎን ተኮትኩቶ ካደገ ትውልድ ምንስ ይጠበቃል።

ስለዚህ አሁን ሀገሪቱ ለገባችበት ውጥንቅጥ አንዱና ዋነኛው መንስኤ ነው ብዬ የማስበው የትውልድ ስብራት ነው። ትውልዱ በአግባቡ ተኮትኩቶ ባለማደጉ፤ ታሪኩን፣ ባሕሉን፣ እንዳያውቅ በመደረጉ ነው።

በተለይ ወላጅ ይህንን ተገንዝቦ ልጆቹን በወጉ ኮትኩቶ፣ በመልካም ሥነ-ምግባር ቀርጾ፣ ፈርሐ እግዚአብሔር እንዲያድርባቸው አድርጎ፣ ባሕል ወጋቸውን ጠብቀው እንዲያድጉ በማድረግ፤ ነገ ላይ የተሻለ ሀገር ተረካቢ ዜጋ በማፍራት የአንበሳውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

ፈር የወጡ ልጆቹንም መክሮ፣ ዘክሮ ወደ ትክክለኛው የሕይወት ጎዳናና የሠላም መንገድ እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቅበታል። “በእንቁላሌ በቀጣሽኝ” እንደተባለው ዛሬ ላይ ልጆቹን መክሮ፣ ዘክሮ፣ ኮትኩቶ ያላሳደገ ወላጅ ነገ ላይ የመጀመሪያ የገፈቱ ቀማሽ እራሱ ወላጅ ነው።

ሀገር ደግሞ የቤተሰብ ድምር ውጤት ናት። መልካም ቤተሰብ እየሰፋ ሲመጣ፤ ሀገር ሠላም ትሆናለች። በአንጻሩ ደግሞ ቤተሰብ ልጆቹን በአግባቡ ኮትኩቶ ካላሳደገ፤ ልክ አሁን እንዳለንበት ዘመን ሀገር በልጆቿ ትታመሳለች፣ ትታወካለች። በመሆኑም ቤተሰብ በነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ግንባታ ላይ ድርሻው አይተኬ መሆኑን ተገንዝቦ፤ ነገ የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ሊተጋ ይገባል።

በትውልድ ላይ ለተፈጠረው ስብራት ብቸኛ መድኃኒት በትውልድ ግንባታ ላይ መሥራት ነው። ትውልድ ግንባታ ሀገሪቱ ከገባችበት ውጥንቅጥ ወይም ችግር በቋሚነት የምትፈወስበት ወይም የምትወጣበት መልሕቅ ነው። ዛሬ ላይ ትውልዱ በመልካም ሥነ-ምግባር ተኮትኩቶ ካደገ ነገ የተሻለች ሀገር እንደምትኖረን ምንም ጥርጥር የለውም።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት (የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች፣ ግብረሠናይ ድርጅቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች… ወዘተ) በትውልድ ግንባታ ላይ መረባረብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በመልካም ሥነ-ምግባር ታንፀው፣ አድገው የበለፀገች ሀገር እውን በማድረግ ሂደት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ደግሞ ሁሉም በፊናው ያለበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።

በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናትና ወጣቶችን በመልካም ሥነ-ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ ለሀገራቸው ብልፅግና፣ ሠላም፣ እድገት … የበኩላቸውን አወንታዊ ሚና እንዲወጡ ደግሞ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ሙሉ ኃላፊነት አለበት። ለነገው ትውልድ ከብክለት የፀዳ አካባቢና አየር ንብረት፣ የሚጫወቱበት ንጹሕና ነፋሻማ አካባቢ በመፍጠር እንዲሁም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የተደራጁ የልጆች ማቆያዎችን በማስፋፋት በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጸ በአካልና በሥነ-ልቦና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም በያገባኛል ስሜት መወጣት ያለበትን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል።

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነ ያለው “የቀዳማይ ልጅነት እድገት ልማት ፕሮግራም” በሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሊሰፋ የሚገባ ምርጥ ተሞክሮ ነው። ፕሮግራሙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እራሳቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚያስተባብሩትና የሚመሩት ሲሆን፤ ልጆች ሰፊና ምቹ የመጫወቻ ቦታ አግኝተዋል።

ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በተደራጁ የልጆች ማቆያዎች ውለው እንዲሁም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው እናቶችና ሕጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ አግኝተው፤ ልጆች ደኅንነታቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ፣ በአካልና በአዕምሮ ዳብረው፣ በመልካም ሥነ-ምግባር ተቀርጸው ነገ ላይ የተሻለ ሀገር ተረካቢ ዜጋ የሚሆኑበት ዓውድ በመዲናዋ ተፈጥሯል። ይህንን ፕሮግራም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የማስፋፋት ሥራ ሊሠራ ይገባል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You