በፔሩ ሊማ ካለፈው ማክሰኞ ምሽት አንስቶ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ሦስት ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች።
የአትሌቲክሱ ዓለም የመጪው ዘመን ኮከብ ወጣቶች አቅማቸውን በሚያሳዩበት በዚህ ውድድር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለት ውድድሮች ሦስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ማንፀባረቅ ችለዋል።
በሴቶች 5ሺ ሜትር በተደረገው የፍጻሜ ውድድር አትሌት መዲና ኢሳ ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ኢትዮጵያ በውድድሩ የደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚውን ስፍራ መቆናጠጥ ችላለች። ወጣት ኮከብ መዲና ከፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ማግስት በወጣቶቹ ቻምፒዮና 5ሺ ሜትር በአስደናቂና አሳማኝ ብቃት ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቃለች።
ከቻምፒዮናው መካሄድ አስቀድሞ የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው ቅድመ ግምት በፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገራቸውን ወክለው የተሳተፉና በዚህ ቻምፒዮና በድጋሚ ተካፋይ የሆኑ አትሌቶች አሸናፊ የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን አትቶ ነበር። እንደተጠበቀውም መዲና በዚህ ዕድሜዋ ሀገሯን በተደጋጋሚ በታላላቅ መድረኮች ማኩራት የቻለች ወጣት አትሌት ሆናለች። ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው 19ኛው የወጣቶች ቻምፒዮና በዚሁ ርቀት አሸናፊ ነበረች። አትሌቷ በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮናም ሀገሯን ወክላ በግሏ እና በቡድን አንድ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ ከማጥለቅ ባለፈ በአፍሪካ ጨዋታዎችም በበላይነት ነበር ያጠናቀቀችው።
በርቀቱ ያላት ፈጣን ሰዓት ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ያበቃት ሲሆን፤ ካለችበት ዕድሜ አንጻር አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጓ የሚታወስ ነው። በሳምንታት ልዩነትም በድጋሚ በወጣቶች ቻምፒዮና በአስገራሚ አሯሯጥ የሀገሯን ልጅ አስከትላ በመግባት ኢትዮጵያ በርቀቱ የወርቅና ብር ሜዳሊያ ባለቤት እንድትሆን አስችለዋል።
ተስፈኛዋ መዲና ውድድሯን ለመሸፈን 14:39.71 የሆነ ሰዓት ሲፈጅባት በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ እአአ ከ2010 ጀምሮ ተይዞ ከቆየው የውድድሩ ክብረወሰን በ28 ሰከንዶች የፈጠነም ነው። ፈጣን በነበረው ሩጫ መዲና ተፎካካሪዎቿን በሰፊ ልዩነት አስከትላ በመሮጥም በርቀቱ ለወደፊት ያላትን ተስፋ ስታሳይ፤ ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ከነበራት የ5ሺ ሜትር የሴቶች ተሳትፎ ስምንተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ውጤታማነቱን ልታስቀጥል ችላለች።
መዲና ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየትም ‹‹ከኦሊምፒክ በኋላ በዚህ ቻምፒዮና ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር በማሸነፌ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ለወራት በዚህ መንገድ ቻምፒዮን ለመሆን ነበር ስዘጋጅ የቆየሁት›› በማለት ገልጻለች። በውድድር የአሸናፊነት ግምት ከማግኘት ባለፈ የመዲና ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ በሚል ከተገመቱ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው አትሌት መቅደስ አለምሸት ደግሞ የብር ሜዳሊያውን ማሳካት ችላለች። ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ የፈጀባት ሰዓት 14:57.44 ሲሆን፤ ሰከንዶችን የዘገየችው ዩጋንዳዊቷ ቻሪቲ ቺሮፕም ሶስተኛ በመሆን የነሀስ ሜዳሊያውን አጥልቃለች፡፡
በተመሳሳይ የወንዶች በ5ሺ ሜትር ውድድር አትሌት አብዲሳ ፈይሳ 13:41:56 በሆነ ሰአት ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ንብረት ክንዴ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ኬንያዊው አትሌት አንድሪው ኪፕሩቶ አላሚሲ የወርቅ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆኗል። ዩጋንዳዊው ኬኔት ኪፕሮፕ የነሐስ ሜዳሊያውን ወስዷል።
በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ቻምፒዮናው ዘንድሮ 20ኛው ላይ ደርሷል። 134 ሀገራት ከ1ሺ700 በላይ አትሌቶቻቸውን እያፎካከሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በ6 የተለያዩ ርቀቶችም በውድድሩ ላይ እየተካፈለች ትገኛለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም