
በአዲስ አበባ ከተማ የገበያን ውል ለመያዝ ይቸግራል። አንዳንዴ በሰዓትና በደቂቃ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋዎች ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ ነጋዴዎች በሀገር ውስጥ ጥንቅቅ ብለው ለሚመረቱ ምርቶች ሳይቀር ውጫዊ ምክንያት ሲያስተጋቡ ይሰማሉ፡፡
በገበያው በመዋዠቅ ልጓም አልባ የሆነውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ ይገኛል፡፡
ከሚጠቀማቸው የገበያ ልጓም መግሪያ አንዱ ሸማች ማኅበራትን ማጠናከር ላይ ያተኩራል፡፡ የሸማች ማኅበራት ሲጠናከሩ የግብርና ምርቶችን ከየማሳው በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ለማህብረሰቡ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉ ይታመናልና ነው፡፡
ሸማች ማኅበራት ከግብርና ምርቶች ባሻገር የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እና ቀጥተኛ የንግድ ትስስር በመፍጠር የዋጋ ንረት የሚያስከትሉ ደላላዎችን ከመስመር በማስወጣት የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በአዲስ አበባ እየተሠራ የሚገኘው በሸማች ሥጋ ቤቶች እንዲሁም በ132 የሰንበት ገበያ ቦታዎች የተለያዩ ምርቶችን ለግብይት በማቅረብ ነዋሪዎችን ከተጨማሪ ወጪ እና ከዋጋ ንረት የመታደጉ ሥራ እንደ አንድ አብነት የሚቀርብ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀብተየስ ዲሮ እንደሚሉት፤ በመዲናዋ እየተከሰተ ያለውን የምርት የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት በሸማች ኅበረት ሥራ ማኅበራት ከዚህም እልፍ ያሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
ማኅበራት በቂ የሆነ ምርት የማከማቸትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ የማቅረብ ሥራ መሠራቱ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ የሚባል ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ብልሹ አሠራርንና ሌብነትን ማስወገድ የቻለ ተቋማዊ ለውጥ ማድረጉን የሚያነሱት ምክትል ኮሚሽነር ሀብተየስ፤ ለውጡም ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያድግ በማድረግ ገበያውን እያረጋጋ እንደሚገኝ ያነሳሉ፡፡
ኮሚሽኑ ስርቆትንና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ ማሳ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ በማደረግ፤ ማህብረሰቡን የማገልገል ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ማህበረሰቡን በፍትሕዊነት የማገልገል ሥራም በመዲናዋ የሚታየውን የምርት የዋጋ ንረት እያረጋጋ ይገኛል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የምርት አቅርቦት በሚገኝባቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጥተኛ የንግድ ትስስር በመዘርጋት፣ አምራቾች ምርታቸውን ለመዲናዋ ነዋሪዎች የሚያቀርቡበት አሠራር በፍጠር፤ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ የማደረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ይህም የሚታየውን የኑሮ ውድነት እያስታገሰ ይገኛል ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ለኅብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ማሳ ግብይት ፈጥረው በሸማች መጋዘን እንዲያከማቹ ፍቃድ መሰጠታቸውን በመጥቀስ፤ ከክልል ማህበራት ጋርም የግብይት ትስስር ፈጥረው የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም እንዲያደርጉ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ማህበረሰቡ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት እንዲፈጥር እድል ከፍቷል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በዓላት በተቃረቡ ቁጥር ጥቂት ነጋዴዎች ምርