እንደ ጀመርን ጨረስነው ልበል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ እና 4ኛ ተርባይኖች ሰሞኑን ሥራ መጀመራቸውን ሌሎቹ ዩኒቶች በተቀመጠላቸው እቅድ መሠረት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። እንዲሁም የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2ሺህ 800 ሜ.ኪ. ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውሃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል። ይህ የተመጣጠነ የውሃ ልቀት ግብርናን፣ የኃይል የማመንጨት ሥራን፣ በቀጣናው ያለ የሀብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማል ብለዋል።

ግድቡ ገጥሞት ከነበር የኮንትራት አመራርና አስተዳደር ችግር፣ የማስፈጸምና የመፈጸም ውስንነት፣ ከውስብስበ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና ዝርክርክነት ተላቆ ከለየለት ክሽፈት ድኖ ነፍስ የዘራው በለውጡ ማግስት በተሰጠው አመራር ስለሆነ የለውጡ ትሩፋትና ደማቅ ዐሻራ ያረፈበት ሜጋ ፕሮጀክት ነው። እንደ ስሙ አንድምታው ከኢኮኖሚያዊ አውታርነት አድማስ ባሻገር ነው። የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ችቦ የለኮሰም ነው ማለት ይቻላል። ሲጠናቀቅ የብርሀን ጭላንጭል ለናፈቃቸው ከ50 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ፀዳል ሊሆን አሽቷል።

በተደጋጋሚ በሚከሰት የኃይል መቆራረጥና እጥረት አሳሩን እየበላ ለሚገኘው ኢንዱስትሪም ሆነ ሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ የምሥራች ይዟል። የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ በዓመት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘትም አልሟል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከፍ ሲልም በአፍሪካም ሆነ በዓለም የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ ከፍ ያደርጋል።

ይህ አንድ ላይ ሲደማመር ለኢትዮጵያ ህዳሴ መበሰር ነጮች እንደሚሉት የመስፈንጠሪያ ሰሌዳ/spring- board/ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዳሴ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture/ የሆነው ይህ ግዙፍ ሕልምና ራዕይ እውን ሆኖ ከአራት ተርባይን 1550 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በቅቷል። ቀደም ሲል በሁለት ተርባይኖች 750 ሜጋ ዋት፤ አሁን ደግሞ በተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች 800 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ያመነጫል ማለት ነው።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዚህ የበቃው በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ ነው። ከሊስትሮ እስከ እንጨት ለቃሚ፤ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን፤ ከአጣ ከነጣ ድሀ እስከ ባለጠጋና ባለሀብት፤ ከሀገሬው እስከ ዲያስፖራው፣ ወዘተረፈ ጠጠር ያልጣለ የለም። ከዓመት ልብሱ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ፣ ከልጆቹ ጉሮሮ ቀምቶ የታላቁን ለግድብ ቦንድ ገዝቷል። ገንዘብ አበርክቷል። ለግሷል። ጉልበቱንና እውቀቱን አዋጥቷል። ከፍ ሲልም ሕይወቱን ሰውቷል ።

በሀገሪቱ ታሪክ ኢትዮጵያዊ በሞላ ያለ ልዩነት እስላም ክርስቲያን፤ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ሀድያ፤ ሳይል በአንድነት ሠራዊትና ደጀን የሆነለት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በነገራችን ላይ በሀገሪቱ ታሪክ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሜጋ ፕሮጀክት ይሄን ያህል ገንዘብ አዋጥተው አያውቁም። የዛሬው ትውልድ እንደ አረንጓዴው ዐሻራ ሁሉ በህዳሴው ያሳየው ርብርብ የቀደሙትን ትውልዶች ክብረ ወሰን ሁሉ ሰባብሯል ማለት ይቻላል ።

ተደቅኖበት ከነበረ የለየለት የክሽፈት አደጋ ታድጎ በእነዚህ ቀውጢና ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ዓመታት ሁሉ ጥርሱን ነክሶ በአጭር ታጥቆና ህልቆ መሳፍርት ለሌለው ጫና አንድ ጊዜም ሸብረክ ሳይል ለዚህ ያበቃው አካል ያለ ምንም ስስትና ንፍገት በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል። የእንችላለን መንፈስን ለኢትዮጵያውያን ከፍ ሲልም ለመላው አፍሪካ ያጋባው የህዳሴው ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ ነው። ካለምንም እርዳታና ብድር በዜጎች አበርክቶና በመንግሥት በጀት እየተገነባ ያለ ተምሳሌታዊ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ተርባይንን የኃይል ማመንጨትን ካስጀመሩ በኋላ አስተላልፈውት የነበር ጥልቅና ወካይ መልዕክት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። “በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚባሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ግን ዕድልም ድልም ነው። ይሄ ትውልድ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ባለ ዕድልም ባለ ድልም ነው። የሺ ትውልድ ጥያቄ በሚመለስበት ዘመን ተገኝቶ ግድቡ ሲገደብ በዓይን ማየት፣ በእጅ መዳሰስ፣ በእግር መርገጥ ባለ ዕድል ሲያደርግ፤ ለግንባታው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ከለገሡት፣ በዲፕሎ ማሲና በሚዲያ ለዓባይ ከሚከራከሩት፣ ታሪክ ሠሪ ጀግኖች ወገን መሆን ደግሞ ባለ ድል ያድርጋል። ” “እነሆ አሁን የህዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውኃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈንና እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል። በፈጣሪ ርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርም። እንኳን ደስ ያለን!!” ነበር ያሉት።

የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል። ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ደግሞ ባለፈው ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ ተጠናቋል። በሦስተኛው የውሃ ሙሌት ደግሞ 22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ መያዝ ችሏል። ይህ ሀገራዊ ግዙፍ የብርሃን እሸት የምሥራች እንካችሁ ብሏል።

ከየካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአንድ ተርባይን ብቻ 275 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። የሁለተኛው ተርባይን ደግሞ 275 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። አራተኛው የውሃ ሙሌትም ተጠናቋል። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል 5ሺ150 ሜጋ ዋት ይደርሳል። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።

በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ643 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን እና የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 አንስቶ እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከፍ ያለ ሀብት ማመንጨት ተችሏል። ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ ንግግር ስንመለስ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በግድቡ ቦታ ተገኝተው ያበሰሩ ዕለት ፤ “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ደስ የሚያሰኝ ታላቅ ድል ነው። ሆኖም ዓባይ ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለዓለም ተሰጥቷል።” ብለዋል።

በእሳቸው አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሠራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ለኢትዮጵያውያን እራትና መብራት ሊሆን ሁለተኛ እሸት የምሥራች ብሏል። የግብፅን የሱዳንን የአሜሪካና የምዕራባውያንን የዓረብ ሊግን ዓለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናን በጥበብና በማስተዋል በመቋቋም መሻገር ተችሏል።

ግብፅ የግድቡን ጉዳይ የዓለም የደኅንነትና የሠላም ስጋት አድርጋ ለማሳየት መጀመሪያ ራሷ በኋላ በዓረብ ሊግ አይዞሽ ባይነት ቱኒዚያን በመጠቀም ጉዳዩን ከአፍሪካ ኅብረት በማውጣት ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳነት ለማሳደግ ያደረገችው ጥረት ሀገራችን በጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ዲስፕሊንና በጥበብ በተመራ ዓለማቀፍ ግንኙነት ሀገራትን ከጎኗ በማሰለፍ የተደገሰላት ደባ እንዲከሽፍ ከማድረጓ ባሻገር የግድቡ ጉዳይ የተፋሰሱ ሀገራትና የአፍሪካ ኅብረት እንጂ የመንግሥታቱ ድርጅት አለመሆኑን ማረጋገጥ ችላለች።

ድርድሩም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ኅብረት ተመልሷል። ምንም እንኳ ግብፅና ሱዳን ሰበብ አስባብ እየደረደሩና ፍላጎታቸውን በሌላ መንገድ ለማራመድ ላይ ታች እያሉ ቢሆንም። ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈው የነበሩ ምዕራባውያንም እርማቸውን እንዲያወጡ አድርጋለች። ሆኖም ዛሬም ሆነ ጥንት ግብፅ አልተኛችልንም። ዓባይን ከመነሻው ለመቆጣጠር ከ11 ጊዜ በላይ ልትወረን ልታስገብረንና ቅኝ ልትገዛን ሞክራ እንዳልተሳካላት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። በዲፕሎማሲው መድረክ ብትረታም በሱዳን አማካኝነት የውክልና ጦርነት ከፍታ መሬታችንን አስወርራለች። ሀገርን ለከዱ ጡት ነካሾች የገንዘብ የጦር መሣሪያ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ለየለት ቀውስና ትርምስ ለመክተት ቀን ከሌት እየሠራች ነበር።

ግድቡ በአሁኑ ሰዓት በአስር ቢሊዮኖች የሚገመት ሜትር ኩብ ውሃ የያዘ ሲሆን እስከ መጭው ታኅሣሥ 70 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመያዝ ራሱን መከላከል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ግብፅ ለዘመናት ኢትዮጵያ ሠላም ሆና አንድነቷ የሚጠናከርና ልማቷም የሚፋጠን ከሆነ ዓባይን ጨምሮ ገና የውሃ ሀብቷን ታለማለች በሚል በስጋት ላይ ያነጣጠረ ስጋት ከውስጥ ተላላኪዎቿ ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያንን ለመበታተን ሠርታለች። ሆኖም የግብፅና የተላላኪዎቿ የቀን ቅዠት በጀግኖች ልጆቿ ይመክናል። እየመከነም ይገኛል። በዚህም ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነፃነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ በብልፅግና ለመድገም ጉዞዋን ጀምራለች። በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ (ፍላግሺፕ) ፕሮጀክት ባለቤት መሆን ችላለች ።

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እንዳሉት፤ በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልምና። ስንዴ እየለመኑ፣ እየተመፀወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች፤ በነፃነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ብሎ መመጻደቅን ድሉን ሙሉኡ አያደርገውም። ሆኖም የመጀመሪያው፣ የሁለተኛው፣ የሦስተኛውና የአራተኛው የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት፤ 2ኛው ዩኒት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የቀጣናውን ጂኦፖለቲክስ እንደ አዲስ በይኖታል። የግብፅን የውሃ ዲፕሎማሲና ፖለቲካም ከንቱ አድርጎታል። ሆኖም ከዚህ ትልቅ ስዕል ዓይንን ለማንሳት የሚያስገድዱ ጦርነቶችና ቀውሶች በሠላም እንዲፈቱ ጎን ለጎን ጥረት ሊደረግ ይገባል። ሠላም በሌለበት የተሟላና የተሳካ ልማት ማረጋገጥ ያዳግታልና።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በአንድ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፤ ከግድብ በላይ ተምሳሌታዊ የሆነ፣ የለውጡ አሻራ፤ የትውልዱ ርብርብ ዳና በጉልህ ያረፈበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግድብ ያለፈ የትውልድ ዐሻራ ያረፈበት፤ ለኢትዮጵያውያን ከኃይል ማመንጨትም በላይ ፋይዳው የጎላ፤ ግንባታው ለይቻላል መንፈስ መሠረት የጣለ፤ በአሁኑ ወቅት ግድቡ ሕዝቡ ባሳየው ቁርጠኝነት እና ተሳትፎ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ያበሰረ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በመተባበር እንደ አንድ ሀገርና ሕዝብ በመሆን ድል የተደረገበት መድረክ የዓድዋ ድል ነው:: በወቅቱ የዘመቱት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ተዋግተውም ማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ ታላቅ ድልና እና ዛሬም ድረስ የሚዘከር ገድል መሆን ችሏል:: ዓባይ ግድብም በተመሳሳይ በመላው ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባ አኩሪ ገድል ነው።

ግድቡ ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ አንድምታ ያለው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ እንዳታድግ ለሚጥሩ ኃይሎች ወሽመጣቸውን የቆረጠ ታላቅ ገድል ነው። የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ ሀገራት ቀድሞ ይዘው በቆዩት ያረጀ ያፈጀ አቋም ሊቀጥሉ ይፈልጋሉ:: ይሁንና ልክ የአንድነት ተምሳሌት እንደሆነው ዓድዋ አንድ መሆን ሲቻል በትብብር የማይገረሰስ ነገር አይኖርም:: በትብብር ውስጥ መሆን ጠላትም ሆነ ሌላ ፈተና ከፊት ለፊት እንዳይቆም የሚያደርግ ነው:: የህዳሴ ግድቡንም በተባበረ ክንድ እዚህ ማድረስ የተቻለ በመሆኑ ማንም ወደ ኋላ ሊመልሰው አይችልም ::

በመላው ሕዝብ ጥረት ከለውጡ በኋላ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ከወትሮው አይሎ መቀጠሉን ገልጸው፤ ለግድቡ እየተበረከተ ያለው አስተዋፅዖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን፤ ግድቡን ለማጠናቀቅ እስከ አሁን ገቢ እየተሰባሰበ ያለው በቦንድ ሽያጭ፣ በ8100 A አጭር የጽሑፍ መልዕክት አማካኝነት እንዲሁም በደረት ላይ የሚደረግ ፒን በመሸጥ ሲሆን፤ ድጋፉ አሁንም ቀጥሏል ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ለግድቡ ግንባታ የሚሰበሰበው ገንዘብ በየዓመቱም እየጨመረ መጥቷል። ለአብነት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት 8100 A ላይ በሚደረጉ ድጋፎች አማካኝነት በአንድ ወር ውስጥ እስከ 13 ሚሊዮን ብር ድረስ መሰብሰብ ተችሏል። መላው ኢትዮጵያዊ ለህዳሴው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You