በክብረወሰን የታጀበው የሲምቦ ዓለማየሁ ድል

በፓሪስ ኦሊምፒክ ከተሳተፉ አትሌቶች መካከል 50 የሚሆኑት 20 ዓመት ያልሞላቸው ወጣቶች ነበሩ። እነዚህ ወጣቶች በታላቁ መድረክ ድንቅ ብቃትና ተስፋ አሳይተው ፊታቸውን ወደ ሌላ ዓለም አቀፍ ውድድር አዙረዋል። ከእነዚህ ወጣት አትሌቶች መካከል 24 የሚሆኑት ከኦሊምፒኩ ማግስት በዕድሜ እርከናቸው በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከእኩዮቻቸው ጋር በፔሩ ሊማ እየተፎካከሩ ይገኛሉ። ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ዛሬ ሲጠናቀቅ ተስፋ የተጣለባቸው ወጣት ከዋክብት አስደናቂ ብቃት አሳይተዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በወጣቶች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከመካሄዱ አስቀድሞ 6 አትሌቶች ልዩነት ፈጣሪ እንደሚሆኑ የዓለም አትሌቲክስ ግምቱን አስቀምጦ ነበር። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል በመጀመሪያ የተጠቀሰችው ኢትዮጵያዊቷ የ3ሺ መሰናክል ተወዳዳሪ አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ ናት። ከትናንት በስቲያ በርቀቱ በተደረገው የፍጻሜ ውድድርም ይህንኑ ግምት ዕውን ያደረገ ብቃት በማሳየት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። አትሌቷ የሻምፒዮናውን ክብረወሰን በማስመዝገብ እንዲሁም በመድረኩ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት አሸናፊ በመሆንም የድርብ ክብር ባለቤት ሆናለች።

በኤሊት ራኒንግ ቲም የምትሠለጥነው ሲምቦ የ19 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት ካሊ ላይ በተካሄደው የወጣቶች ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ ነበር በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ስኬታማ ጉዞዋን የጀመረችው።

ከዚያ በኋላ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የሄንግሎ የዙር ውድድር ላይ 9:18.98 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ከ18 ዓመት በታች ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። ተስፈኛዋ አትሌት ቀጣዩን ተሳትፎዋን ያደረገችው በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ሲሆን፤ ርቀቱን 9:09.19 በሆነ ሰዓት በመሸፈን ሰዓቷን በድጋሚ አሻሽላለች። ይኸውም በኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድጋሚ ሃገሯን ወክላ እንድትሳተፍ አድርጓታል። በታላቁ የአትሌቲክስ መድረክ የነበራትን መጀመሪያ ተሳትፎ እንዲሁም የውድድር ዘመኑን 5ኛ ደረጃን በመያዝ በዲፕሎማ ነበር ያጠናቀቀችው።

ተስፈኛዋ አትሌት እአአ የ2023 ውድድር ዓመትን በዶሃ ዳይመንድ ሊግ ስትጀምር ኬንያዊቷን ባትሪስ ቼፕኮች ተከትላ ነበር የገባችው። በወቅቱ 9:05.83 በመሮጥ ለግሏ ፈጣን ሰዓትን ስታስመዘግብ በየጊዜው ያላትን ፈጣን መሻሻልም አስመስክራበታለች። ከአንድ ወር በኋላም የፍሎረንስ ዳይመንድ ሊግ ተሳትፎዋን 9:00.71 በሆነ ሰዓት በመግባት የቦታውን ክብረወሰን እንዲሁም የራሷን ፈጣን ሰዓት በድጋሚ ማሻሻል ቻለች። ይኸውም ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድትወክል አስችሏታል። ቡዳፔስት ላይ በነበረው ውድድርም ማጣሪያዎቹን በጥሩ ውጤት በማለፍ ለፍጻሜ ብትበቃም ባልተጠበቀ ሁኔታ 13ኛ ደረጃን በመያዝ ልታጠናቅቅ ችላለች።

በርቀቱ ባላት ሰዓት ከዓለም 6ኛዋ ፈጣን አትሌት የሆነችው ሲምቦ በቅርቡ በተካሄደው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሃገሯን ለመጀመሪያ ጊዜ ወክላ መመረጧ የሚታወስ ነው። በመድረኩም ልምድ ካላቸው አትሌቶች ጋር ተፎካክራ የዲፕሎማ ባለቤት መሆኗን ባረጋገጠች በቀናት ልዩነት ደግሞ በወጣቶች ሻምፒዮኗ ኢትዮጵያን ለመወከል ችላለች። አስቀድሞ እንደተሰጣት ግምትም ውድድሩ በድንቅ አቋም ተፎካካሪዎቿ ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስዳ ልታሸንፍ ችላለች። የሮጠችበት 9:12.71 የሆነ ሰዓትም (ከቀድሞው የ7 ሰከንዶች የፈጠነ) የሻምፒዮናው ክብረወሰን ሲሆን፤ በርቀቱ ሁለት ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ቀዳሚዋ ኢትዮጵያዊት አትሌትም ሆናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬሕይወት ገሰሰ ደግሞ 9:34.50 በሆነ ሰዓት በመሮጥ 4ኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች። በዚህም ትናንት ምሽት የተካሄዱ ውድድሮችን ሳይጨምር ኢትዮጵያ 2 የወርቅ እና 2 የብር ሜዳሊያዎችን በሻምፒዮናው በማስመዝገብ በቀዳሚነት ተቀምጣለች።

በወንዶች በኩል በተደረገው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ደግሞ አትሌት ይበልጣል ጋሻው 4ኛ እንዲሁም አትሌት ገብሩ አብርሃ 8ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። ትናንት ምሽትም የሴቶች 10ሺ ሜትር ርምጃ ሲካሄድ፤ እኩለ ሌሊት ላይ ደግሞ የወንዶች እና ሴቶች 800 ሜትር እንዲሁም የሴቶች 3ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You