የሴካፋ ዞን የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ባለፉት አራት ዓመታት ሲካሄድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ ቢሆንም በሁለቱ ዋንጫ ማሳካት አልቻለም ነበር። ዘንድሮ ግን ለሦስተኛ ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚ ሆኖ በቀረበበት ፍልሚያ የዞኑን ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት በቅቷል።
ለአራተኛ ጊዜ ከነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የሴካፋ ዞን የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ትናንት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም ተጠናቋል። በፍፃሜው ፍልሚያ በሜዳውና በደጋፊው የኬንያ ፖሊስ ቡሌትን የገጠመው ንግድ ባንክ ጨዋታውን አንድ ለምንም በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።
ከማራኪ የጨዋታ ብልጫ ጋር ዋንጫውን ለማንሳት የተፎካከሩት ንግድ ባንኮች ያገኙትን የግብ አጋጣሚ መጠቀም ሳይችሉ ቢቆዩም፣ 78ኛው ደቂቃ ላይ በአስደናቂ ቅብብል በኮከቧ ሴናፍ ዋቁማ ግሩም አጨራረስ ታግዘው ኳስና መረብ አገናኝተዋል። ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረችው ሴናፍ ዋቁማም በስድስት ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆና አጠናቃለች። የአማካኝ ስፍራ ተጫዋች መሳይ ተመስገን ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ሆና ተመርጣለች። ይህም ንግድ ባንክን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴካፋን የክለቦች ዋንጫ ከማንሳት ባለፈ የሴካፋን ዞን ወክሎ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ አድርጎታል። የውድድሩ ኮከብ አሠልጣኝ የኬንያ ፖሊስ ቡሌትስን ለፍፃሜ ያበቃችው ቤልዲን ኦዴምቤ ሆና ስትመረጥ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂም ከተመሳሳይ ክለብ ኤ ኩንዱ ተመርጣለች።
ዘጠኝ ክለቦች በሁለት ምድብ ሲፎካከሩበት በቆየው ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፎ ነበር ለፍጻሜው ፍልሚያ መብቃት የቻለው። በምድብ አንድ ሦስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሮ ሦስት ብቻ ሲቆጠሩበት የግማሽ ፍጻሜውን ጨዋታም በሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች አስቆጥሮም አስደናቂ ጉዞ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በ2013 ዓ.ም ኬንያ ባስተናገደችው የመጀመሪያው ውድድር ላይ 2ኛ፣ በ2014ቱ የታንዛኒያ ውድድር ላይ ደግሞ 3ኛ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ዑጋንዳ ላይ ተደርጎ በነበረው ውድድር 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ንግድ ባንክ በነዚህ ዓመታት በውድድሩ አስደናቂ ጉዞው የፍፃሜ ተፋላሚ ሲሆን ቡድኑን በዋና አሠልጣኝነት የመራው ብርሃኑ ግዛውም በመጨረሻም ዋንጫውን በማንሳት አዲስ ታሪክ ሠርቷል።
ክለቡ ከዚህ ቀደም እአአ በ2021 ውድድሩ በተጀመረበት የመጀመሪያ ተሳትፎ ለፍጻሜ ደርሶ ባለቀ ሰዓት በተሰጠበት የፍጹም ቅጣት ምት በኬንያው ቪጋ ክዊንስ ተሸንፎ ዋንጫውን ማንሳት እንዳልቻለ ይታወሳል። አምናም በተመሳሳይ በዑጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው ውድድር ለፍፃሜ ቀርቦ በታንዛኒያው ጄኬቲ ኩዊንስ በመለያ ምት ተሸንፎ ከዋንጫ ውጪ መሆኑ ይታወቃል። ከፍፃሜው ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በተካሄደው የደረጃ ጨዋታ የዑጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ የታንዛኒያውን ሲምባ ኩዊንስን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ውድድሩን በሦስተኛነት አጠናቋል።
የሴካፋ ዞንን በመወከል በአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍ አንድ ቡድን ለመለየት ዘጠኝ ቡድኖች በሁለት ምድቦች ተከፍለው ውድድራቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የዋንጫው አሸናፊ ቡድንም የሴካፋን ዞን ወክሎ በ2024 የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የሚሳተፍ ይሆናል። በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች የሚገኙ የሴት ቡድኖች የማጣሪያ ውድድር ካደረጉ በኋላ ዞኖቻቸውን በመወከል የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይካፈላሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/ 2016 ዓ.ም