የታላቁ ስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ አቻ የሆነው የፓራሊምፒክ ውድድር በኢትዮጵያ ትኩረት ካልተሰጣቸው የስፖርት ዘርፎች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ የፓራ አትሌቶች በውጤት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች እያስጠሩ ይገኛሉ።
ከነዚህ ስኬታማ የፓራ አትሌቶች መካከል ትዕግስት ገዛኸኝ ቀዳሚ ናት። ትዕግስት እድሜዋ ገና 24 ነው። የትውልድ ሥፍራዋ ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎላላ እና ጠራ ወረዳ ሲሆን፣ የስፖርቱን ሕይወት የጀመረችው ከልጅነቷ ቢሆንም ከፓራ አትሌቲክስ ጋር የተገናኘችው በቅርቡ ነው። ከዛ በፊት በጉዳት አልባው አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድል የነበራት ቢሆንም ከጊዜ በኋላ የዓይን እይታ መጠኗ ከመቀነሱ ጋር በተየያያዘ ወደ ፓራሊምፒክ ስፖርት ብቅ ብላለች።
በደብረብርሃን ከተማ ሥልጠናዋን በመከታተል ዞኗን ወክላ በክልል እና በሀገር አቀፍ የፓራ አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የተሻለ ሰዓት በማስመዝገቧ ሀገሯን በታላላቅ መድረኮች ለመወከል በቅታለች። የመጀመሪያ ውድድሯን ቱኒዝ ላይ አድርጋ ውጤታማ በመሆኗ በቶኪዮ ፓራሊምፒክ 1500 ሜትር ውድድር ሚኒማ ማሟላት ቻለች። በመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ በቶኪዮ 2020 የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በዓይነስውራን ጭላንጭል ምድበ (T 13) በ 1500 ሜትር ሩጫ ውድድር ላይ 4:23:24 በመግባት በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ በማሳካት ፈር ቀዳጅ መሆን ቻለች።
በሰኔ 2024 ኮቤ ጃፓን የዓለም ቻምፒዮና በ1500 ሜትር ዓይነስውራን ጭላንጭል ምድብ (T13) 4:18:90 በመሮጥ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ከማጥለቋ ባሻገር የፓሪስ ፓራሊምፒክ የቀጥታ ተሳትፎ እድልን ማሳካት ችላለች ። ትዕግስት በግማሽ ማራቶን 1;06:20፣ በ10 ኪሎ ሜትር ደግሞ 31;08 የሆነ የግሏ ፈጣን ሰዓት አላት።
በፓራ ውድድሮች እያስመዘገበች እንደም ትገኘው ውጤትና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ባስጠራችበት ልክ ተገቢው ትኩረት ያልተሰጣት አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ አሁን ላይ በፌዴራል ፖሊስ (ኦሜድላ) ክለብ ከጉዳት አልባው የአትሌቲክስ ቡድን ጋር ታቅፋ እየሠራች ትገኛለች። አሠልጣኟም በመካከለኛና ረጅም ርቀት በርካታ ከዋክብቶችን እያፈራ የሚገኘው ህሉፍ ይህደጎ ነው።
የረጅም ርቀት ንግሥቷ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አድናቂ የሆነችው ትግስት ገዛኸኝ እንደ ጥሩነሽ ሁሉ በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ሀገሯን ማስጠራት የዘወትር ህልሟ ነው። ባለፈው ቶኪዮ ፓራሊምፒክ ላይ ህልሟን አንድ ብላ ማሳካት ጀምራለች። ባለፈው ቅዳሜ ምሽትም በፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክ በተመሳሳይ ውድድር ሁለተኛ ድሏን በማጣጣም በተከታታይ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ወርቅ በማጥለቅ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ማኖር ችላለች።
በፓሪስ 2024 የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ትዕግስት ገዛኸኝ የወርቅ ሜዳሊያውን በዓይነስውራን ጭላንጭል ምድበ (T 13) 1500 ሜትር ሩጫ 4:22:39 በማጠናቀቅ ነበር ቀዳሚ የሆነችው። እስከ ውድድሩ መጨረሻ ድረስ አስደናቂ ፉክክር በታየበት ምሽት ትዕግስት ከሞሮካዊቷ አትሌት ኤል ኢድሪሲ ፋቲማ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጋ የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዳለች። ይህም በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ የመጀመሪያዋ የፓራ አትሌት ያደርጋታል። ኢትዮጵያም በብቸኛው የትዕግስት ወርቅ ሜዳሊያ በእለቱ በፓራሊምፒኩ የደረጃ ሰንጠረዥ ከዓለም 28ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ብርቱ ፉክክር በታየበት ውድድር ትዕግስትን ተከትላ ሞሮካዊቷ አትሌት ኤል ኢድሪሲ ፋቲማ 4:22:98 ሰዓት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች። አሜሪካዊቷ ኮርሶ ሊዛ 4:23:45 በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያው ባለቤት ሆናለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም