ተስፋ ሰጪው የመኸር እርሻ – በኦሮሚያ ክልል

በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ልዑክ ከሰሞኑ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች መካከል አራት በሚደርሱ ዞኖች በማቅናት የመስክ ምልከታ አካሂዷል። የመስክ ምልከታው በዋናነት ያካተተው በኩታ ገጠም የተዘራው የቦለቄ እና የስንዴ ማሳ እንዲሁም በየዞኖቹ እየተተገበሩ የሚገኙ የሌማት ትሩፋቶችን ለመጎብኘት ነው።

በርዕሰ መስተዳደሩ የተመራው ልዑክ፣ ያቀናባቸው ዞኖች ምዕራብ አርሲ፣ አርሲ፣ ምዕራብ ሐረርጌ እና ምስራቅ ሐረርጌ ናቸው። የልዑክ ቡድኑ እንቅስቃሴ ምንም እንኳ ጥድፊያ የተሞላበት ቢሆንም፤ ከአንዱ ዞን ወደሌላኛው ዞን በተንቀሳቀሰ ቁጥር ግራ ቀኙ በስፋት ሞልቶ የሚስተዋለው በኩታ ገጠም እየለማ ያለ የስንዴ አሊያም የቦለቄ ወይም ደግሞ ሌላ የአዝርዕት ዓይነት ነው። አንዳንድ ወረዳዎች የደረሰ ቡቃያ ከፍ ብሎ ሲታይ ዓይን ያጠግባል። ለዓይ ን የሚያጠግበው ቡቃያ በጥቂቱ በሚነፍሰው ነፋስ ዛላው ከግራ ከቀኝ ይዘናፈላል። ከመንገድ ገንጠል ብሎ ወደ ውስጥ ሲገባ ደግሞ የከብት እርባታውና ማደለቢያው፣ የዶሮ እርባታውና የንብ ማነብ ሥራው በወጣቱና በአካባቢው ነዋሪ ሲከናወን ይስተዋላል።

የመስክ ምልከታው ጅማሬውን ያደረገው በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ወረዳ በኩታ ገጠም የተዘራውን ቦለቄ በመጎብኘት ሲሆን፣ ከቦለቄ በተጨማሪ ዞኑ በስንዴ፣ በገብስ፣ በአኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ሱፍ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝና ሩዝ ላይ እንዲሁ በኩታ ገጠም እያለማ መሆኑን የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብሳ ገመዳ በወቅቱ ተናግረዋል። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ የምዕራብ አርሲ ዞን በአጠቃላይ ከ660 ሺ ሔክታር በላይ መሬት በመኸር የተያዘ ነው። ከእነዚህ መካከልም በአዝርዕት ዘርፍ 11 የሚጠጉ ኢንሼቲቮች እህል ላይ እየተሰራ ይገኛል። ከዛ ውስጥ አንዱ እና ወሳኙ ተብሎ እየተሰራ ያለው ደግሞ በቦለቄ ላይ ነው።

በዞኑ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት የቦለቄ ምርት በስፋት ሲመረት አይስተዋልም። ከዚህ ባለፈም ለውጭ ምርት እንዲሆን ታስቦበት እምብዛም እንደማይመረት የተናገሩት አቶ ኢብሳ፣ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከ144 ሺ ሔክታር መሬት በላይ በቦለቄ ተሸፍኗል ይላሉ። ከዚህ ቀደም ቦለቄ እንደ አንድ መደበኛ ምርት የሚታይ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን የወጪ ምርት በመሆኑ ትልቅ ትኩረት በመንግሥት በኩልም ተሰጥቶታል። በመሆኑም አርሶ አደሮችን በሰፊው በማሳተፍና በማነቃቃት የቦለቄ ምርት ሥራን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። ከዚህ ቀደም ለቦለቄ ክላስተር የተሰጠው ቦታ አነስተኛ ሲሆን፣ የሚሸፍነው የመሬት መጠንም አነስተኛ ነበር። ከዚህ አንጻር አምና በዞኑ በቦለቄ የተሸፈነው መሬት ወደ 80 ሺ ሔክታር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ አንዱና ዋናው ኢኒሼቲቭ እንደመሆኑ መሬቱን የበለጠ ማስፋት እና ምርታማነቱንም መጨመር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ቀደም ሲል የቦለቄ ምርት አርሶ አደሩ በሚያመርትበት ጊዜ ትልቁ ችግሩ የገበያ ሲሆን፣ የደላላ ሰንሰለት በማስወገድ አርሶ አደሩ ከላኪውና አስመጪው ጋር በቀጥታ መገናኘት እንዲችል በኮንትራክቿል ፋርሚንግ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል። የቦለቄው ምርት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው እንደመሆኑና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ በመሆኑ እንደ ዞኑም ከ40 በላይ የሚሆኑ አስመጪና ላኪዎች ወይም በኮንትራክቿል ፋርሚንግ ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶችን የማሰማራት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

“እኛ ዓላማ አድርገን የምንሰራው የራሳችን ብራንድ የሆነ ቦለቄ ለዓለም ገበያ ለመላክ ነው።” ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ይህንንም ለማረጋገጥ ሰፋፊ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በጥራትም በብዛትም ጭምር በአግባቡ በመሥራት ላይ እንገኛለን። ከዚህም የተነሳ ገበያ ላይ ተፈላጊ የሆነ ቦለቄ ማምረት አለብን በሚል መጠነ ሰፊ ሥራ በመተግበር ላይ ነን። ከዚህ ጋር ተያይዞ አስመጪና ላኪዎችም ከእኛ ጋር በመሥራት ላይ ሲሆኑ፣ የጋራ ውይይትም በየጊዜው እናደርጋለን ብለዋል።

የኢፌዴሪ እና የክልል አመራሮችን የያዘውን ልዑክ በመምራት የመስክ ምልከታውን በተለያዩ የየዞኖቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሲያካሄዱ የቆዩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በኩታ ገጠም ተዘርቶ መሬቱን ሙሉ ለሙሉ ያለበሰውን አዝርዕት እና የሌማት ትሩፋቱን ካስተዋሉ በኋላ በተመለከቱት ልማት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የየአካባቢውን አርሶ አደሮች ለበለጠ ልማት በንግግራቸው ያነሱ ሲሆን፣ በመስክ ምልከታው ያስተዋሉት ነገር ቢኖር አሁን በተያዘው አቅጣጫ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሽመልስ እንዳሉት ከሆነ፤ በአጠቃላይ በእንስሳት ልማትም፣ በአዝርዕት ልማቱም ሆነ በቅባት እህሉ እና በሌሎችም ልማቶች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩ ናቸው። እነዚህ ልማቶች ተደምረው በቀጣናው ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችልም መገንዘብ ያስችላል። ይህ ቀጣና ትልቅ አቅም ያለው ነው። ቆላ፣ ደጋ እና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያለው አካባቢ እንደመሆኑ ለእንስሳት ልማትም ሆነ ለሌሎች ግብርና ሥራዎች ትልቅ አቅም ያለው ነው። የተሰሩ ሥራዎችም ሲታዩ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ስለመሆናቸው ማስተዋል ይቻላል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፣ “በዚህ አጋጣሚ የአካባቢውን አመራር እና ሕዝቡን በጣም ማበረታታት እፈልጋለሁ።” ሲሉ ጠቅሰው፤ በክልሉ በክረምት ሥራው ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው የግብርና ትራንስፎርሜሽኑ አራት ግቦችን ማዕከል ባደረገ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ የውጭ ኤክስፖርትን በጥራትም በብዛትም መጨመር እና በዚህ ውስጥ ደግሞ ሰፊ የሥራ እድል የመፍጠር ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ዓመታት በክልላችን ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው በቅባት እና በጥራጥሬ እህል ላይ ነው የሚሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ነው የተናገሩት። በዚህ ዓመትም ከሶስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ በሰሊጥ፣ በማሾ፣ በቦለቄ፣ በለውዝ፣ በአኩሪ አተር እንዲሸፈን ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በአጠቃላይ በቦለቄ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት፣ በማሾ ደግሞ ወደ 300 ሺ ሔክታር መሬት ለመሸፈን እየተሰራ ነው። ለውዝ ከ500 ሺ ሔክታር መሬት በላይ እንዲሁም አኩሪ አተር 600 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ለመሸፈን እየተሰራ ነው። እስካሁን 500 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ተዘርቷል። ሰሊጥ 500 ሺ ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ሲሆን፣ ከእነዚህ የቅባት እህሎች ከፍተኛ ምርት የሚጠበቅ ይሆናል።

 

እነዚህ የቅባት እህሎች ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ ነው። በሀገር ውስጥም ከምግብ ዘይት ጋር ተያይዘው ያሉ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚያገኙት ከእነዚህ የቅባት እህሎች መሆን ይችላል። ከዚህም ባለፈ ደግሞ ለወጪ ምርት የምናቀርብበትን እድል የሚፈጥር ነው። ጥራጥሬውም በተመሳሳይ መልኩ ለውጭ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀርብ ነው። በዚህ ረገድ ኢንሼቲቮችን ቀርጸን መንቀሳቀስ ከጀመርን ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመታችንን ይዘናል። በማለት እስካሁን ያለው ሂደትም ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

በክልሉ በሚገኙ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥሩ ውጤት አይተናል የሚሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሻሸመኔ ወረዳ ላይም በክላስተር እየለማ ያለው አዝርዕት ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ማስተዋል መቻላቸውን አስረድተዋል። ይህን አጠናክረን ከሄድን ከፍተኛ ውጤት ይመጣል የሚል እምነት አለን በማለት በግብርና ሥራው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

‹‹ሌላው የስንዴ ልማታችን ሲሆን፣ የክረምት ማለትም የመኸር እቅዳችን ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው›› ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ከዚያ ውስጥ ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ገና ክረምት ያልገባባቸው ዞኖችና ዘር የተጀመረባቸው አካባቢዎችም አሉ። ለአብነትም ሲጠቅሱ እንዳሉት፤ የበልግ ምርት እንደ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ አካባቢ ስንዴ እየተዘራ ይገኛል። በቀጣይም የጉጂ እና ቦረና አካባቢዎችን አካትተን የምንዘራ ሲሆን፣ እነርሱ ሲካተቱ እስከ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እስከ ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሔክታር እንደርሳለን ብለን አቅደን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ አብራርተዋል። ስንዴ በስፋትም በጥራትም እየጨመረ መምጣት ችሏል። ከፍተኛ ውጤትም ያገኘበት እንደመሆኑ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ፤ ኢኒሼቲቩ በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ነው። በወቅቱ ሲጀመር በክረምት ይሸፈን የነበረው 900 ሺ ሔክታር መሬት አካባቢ ነበር። ከዚያ ቁጥር በመነሳት በአሁን ወቅት ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በስንዴ መድረስ ተችሏል። ይህ የሚያሳየው ምርታማነቱን መጨመር ከተቻለ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ነው።

በአጠቃላይ ዘንድሮ በክልሉ በመኸር እርሻ ለመሥራት የታቀደው ወደ አስር ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ነው። እስካለፈው ሳምንት ከዚህ ውስጥ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው ሁለቱ ባሌዎችና የጎጂ እንደሆኑ የቦረና አካባቢ በዘር ሲሸፈን ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። ከዚህ በመነሳት እቅዳችንን እናሳካዋለን የሚል እምነት አለን ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ወደፊት ምርታማነት ላይ ትኩረት አድርገን ከሰራን፣ የዘር ግብዓት፣ ኮምፖስት እና ሌሎች ግብዓት ላይ ከተጋንና ሜካናይዜሽንን በአግባቡ ከተጠቀምን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ አያቅተንም። እኛ አሁን ከምናመርተው ምርት ከሁለትና ሶስት እጥፍ በላይ ማደግ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ሽመልስ ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ሽመልስ፣ በአሁኑ ወቅት ከዓለም አንጻር ከሁሉም አዝርዕት የእኛ ምርታማነቱ በጣም ዝቅተኛ ነው። ስለሆነም ምርታማነቱ ላይ በደንብ ሰፋ አድርገን ከሰራን ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይችላል ብለዋል።

በዚህ ረገድ አርሲ ዞን እንደ ምሳሌ የምናየው ጥሩ ውጤት እያመጣ ያለ ዞን ነው። ይህን አጠናክረን፣ መካናይዜሽኑን አሳልጠን፣ የውሀ አጠቃቀማችንም አሻሽለን ከሄደን በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት እናስመዘግባለን። የግብርና ትራንስፎርሜሽኑም ያቀድነውን ያህል እናሳካለን ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You