የአንድነት ፓርክ የመካነ እንስሳትና አኳርየም – አዲሱ የስምምነት ማዕቀፍ

በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች የመካነ አንስሳና አኳሪየም (zoo tourism) በመጎብኘት ቀዳሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጎብኚዎች መዳረሻ ከሚያደርጓቸው ታሪካዊ፤ ባሕላዊ መስሕቦች፣ የአርኪዮሎጂና የፓሊዮንትሮፖሎጂካል ስፍራዎች በላይ የተሻለ ቁጥር የሚያስመዘግቡትም በከተሞች መካከል የሚገኙት ሰው ሠራሽ የዱር እንስሳት መካነ አንስሳት ስፍራዎች ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ይነገራል።

በዚህ የተነሳ ሀገራት የመካነ እንስሳትና አኳሪየም ቱሪዝምን (zoo tourism) በማቋቋም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለማግኘት የመስሕብ ስፍራዎቻቸውንና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ ይጠቀሙባቸዋል። እነዚህ የቱሪስትን ቀልብ የሚስቡ የከተማ ውስጥ መካነ እንስሳት ለጉብኝት ከሚኖራቸው ፋይዳ ባሻገር የሥነ ምሕዳርን ሚዛን ለመጠበቅ፣ ሊጠፉ የተቃረቡ እንስሳትን ለማራባት እና ለተመራማሪዎች እንደ ተቋም ለማገልገል ምቹ መሆናቸውን የዘርፉ ምሑራን ይመሰክራሉ።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት በአዲስ አበባ ከተማ መካነ እንስሳት (በተለምዶ አንበሳ ግቢ እየተባለ የሚጠራውን) አቋቁማ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎች ክፍት አድርጋ ቆይታለች። በኢትዮጵያ የሚገኙ የዱር እንስሳትም በከተማዋ ስድስት ኪሎ አካባቢ በተዘጋጀላቸው ሰው ሠራሽ መኖሪያ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስፍራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልሆነ እና ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉት በማንሳት ትችት ይቀርብበት ነበር። (አሁን በአዲስ መልኩ መሠራቱን መረጃዎች ያመለክታሉ) ሀገሪቱ ካላት ሀብት አንፃርም ስፍራው በቂ እንዳልነበር የሚሞግቱ ነበሩ።

ከአምስት ዓመት በፊት ግን ከላይ ላነሳናቸው አስተያየቶች ምላሽ የሚሰጥ ዘመናዊ መካነ እንስሳ እና አኳሪየም (city zoo) በአዲስ አበባ እምብርት ተገንብቶ ይፋ ሆኗል። ይህ ፓርክ በዓለማችን ላይ ከሚገኙና ደረጃቸውን ከጠበቁ ሰው ሠራሽ ፓርኮች ጋር የሚወዳደር እንደሆነ ይነገራል። ጎብኚዎችም በስፋት ተመራጭ እያደረጉት ይገኛሉ።

የአንድነት ፓርክ በኢትዮጵያ አዲስ የመስሕብ መዳረሻዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በዱር እንስሳት ልማትና ምርምር ዙሪያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይገመታል። ይህንን አስተዋፅዖውን ለማሳደግና ከሰሞኑ ሥራዎች መጀመራቸውን የፓርኩ ኃላፊዎች ይፋ አድርገዋል። በሂደቱም የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከፓርኩ ጋር እንደሚሠራ ተመልክቷል። በዚህም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ሁለቱ አካላት የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ በተገኘበት አንድ የመግባቢያ ስምምነት አድርገዋል። እኛም ይህንን የመግባቢያ ስምምነት ከዚህ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ የታላቁ ቤተ መንግሥት የአንድነት ፓርክ እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች በጋራና በቅንጅት ለማከናወን ያደረጉት ነው። ስምምነቱን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ በባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራና በአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር) የተፈፀመ ነበር።

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኩመራ ስምምነቱ በተፈፀመበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳትን በተመለከተ የቴክኒክ ድጋፍ ጥያቄ ከፓርኩ ሲቀርብለት ምላሽ ለመስጠት ትልቅ መሠረት ይሆናል። በተጨማሪም በተፈጥሮ የመኖሪያ አካባቢ በሚኖሩ የዱር እንስሳትም ሆነ በታላቁ ቤተ መንግሥት የአንድነት ፓርክ መካነ እንስሳት እና አኳርዬም የሚገኙ በዱር እንስሳት አረባብ፣ ጥበቃ ፣ጤና፣ አመጋገብ አኗኗር እንዲሁም ተያያዥ በሆነ ሥነ-ሕይወታዊና ሥነ-አካላዊ ጉዳዮች ላይ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ለማገዝ ይረዳል። ፓርኩም ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያሉትን ልምዶች ያካፍላል።

‹‹ፓርኩን በተመለከተ ከሃገር ውስጥ የሚገቡትን የዱር እንስሳት ዝርያና ብዛት ለመወሰን በጥናት በመለየት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚፈቀድ ሆኖ ቁጥራቸው የተመናመኑ ሆነ ሌሎች ዝርያዎችን በተመለከተ እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ፓርኩ እንዲገቡ ያደርጋል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ወደ ፓርኩ የገቡት የዱር እንስሳት ዝርያዎች ደኅንነታቸውን በጠበቀ መልኩ መከናወኑን በጋራ በመከታተል ድጋፍ ሌላኛው የስምምነቱ አካል እንደሆነ ይገልፃሉ። በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳትን በተመለከተ የቴክኒክ ድጋፍ ጥያቄ ከፓርኩ ሲቀርብላቸውም ምላሽ እንደሚሰጡ ያስረዳሉ።

ባለሥልጣኑ በሃገሪቱ በሚገኙ የዱር እንስሳት ጤና ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ከተባባሪ ወገኖች ጋር በጋራ ፓርኩን በማሳተፍ መፍትሔ ይፈልጋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚሀ ተግባርና ኃላፊነቶቹ መካከልም የሚከተሉት ዋንኞቹ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በዚህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የዱር እንስሳት ልማትና አጠቃቀም በሚመለከት በትብብር የሥልጠና ኘሮግራም ማካሄድ፣ ወቅታዊ መረጃዎችና ተሞክሮን መሰብሰብ፣ የዱር እንስሳት አኗኗርና ባሕሪ ተዛማጅና ተስማሚ የሆኑ ውበትና ጥምር ጥቅም ያላቸው ዕፅዋትን በመምረጥና በመንከባከብ ሂደት ላይ ድጋፍ በማድረግ የአንድነት ፓርክን ለማገዝ ስምምነት ላይ መድረሱን ይገልፃሉ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ከስምምነቶቹ መካከል በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ የቴክኒክ ዕርዳታና ሌላም ድጋፍ ሊሰጡ ከሚችሉት አካላት ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ፓርኩ እንዲሳተፍ ማድረግ፣ ወቅታዊ እና አስፈላጊ የሆኑ የአጭር፣ መካከለኛና የረዥም ጊዜ የጋራ የልማት ኘሮጀክቶች የድርጊት መርሐ ግብር በመቅረጽ አብሮ መሥራት፣ ባለሥልጣኑ በፓርኩ ተሰብስበው የሚጠበቁት የዱር እንስሳት ቁጥር ከመጠን በላይ ሆኖ ለማስተዳደር በሚያስቸግር ጊዜ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ከመጠን በላይ ለሆኑት የዱር እንስሳት አኗኗር አመቺ ወደ ሆነው የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታ ወይም በጥናት ወደ ተለዩ የመኖሪያ አካባቢ እንዲለቀቁ ማድረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ገልፀዋል።

የታላቁ ቤተመንግሥት የአንድነት ፓርክን በመወከል ስምምነቱን ያደረጉት ደግሞ የፓርኩ ዋና ዳይሬክተር ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው ስምምነቱን አስመልክቶ አንደገለፁት፤ በፓርኩ የሚሠሩ ተግባራት ከአካባቢ ልማትና ጥበቃ ዓላማዎች ጋር እንዲስማሙ አድርጐ እንደሚፈፀም ተናግረዋል። ይህንን ተግባር ለማከናወንም ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ማድረግ እንዳስፈለገ አስረድተዋል።

ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በፓርኩ ወደ ተገነባው የዱር እንስሳት መኖሪያ የሚገቡ የዱር እንስሳትን በጥናት በመለየት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ጠይቆ ያስገባል ያሉት ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር)፤ ከዚህ በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለው ልምድ፣ ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የዱር እንስሳት አኗኗርና ባሕሪ ተዛማጅና ተስማሚ የሆኑ ውበትና ጥምር ጥቅም ያላቸው ዕፅዋትን በመምረጥና በመንከባከብ ሂደት ላይ ድጋፍ በማድረግ እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት የአንድነት ፓርክ እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በሚያስተሳስሯቸው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች በጋራና በቅንጅት ማከናወን የሚገባቸውን ተግባራት በማመላከት በቅንጅትና በትብብር የልማትና ጥበቃ ሥራውን በማከናወን የተቋማቱ የተናጠል ራዕይ በጋራ እንዲሳካ ማድረግ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ስምምነቱ ያስፈለገው በዚህ ምክንያት መሆኑንም ይገልፃሉ።

እንደ ታምራት (ዶ/ር) ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር የተደረገው ስምምነት ማዕቀፍ በፓርኩ በተከለለ ቦታ ላይ መካነ እንስሳት እና አኳርዬም ማስተር ኘላን መሠረት ለዱር እንስሳት የመሬት አጠባበቅና ዲዛይን ሥራዎችን ለማከናወን፤ የዱር እንስሳትን ከተፈጥሮ የመኖሪያ አካባቢያቸው የማልማትና ሕገወጥ ተግባራት እንዳይፈፀሙባቸው የመከላከል ሥራውን ለመሥራት፤ የዱር እንስሳት ልማትና አጠቃቀም በሚመለከት በትብብር የሥልጠና ኘሮግራም ለማካሄድ፣ ወቅታዊ መረጃዎችና ተሞክሮን ለመሰብሰብ እና ለተጠቃሚዎች ለማሰራጨት እንደሚረዳቸው ይናገራሉ።

‹‹በፓርኩ ውስጥ ባሉ የዱር እንስሳት አኗኗርና ባሕሪ ተዛማጅና ተስማሚ የሆኑ ውበትና ጥምር ጥቅም ያላቸው ዕፅዋትን ይመርጣል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ባሻገር የዱር እንስሳቱን እንደሚያራባ፣ እንደሚያስፋፋ እንዲሁም እንደሚንከባከብ ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ለመሰል ፓርኮችም ተሞክሮውን ያካፍላል ይላሉ። በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ የቴክኒክ ዕርዳታና ሌላም ድጋፍ ሊሰጡ ከሚችሉት አካላት ጋር ግንኙነት እንደሚመሠርትም ያብራራሉ።

የዝግጅት ክፍላችን በወቅቱ በስፍራው ተገኝቶ መረዳት እንደቻለው የአንድነት ፓርክ ውስጥ የሚገኘውን የመካነ እንስሳት በተመለከተ የተደረገው ስምምነት የሚከተሉት ማዕቀፎች ጨምሮ ይይዛል።

በሰነዱ ላይ እንደተመለከተው፤ በፓርኩ ዙሪያ ወቅታዊ እና አስፈላጊ የሆኑ የአጭር መካከለኛና የረዥም ጊዜ የጋራ የልማት ኘሮጀክቶች የድርጊት መርሐ ግብር በመቅረጽ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ይሠራሉ። በፓርኩ የሚሠሩ ተግባራት ከአካባቢ ልማትና ጥበቃ ዓላማዎች ጋር እንዲስማሙ አድርገው ይፈጽማሉ። የአንድነት ፓርክ በመካነ እንስሳት ውስጥ ተሰብስበው የሚጠበቁት የዱር እንስሳት ቁጥር ከመጠን በላይ ሆኖ ለማስተዳደር በሚያስቸግር ጊዜ ከባለሥልጣኑ ጋር በመነጋገር እና አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ አመቺ ወደ ሆነው የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታ ወይም በጥናት ወደ ተለየው የመኖሪያ አካባቢ እንዲለቀቁ ያደርጋሉ።

እንደ መውጫ

የኢትዮጵያ አንድነት ፓርክ በሀገሪቱ ካሉት ዘመናዊ እና ዘርፈ ብዙ የቱሪስት መስሕቦች አንዱ መሆኑን ጎብኚዎች ይመሰክሩለታል። ግንባታው በተካሄደ በሁለት ዓመት ውስጥም ከ500 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ጎብኝተውታል። የኢትዮጵያ አንድነት ፓርክ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የብሔራዊ ታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኛል። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ በ1800ዎቹ ባሳነፁት በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በሚገኘው በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አንድነት ፓርክ አዲስ አበባን ለማስዋብ እየተሠሩ ካሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የመዳረሻ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንድነት ፓርክ ፕሮጀክትን በአምስት ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ያስገነቡት ሲሆን ከጥቅምት 2011 ዓም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ቆይቷል። የአንድነት ፓርክ በ20 ሄክታር መሬት ላይ በብሔራዊ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተመሠረተ ነው። ስፍራው ለጎብኚዎች ከታሪካዊ፣ ባሕላዊ እሴቶች እና የተፈጥሮ ስጦታዎች ለመማር ዕድል እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።

የኢትዮጵያ አንድነት ፓርክ የተፈጥሮ፣ የባሕል፣ ታሪካዊ እና የቅርስ ቱሪዝም መስሕቦች በአንድ ቦታ ላይ የያዘ መሆኑን የፓርኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። የተፈጥሮ መስሕቦች ከሆኑት ውስጥ 37 አጥቢ እንስሳት፣ ዘጠኝ የእንስሳት አይነቶች ማለትም ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ኩዱ፣ ኢምፓላ፣ ኢላንድ፣ ጌምስቦክ፣ ኒያላ፣ ዋይልድ ቤስት እና ነጭ አውራሪስ፣ 13 የውሃ ውስጥ እንስሳት ዝርያዎች እና ሀገር በቀል የተለያዩ አእዋፍ የያዘ ነው። በተለምዶ ጥቁር አንበሶች የሚባሉትና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትም በዚሁ ስፍራ አሉ። ይህንን ስፍራ በየቀኑ በርካታ ሰዎች በመታደም ይጎበኙታል። በዓመትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች ይመለከቱታል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You