ላለፉት አምስት ቀናት በፔሩ ሊማ ሲካሄድ የቆየው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በተካሄዱ ውድድሮች መቋጫውን አግኝቷል። ከፍተኛ ፉክክር ሲያስተናግድ በቆየው ውድድር ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች ድምቀት ነበሩ። ሻምፒዮናው በፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ለተከፋው ስፖርት ቤተሰብ ተስፋ የሰጠ ሲሆን፤ በተሰበሰበው የሜዳሊያ ቁጥርም እንደተለመደው ቡድኑ ከቀዳሚዎቹ መካከል ሊሰለፍ ችሏል።
በሴቶች የ5ሺ ሜትር ድል የጀመረው የኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተሳትፎ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሲቀጥል፤ ከትናንት በስቲያ ደግሞ በሴቶች 3ሺ ሜትር እና ወንዶች 800 ሜትር ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያዎች የደረጃ ሰንጠረዡን ተቀላቅለዋል። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፍሬዋ አትሌት አለሽኝ ባወቅ እና ጄነራል ብርሃኑ የሃገራቸውን ሰንደቅ በድል ያውለበለቡ ሲሆን፤ አትሌት ማርታ ዓለማየሁ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ልትሆን ችላለች።
በሴቶች 3ሺ ሜትር ውድድር እአአ ከ2016 አንስቶ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባ አታውቅም። በዚህ ሻምፒዮና ግን ሃገራቸውን በመወከል የሚሳተፉት አትሌቶች ያላቸው ፈጣን ሰዓት በድጋሚ የሜዳሊያ ሽሚያው አካል መሆኗን የሚያመላክት ነበር። በፍጻሜው ሩጫ ግን ኬንያዊቷ አትሌት ማሪዎን ጄፕጌቲች አብዛኛውን ርቀት በመሸፈን ግምቱን አጠራጣሪ አድርጋው ነበር። ይሁንና ርቀቱ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀረው ከፍተኛ የራስ መተማመን የነበራት ኢትዮጵያዊቷ አለሽኝ ባወቅ አስገራሚ በሆነ ፍጥነት አልፋት 8:50.32 በሆነ ሰዓት ድሉን የግሏ ማድረግ ችላለች።
ኬንያዊቷ አትሌት ከሁለት ሰከንድ በኋላ ተከትላት በመግባት የብር ሜዳሊያውን ልታጠልቅ ችላለች። ሌላኛዋ ጠንካራ የሜዳሊያ ተፎካካሪ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማርታ ዓለማየሁ ስትሆን የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው በአንድ ሰከንድ ብቻ ተበልጣ ነው። በርቀቱ በተገኙት ሁለት ሜዳሊያዎችም ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የ4ኛ ቀን ውሎ በሰንጠረዡ ቀዳሚዋ ሃገር መሆኗን ማረጋገጥ ተችሎ ነበር።
በሰኔ ወር በሃዋሳ ከተማ ከተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ሻምፒዮና በ800 ሜትር አሸናፊ የነበረው አትሌት ጄነራል፤ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ በስፔን ነርጃ በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ነበር። ይሁንና በርቀቱ የሚጠበቀው ሰዓት ባለመመዝገቡ ብሔራዊ ቡድኑ በርቀቱ አለመሳተፉ የሚታወስ ነው። አትሌቱ በ20ኛው የወጣቶች ሻምፒዮና ሃገሩን ሲወክል ባለፉት ቀናት በተካሄዱት የማጣሪያ ውድድሮች ያሳየው አሯሯጥ በፍጻሜው ለሜዳሊያ ተፎካካሪነት እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር።
በዚህ ርቀት ባለው ፈጣን ሰዓት ምክንያት የሻምፒዮናው ክስተት ይሆናል በሚል ለአሸናፊነት ይጠበቅ የነበረው አትሌት አውስትራሊያዊው ፓይተን ክሬጅ ነበር። በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳታፊና በግማሽ ፍጻሜው አስገራሚ ብቃቱን ያንጸባረቀው አትሌቱ በወጣቶች ሻምፒዮና ልዩነት ፈጣሪ እንደሚሆን አስቀድሞ ተገምቶ ነበር። በእርግጥ ባልተጠበቀ ሁኔታ በማጣሪያዎቹ ላይ ብቃቱን ያሳየው ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈተና ሊሆን እንደሚችል በመታየቱ ውድድሩ ይበልጥ አጓጊ ሆኖ ነበር። ፈጣን በነበረው የፍጻሜ ውድድር ላይም የ19 ዓመቱ ጄነራል አሳማኝ በሆነ አሯሯጥ 1:46.86 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሃገሩ ማስገኘት ችሏል። 6 ማይክሮ ሰከንዶችን የዘገየው ክሬጅ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ ጃፓናዊው ኮ ኦቺ ደግሞ ከአንድ ሰከንድ በኋላ በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቁን አረጋግጧል።
በዚህ ርቀት እምብዛም ውጤታማ ያልሆነችው ኢትዮጵያ በቅርቡ በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም ኦሊምፒክ ላይ በሴቶች ሜዳሊያ ሲመዘገብ፤ በወንዶች በኩል ግን አትሌት መሐመድ አማን በኋላ ተፎካካሪ አትሌት ማፍራት ሳይቻል ዓመታት መቆጠራቸው የሚታወቅ ነው። በዚህ ቻምፒዮና ላይ በርቀቱ ጠንካራ ተፎካካሪና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ጄነራል በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተስፋ ሊሆን ችሏል።
ሻምፒዮናው ትናንት በነበረው የመጨረሻውና የ5ኛ ቀን ውሎም (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከእኩለ ሌሊት በኋላ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለሜዳሊያ የሚጠበቁባቸው የ1ሺ500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም የወንዶች 3ሺ ሜትር ውድድሮች ተካሂደዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም