ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ሚዲያ እንደ አራተኛ መንግሥት ይቆጠራል ይሉታል። ይህ ማለት በየትኛውም አቅጣጫና መስፈርት ዘርፉ ታላቅ ኃይልና ጉልበት አለው ማለት ነው። የእኛ ሀገር የሚዲያ ታሪክ እንደአደጉት ሀገራት በልቀት ተራምዷል የሚባል አይደለም። ‹‹የእኛ ሚዲያ ጊዜውን በዋጀ መንገድ የአቅሙን ያክል ሲተጋ ቆይቷል›› የሚሉ ግን አይጠፉም።
የእነሱ ሀሳብ የሚከበር ሆኖ እንደ አጠቃላይ ግን ‹‹ድንቅ›› የሚያስብል ፈጣን ጉዞ ላይ አለመሆናችንን ልብ ይሏል። ሚዲያችን አይደለም ከምዕራባውያኑ ጎራ ከጥቂት አቻ አፍሪካ ሀገራት ጋር ለመወዳደር ብዙ እንደሚቀረው አሳምረን እናውቃለን። እስከዛሬ ያሉና የሚታዩ ለውጦች እንዳሉ ሆኖ ብዙ የሚጎድሉን እውነታዎች አሉና።
በቅርቡ በሀገራችን የመጀመሪያው የተባለለት የሚዲያ አዋርድ ሲካሄድ ቆይቶ ከቀናት በፊት ተጠናቋል። ይህ ውድድር እስካዛሬ ያልታሰበና የመጀመሪያ መሆኑ ብዙዎች በመልካም እይታ ተቀብለውታል። ይህ በጎነት እንዳለ ሆኖ በውድድሩ ላይ ከጅማሬው እስከፍጻሜው ሲስተዋሉ የቆዩ ችግሮች ያለአንዳች ዕርማት ቀጥለው ለፍጻሜ በቅተዋል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ በርካቶችን አስገርሟል፤ አሳዝኗልም። ብዙዎቹ እንዳሉት ሰፊና ግዙፉን ‹‹ሚዲያ ይሉትን ተቋም ይዘው ውድድርን ያስጀመሩ አካላት አስቀድመው ትልማቸውን የለዩ አይመስልም።
ገና ከጅማሬው በተለያዩ ዘርፎች በዕጩነት የቀረቡ ሚዲያዎችንና ባለሙያዎችን በአግባቡ ለይተው ያቀረቡ አልነበሩም። ጥቂት ቆይተው ስህተትን ለማረም የሞከሩ ቢሆንም በግልጽ ከተረጋገጠ ወቀሳና ቅሬታ ግን መዳን አልተቻላቸውም።
አሁን ባለንበት ዘመን በርካቶች ሚዲያው ላይ ያላቸው አትኩሮትና ልማድ እየሳሳ መሄዱ ይታወቃል። ለዚህ ጥቂት ማሳያዎችን መጥቀስ ቢቻልም በዋንኛነት ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ እንደምክንያት ይነሳል። እነዚህና ሌሎች እውነታዎች ተደራርበው ባሉበት አጋጣሚ ሚዲያውንና ዘርፉን የሚዘውሩ ባለሙያዎችን አክብሮ ዕውቅና ለመስጠት መንቀሳቀስ ታላቅ ምስጋናን የሚያስቸር ነው።
ወደዋናው ጉዳያችን እንመለስ። ወደሰሞኑ የሚዲያ አዋርድ ውድድርና ፍጻሜ። ይህ ውድድር ከጅማሬው ሲነሳ የዕጩዎች መስፈርትና ልዩነትን በወጉ የለየ እንዳልነበር ይወሳል። ለዕጩነት ከቀረቡ ባለሙያዎች የተመረጡ ሥራዎች በተለይ በኅትመቱ ዘርፍ ግዜ ተወስዶ ጥናት የተደረገባቸው አልነበሩም።
ለዚህ አንድ ማሳያን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ በመጀመሪያው ዙር ለዕጩነት ከቀረቡ የአርቲክል ጽሑፎች መካከል ምርጫን አግኝቷል የተባለ አንድ ሥራ የተለየው በክፍል ሁለት ላይ ከወጣው ጽሑፍ ተገንጠሎ ነበር። እንደተባለው በቂ ጥናትና ግዜ ተወስዶ ቢሆንማ የመረጣው አካል ክፍል አንድ ላይ የቀረ የመነሻ ታሪክ ስለመኖሩ በጠረጠረ ነበር።
