
ዜና ትንታኔ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ከትናንት በስቲያ መግለጫ አውጥቷል። መግለጫውም በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሠላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል ይላል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚሁ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት፣ ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል የሚለው መግለጫው፤ በሁኔታው ላይ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ ወታደር ያዋጡ አገሮች ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም ነው ያለው፡፡
የመከላከያ ሠራዊታችንን መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ ተከታታይ መግለጫዎች ሲወጡ ኢትዮጵያ በዝምታ እንድታልፍ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ፍላጐት መኖሩ እንደሚታይ መግለጫው ጠቅሶ፤ ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም፡፡ ይህም በመሆኑ በቀጣናው የብሔራዊ ደኅንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች ትገኛለች ሲል መግለጫው ያብራራል፡፡
ኢትዮጵያ ለሶማሊያና ለአካባቢው ሠላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ያለውን ወቅታዊ አለመግባባት ለመፍታት እንዲያስችል በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይም በንቃት ተሳትፎ አድርጋለች የሚለው መግለጫው በእነዚህ ንግግሮች ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል። የሶማሊያ መንግሥት እነዚህን ሠላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡
በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሠላም ተልዕኮ የማዘጋጀት እና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ በቀጣናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ ሃገራትን ተገቢ የሆኑ ስጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እና ከንቱ ዓላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸውን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም ሲልም መግለጫው ያስጠነቅቃል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ሰነድ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ከሶማሊላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል፡፡ ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሶማሊያ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ከማውራት ይልቅ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በጉዳዩ መምከርና መፍትሔ ባይሆንም ማስፈራራትን መርጣለች፡፡
የሶማሊያ ባለሥልጣናት አልሻባብን እየተዋጋ ከ15 ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ የሶማሊያና የኢትዮጵያ ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ሀገሪቷ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራች ነው፡፡
ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራች መሆኗ ለኢትዮጵያ ምን ስጋት አለው? ቀጣይ የኢትዮጵያ የቤት ሥራ ምን መምሰል አለበት? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ምሑራን ሀሳባቸው አካፍለውናል፡፡ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ቦጋለ እንደሚገልጹት፤ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ባላንጣ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር የጀመረችው የተለየ ግንኙነት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ሠላም አስበው ስለማያውቁ ጥንቃቄና ትኩረት ይፈልጋል፡፡
ከጥንት ዘመን ጀምሮ በተለያየ አግባብ ኢትዮጵያን ያዳክማል የሚሉትን አካሄድ ሲከተሉ የቆዩ መሆናቸውንም ረዳት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ገልጸዋል፡፡ በሶማሊያ ጋባዥነት ወደ ቀጣናው እየገቡ ያሉ እነዚህ የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄን ለማዳፈን እየሠሩ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ በአንጻሩ ሶማሊያ ለበርካታ ዓመታት ችግር ሲገጥማት ከችግሯ ለማላቀቅ እነዚህ ኃይሎች ምንም አይነት ድጋፍ ሲያደርጉ አልታዩም ያሉት ምሑሩ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ሶማሊያ እንድትረጋጋ አድርጋለች ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
እስካሁን ድረስ የሶማሊያ ችግር ያልታያቸው ኃይሎች ዛሬ ለምን ጉዳዩ እንደሳባቸው ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ የገዘፈ ባይሆንም ስጋት ስላለው ጥንቃቄና ትኩረት ይሻል ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይ በምትሠራቸው የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ፣ ኢኮኖሚና ወታደራዊ ሥራዎቿ አዲሱን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አካሄድ ትኩረት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ ያስገድዳልም ብለዋል፡፡
በተለይ የተለያዩ የሶማሊያ ልሂቃንን በመጠቀም ወደሚፈልጉት አጀንዳ የማምጣት እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቅሰው፤ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያንና የሶማሊላንድን የባሕር በር ስምምነትን ተከትሎ እነዚህ ኃይሎች ከማንኛውም ሀገር ቀድመው የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላንጣዎች ከአልሸባብ ጋር ተስማምቶ መሥራት አይችሉም የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ምክንያቱም ሁለቱ የማይታረቁ ሀሳብ ያላቸውና አብረው ሊሠሩ የማይችሉ አካላት ናቸው ባይ ናቸው፡፡ ሶማሊያን ለማረጋጋት የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ተቋማት በተለይ ወታደራዊ፣ ፖሊስና በየአካባቢው ያሉ የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲጠናከሩ እነዚህ የውጭ ኃይሎች አንዳችም ፍላጎት የላቸውም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ሞቃዲሾ ላይ ቁጭ ብሎ የእነዚህ ኃይሎችን አጀንዳ የሚያስፈጽም አካል እስካለ ድረስ ቤተመንግሥቱን ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በሻገር እንደ ኢትዮጵያ መስዋዕትነት ከፍሎ በሰፊው የሶማሊያ አካባቢ ሠላም እንዲመጣና አስፈላጊ ሲሆን አሸባሪዎችን የሚዋጋ አካል አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የአካባቢ አስተዳደሮችን መደገፍና ሕዝቡ ሲቸገር የራሱን ምግብ አካፍሎ የኖረ ነው፤ ይህን የሚያደርግ ሌላ አካል እንደማይኖር በመግለጽ፤ ሶማሊያ አካሄዷን መፈተሽ እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያ ጎረቤት በመሆኗ በሶማሊያ የሚነድ እሳት በቀጥታ ወላፈኑ ኢትዮጵያን ይጎዳል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ኃላፊነትም ስለሚሰማት ለሶማሊያ መረጋጋት አስፈላጊውን ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ አሁን የሶማሊያ ሉዓላዊነት ያሳስበናል የሚሉት ኃይሎች በኢትዮጵያ ልክ ተንቀሳቅሰው የሶማሊያን ሠላምና ደኅንነት የማስከበር ፍላጎትም ሆነ ተነሳሽነት የላቸውም፡፡ ድንበር ተጋሪም አይደሉም፤ የጋራ ታሪክ የላቸውም፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ከታሪካዊ ግንኙነት ባሻገር የሶማሊያ ችግር በቀጥታ ስለሚጎዳት ለሠላም መስፈን ብዙ ዋጋ ከፍላለች ነው ያሉት፡፡
እነኝህ ኃይሎች በኢትዮጵያ ልክ በኃላፊነት የፖለቲካና የፀጥታ ሥራ ሊሠሩ አይችሉም ያሉት ተመራማሪው፤ ሶማሊያ ጉዳዩን በአፅንዖት ማየት አለባት፡፡ ችግሩ ሞቃዲሾ ላይ ያለው የሶማሊያ መንግሥት ይህን መረዳት አይፈልግም፡፡ በጊዜያዊ ስሜት በመነሳሳት ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መነጋገር መግለጫ መስጠትና መሰል እርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር ስለ ሶማሊያ ዘላቂ ጥቅምና ሠላም እያሰበ አይደለም ብለዋል፡፡
አንዳንድ የአካባቢ አስተዳደሮች የእነዚህ የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ሶማሊያን መርዳት፣ እንድትረጋጋ ማድረግ ሳይሆን ነገር ፍለጋ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሚጎዳው የሶማሊያን ሕዝብ መሆኑን ስለሚገነዘቡ የኢትዮጵያ ወታደር ከሶማሊያ መውጣት የለበትም፤ እነዚህ ኃይሎች እንዲመጡብን አንፈልግም የሚሉ ድምፆችን እያሰሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/ 2016 ዓ.ም