ዕቅድ እና አዲስ ዓመት

አዲስ ዓመትን ለመቀበል ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች አንዱ ዕቅድ ነው። እንዲያውም ለበዓሉ ዶሮ፣ በግ እና ሌሎች ነገሮች ከመታሰባቸው በፊት የሚዘጋጀው ዕቅድ ነው።፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በጣም ቀላል ስለሆነ ነው። ወጪ አይጠይቅም፤ አይተገበርም፤ ዝም ብሎ ብቻ ማቀድ ነው። ቀላል ነው ያልኳችሁ ስለማይተገበር ነው እንጂ እንደ ዕቅድ ከባድ ነገር የለም። አሁን አሁን የተለመደው ግን ዝም ብሎ ማቀድ ብቻ መሆኑ ነው።

አዲስ ዓመት መጣሁ መጣሁ ሲል የሬዲዮ ጣቢያዎችን ልብ ብላችኋል? ለአስተያየትም ይደወል፣ ለዘፈን ምርጫም ይደወል፣ ለጥያቄና መልስም ይደወል… ብቻ ደዋይ አየር ላይ ካለ የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹የአዲስ ዓመት ዕቅድህ ምንድነው?›› የሚል ነው። ጋዜጠኛው በየዓመቱ ያለመታከት ያቅዳል፤ ደዋይም ያለመታከት ይናገራል። የአንዳንዶቹ ይከሽፋል፤ ባቀዱት ልክ የሚተገብሩትም ይኖራሉ።

የእቅድ ነገር ከተነሳ እንኳን በግለሰብ ደረጃ ያለው ትልልቅ ፕሮጀክቶችም በተለይ ቀደም ሲል በነበሩት ዘመናት ከዕቅዱ በእጥፍ የሚዘገዩ ናቸው። ግን እኮ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ይዘገያሉ ማለት የግለሰብ ዕቅድም ይዘገያል ማለት አይደለም።

በነገራችን ላይ የባለፈው ዓመት የመንግሥት ዕቅድ ምን ነበር? ብለን የመጠየቅ ልምድ ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ፤ በየዓመቱ የጳጉሜን ወር በመጣች ቁጥር በመንግሥት ደረጃ ትከበራለች። የጳጉሜን ቀናት የየራሳቸው ስያሜ ተሰጥቷቸው ይከበራሉ። ቀኑ የተሰየመበት ጉዳይ (ለምሳሌ የሰላም ቀን) ትኩረት እንዲደረግበት ይነገራል። ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፤ አዲሱ ዓመት ባለፈው ዓመት የታየ ችግሮች የማይደገሙበት ይሁን… እየተባሉ ይነገራል። ችግሩ ግን በሚቀጥለው ዓመትም ይደገማል።

አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር እናቅዳለን፤ ግን የአብዛኞቹ አይሳካም። ማቀድ ግን የሰው ባህሪ ነውና አይቀርም። እኔ ግን ‹‹ዘንድሮ ምን አቅደኻል?›› ብትሉኝ ባለፈው ዓመት ያቀድኩት ስላለ እሱኑ ነው የምደግመው። በርግጥ የባለፈው ዓመትም በዚያኛው ዓመት ታቅዶ የነበረ ነው። ይሄ ማለት እንግዲህ አልተካሳም ማለት ነው። በርግጥ የእኔ እቅድ ከልጅነቴ ጀምሮ ያለው አንድ ዓይነት አይደለም። በሁለት ከፍዬ ነው የምነግራችሁ።

የመጀመሪያው የልጅነቴ ነው (የተማሪነቴ ማለት ነው)። የተማሪነት ዕቅዴን ሳስበው ያስቀኛል። ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አቅድ ነበር። አዲስ ዓመት ማለት ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል የምንዘዋወርበት ማለት ነው። ታዲያ በየዓመቱ አዲስ ዓመት ሲመጣ የማቅደው ከክፍሉ አንደኛ መውጣት ነበር። ባለፈው ዓመት የበለጠኝ ተማሪ ካለ በሚቀጥለው እንዳይበልጠኝ አቅድ ነበር (እኔ ሳቅድ እሱ አያቅድም አይደል?) እንዲህ እንዲህ እያልኩ አንዳንድ ዓመት ሲሳካ አንዳንዱም ሲከሽፍ 12ኛ ክፍል ጨረስኩ። ከዚህ በኋላ ደግሞ የትምህርት ክፍል (ዲፓርትመንት) እና የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ዕቅድ ይሆናል። ይህን እንኳን አሳክቻለሁ። የምፈልገውንና የሞላሁትን የትምህርት ክፍል አገኘሁ። ልክ የትምህርት ክፍሉን እንዳገኘሁ ቀጥሎ የነበረው እቅድ 4 ነጥብ አምጥቶ የግቢው ሰቃይ መባል ነበር፤ ምን ዋጋ አለው የነጥብ ሳይሆን የካፌው ሰቃይ ሆንኩ።

እንግዲህ የተማሪነት ነገር እያለቀ ሲመጣ ቀጥሎ ያለው እቅድ ሀገር የመረከብ ሆነ። ተማሪ እያለን ‹‹የነገ ሀገር ተረካቢዎች›› እየተባልን አድገናል። ታዲያ ቀኑ ደረሰና የምረቃው ዕለት ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ሀገር ተረክባችኋል›› ሲባል ደነገጥኩ። እንዲያውም ይባስ ብሎ አዲስ አበባ መጥቼ ሥራ ፍለጋ ስባዝን ነው ‹‹እንዲህ ነው እንዴ ሀገር መረከብ!›› ያልኩት። በርግጥ አንዳንድ ሰዎች እንደሚመክሩን ሀገር መረከብ ማለት የግድ ሥልጣን መያዝ አይደለም አሉ፤ ኧረ እንዲያውም ይባስ ብሎ ሀገር ለመረከብ የግድ ሥራ መያዝ አይጠበቅም የሚሉም አሉ። ባይሆን እንኳን ሀገር ለመረከብ የግድ መቀጠር ሳይሆን ሥራ መፍጠርም ሀገር መረከብ ነው ቢሉ ያስማማል። ሥራ መፍጠር እንዲያውም ትልቁ ሀገር መረከብ ነው።

የሆነው ሆኖ ግን ሥራውንም ቢሆን ተቀጠርኩ(ሀገር ተረከብኩ ማለት ነው) ግን ለሀገሬ ምን አበረከትኩ? እሱን በሌላ ቀን እናውራው፤ መነሻችን እቅድ ስለሆነ ማለቴ ነው።

ያስቀኛል ያልኳችሁ ተማሪ እያለሁ የነበረኝን እቅድ ነበር አይደል? የአሁኑ ግን የባሰ ያስቀኛል። ለነገሩ ይሄኛው ዕቅድ ከተማሪነቱ ለየት የሚያደርገው የሚታቀደው ዓመት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየወሩ መሆኑ ነው። ይሄ እቅድ ግን የእኔ ብቻ ይሆን? ማለቴ የዓመቱ እቅድ ቀርቶ የወር እቅድ። ዕቅዴ ብር መቆጠብ ነው። የማሳከው ግን ማባከኑን ነው። ልክ እንደ ተማሪነቱ ዕቅድ በቃ ከዚህ ጊዜ ጀምሬ… እያልኩ እፎክራለሁ፤ ግን ያው ነው። እንዲህ አዲስ ዓመት ሲመጣ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ቆጥቤ የሆነ ነገር ማድረግ (ቤት መሥራትን አይጨምርም)። የቁጠባ ነገር ከተነሳ ግን ሰሞኑን የደሞዝ ሰሞን ነው አይደል? በነገራችን ላይ የዚህ ወር ደሞዝ ትልቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ግደላችሁም ብዙ ምክንያት አለው። አንድ ቢሉ መጭው ድርብርብ በዓላት ያሉበት ነው፤ ሁለት ቢሉ አንድ ወር ሙሉ (ጳጉሜን) በነፃ ታገለግላለህ። ደግነቱ የቤት ኪራይም አይከፈልም። አንዳንዱ ጋዜጠኛ እኮ ‹‹ምን ልስራ!›› ያሰኘዋል። በቅርብ ጊዜ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ‹‹በጳጉሜን ወር ለምን ደሞዝ አይከፈልም፣ ለምን የቤት ኪራይ አይከፈልም›› የሚል ፕሮግራም ሰማሁ። ይህን ፕሮግራም አከራዬ ሰምታው ይሆን ብዬ በጋዜጠኛው እየተናደድኩ ወደቤት ስገባ ደግነቱ ቤት የተከፈተው ቃና ስለነበር እፎይ አልኩ።

የእኔ የአዲስ ዓመት እቅድ መቆጠብና ቆጥቦ የሆነ ነገር መግዛት ነው ብያችኋለሁ። ይህ እንግዲህ ዕቅድ እንደየሰው ይለያያል ማለት ነው። ለምሳሌ ማግባት የሚፈልግ ማግባት ይሆናል፤ ቤት የሚሰራ መሥራት፤ መኪናም ከሆነ እንደዚያው። በሬዲዮ ላይ አንድ በተደጋጋሚ የምሰማው ዕቅድ ግን ከሱስ መላቀቅ የሚል ነው። ይህ ዕቅድ ግን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም መታቀድ አለበት። ቀላል ችግር አይደለም።

እንግዲህ እቅድ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ የትኛውም ሰው ያቅዳል። ጎዳና ላይ ከሚያድረው ጀምሮ በፎቅ ላይ ፎቅ የደራረበው ሁሉ ያቅዳል። የተሳካለት ይሳከለታል ያልተሳካለትም ለሚቀጥለው ዓመት ይደግመዋል። ጎበዝ! ማቀድ ብቻውን ዋጋ የለውም፤ ዋጋ የሚኖረው ማሳካቱ ነውና ከታቀደበት ቀን ነው መጀመር። ዕቅድ ለማታሳኩ ሰዎች ይቺን የበዕውቀቱ ሥዩምን ግጥም ጋበዝኳችሁ።

እኛ እኮ ለዘመን

ክንፎቹ አይደለንም

ሰንኮፍ ነን ለገላው፤

በታደሰ ቁጥር

የምንቀር ከኋላው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You