በተመሳሳይ በእንግሊዝኛው የኅትመት ዘርፍ ከአማርኛው ጋዜጣ በትርጉም የተመለሰ አንድ ሥራም ለዕጩነት ቀርቦ እንደነበር በዙሪያው የነበሩ ባለሙያዎች ያውቁታል። በቂ ጥናት ቢደረግ ደግሞ ሌሎችም እውነታዎች ሊፈለፈሉ ይችላሉ። በሦስት የተለያዩ ጊዜያት ሲካሄድ የቆየው ድምፅ መስጠት የበዛ ቴክኒካዊ ችግሮችን ያስተናገደ ነበር። ለዚህ ግልጽ ችግር ደግሞ አዘጋጆቹ ለአንድ ግዜ እንኳን ይቅርታ የጠየቁበት አጋጣሚ አልነበረም። ይህ ደግሞ ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ መላውን ተሳታፊ እንዳለማክበር ይቆጠራል።
ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሳ የሁለተኛውን ዙር ቆይታ አለመጥቀስ አይቻልም። ለድምፅ መስጫ ሲሉ ያዘጋጁት ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ፍጹም ውስብስብና እጅግ አስቸጋሪ ነበር። ይህ ታውቆ ጥቆማ በደረሳቸው ግዜ ጆሮ ዳባ ማለታቸውና ከሰጡት የጊዜ ገደብ ያለማስጠንቀቂያ ቀድመው ጊዜውን ማቋረጣቸው ከትዝብት ያለፈን ጊዜ አስተናግዷል። ለዚህኛውም ድርጊት አዘጋጆቹ ደንታ ቢስነታቸው ግልጽ ነበር።
በዚህ ውድድር በየጊዜው መረጃ አለመስጠትን ጨምሮ ሲስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች ብዙ ናቸው። ድምፅ አሰጣጡ አሰልቺና ረጅም ቆይታን አስተናግዷል። ይህን እውነታ ለራሳቸው እንተወውና ወደመጨረሻው ቀን የሽልማት ግዜ እንመለስ።
በሦስት ተከፍሎ በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ እስከ ሁለተኛው ዙር ሁሉም ተወዳዳሪ በግልጽ ውጤቱን ሲመለከትና ርስ በርስ ሲፎካከር ቆይቷል። ሦስተኛውና የመጨረሻው ዙር ግን በስልክ መልዕክት ድምፅ መስጠት ላይ ያተኮረ ነበር።
ይህኛው ውድድር ብዙዎቹ ሲሉት እንደነበረው መስፈርት ማሟያ ሳይሆን ገቢ ማስገኛ ብቻ ነበር ሲባል ከርሟል። ለአስር ቀናት ሲቆይም ያለ አንዳች የቴክኒክ ስብራትና ዕንቅፋት ነው። ከዚህ አኳያ ብዙ መታማቱ ደግሞ ፈጽሞ አያስደንቅም። በሂደቱ የማንም ድምፅ በግልጽ የሚነበብ አልነበረምና አሸናፊና ተሸናፊው አልተለየም። በዚህ መነሻ ብዙኃኑ የጠበቀው አስቀድሞ የተያዘውን ውጤት ነበር። መጨረሻው እንዳልነበረ ቢሆንም።
በውድድሩ ዜና አንባቢዎች በሚል ብዙዎች ተሳትፈዋል። ለመሆኑ ዜና ማንበብ ችሎታ ውበት፣ ሙያ ወይስ ሌላ እስከመባል ቢያደርስም። በተመሳሳይ በቴሌቪዢን ለማንበብ ብቻ የሚመጡና በሌላ መሥሪያቤት የሚሠሩ የትርፍ ጊዜ ተከፋዮች ጭምር የጋዜጠኝነት ካባ ተደርቦላቸው በውድድሩ ተካፍለዋል። በዚሁ የሚዲያ ዘውግ ዲጄዎችም ተሳታፊና ተሸላሚዎች ነበሩ። ይህ ሙያዊ ቅርበት በራሱ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም ምላሽም ሆነ ማብራሪያ አልተሰጠበትም።
በስፖርት ጋዜጠኝነት ዘርፍ ደግሞ የባለሙያው ችሎታ ሌላ ጉዳይ ቢሆንም አጠቃላይ ስፖርቱን የሚሸፍን ሽልማት አልተሰጠም። አሸናፊው ‹‹እኔ የእግር ኳስ ብቻ እንጂ የአጠቃላይ የስፖርት ጋዜጠኛ አይደለሁም›› ብሎ እየመሰከረ ሽልማቱ ይገባሃል ተብሏል። እዚህ ላይ የሀገር ውስጥ ስፖርት ዘገባን ጨምሮ አጠቃላይ ሙያዊ ዕውቀቱ ያላቸው ወጣትና አንጋፋ ጋዜጠኞች መዘንጋታቸውን ልብ ይሏል።
በውድድሩ ተሳትፎ የነበራቸው በርካታ ጋዜጠኞች ከመጀመሪያ ዙር በኋላ እንዳይወዳደሩ ገደብ ተጥሎባቸው ሂደቱን አቋርጠዋል። በተመሳሳይ ግን በአንድ ተቋም ሙያውን የሚጋሩ ባልደረቦቻቸው ያለአንዳች ገደብ ተወዳድረው እንደውም ለሽልማት ጭምር በቅተዋል። እንዴትና ለምን የሚል አወዳዳሪ በሌለበት ደግሞ ሚዛናዊ ፍርድ የሚጠበቅ አይሆንም ።
በሽልማቱ ብዙዎች እንደታዘቡት እስከ ሁለተኛው ዙር እጅግ አነስተኛ የሚባል ነጥብ ያስመዘገቡና በከፍተኛ የቁጥር ልዩነት የተመሩ ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ተብለው ተሸልመዋል። እንደውም አንዳንዶቹ ሁለቱንም ዙር በአግባቡ ያላሟሉና በቂ ተሳትፎና ቆይታ ያልነበራቸው እንደሆኑ ታውቋል።
አስገራሚው ጉዳይ በኅትመቱ ዘርፍ ምርጥ አርቲክል ተብሎ የተመረጠው በእንግሊዝኛ የተጻፈው ገጽ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ አርቲክል ምንድነው የሚለው እውነታ ሳይዘነጋ የተመረጠውና በውጭ ቋንቋ የቀረበው ሥራ ምን ያህሉ አንብቦ ተረድቶታል? የሚለውን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። ይህ ሲታሰብ ደግሞ አርቲክሉን በውጭና በሀገር ውስጥ ቋንቋ በመለየት ማወዳደሩ ተገቢ በሆነ ነበር።
በመጨረሻው ቀን በመድረክ ላይ የነበረው ቆይታም አዘጋጆቹን ግልጽ ከሚባል ትዝብት የጣለ ነበር ለማለት ያስደፍራል። አብዛኞቹ ተሸላሚዎች ከአንድ ሚዲያ በርከት ያሉ መሆናቸው ተስተውሏል። አንዳንዶቹም ልዩ ቅርበታቸውን ለማሳየት ሽልማቱን ሲቀበሉ ለምስጋናው ጓደኛዬ፣ ወዳጄ በማለት ሲሞከሻሹ ተደምጠዋል።
በመጨረሻም ሽፍንፍን በሆነው የስልክ መልዕክትና በዳኞች ውሳኔ አሸንፈዋል የተባሉ ተወዳዳሪዎች ለሽልማት መብቃታቸው ታየ። ከዚህ ቀድሞ በሁለት ዙሮች ከፍተኛ የሕዝብ ድምፅ የነበራቸው ተወዳዳሪዎች ውጤት ግን የት እንደደረሰ አልታወቀም። አሁንም ማብራሪያና አስተያየት አልተሰጠበትም።
‹‹እኛን ብቻ ስሙን፣ እመኑን›› ይሉትን ፍጻሜ በራስ ሀሳብ ማወጅ ተገቢ ባይሆንም እንዲህ ተደርጎ የመጀመሪያው የሚዲያ አዋርድ ፍጻሜ ተጠናቋል። ዳግም በሁለተኛ ዙር እንመለሳለን የሚሉን አዘጋጆች እነዚህን በወፍ በረር የተጠቀሱ ጥቂት አስተያየቶችን ተግባራዊ ቢያደርጉ አይከስሩም፣ አያፍሩም። ከትክክለኛው ሙያዊ ሚዛን ላይ ያርፋሉ እንጂ።
ከታዛቢው ዓይኖች
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም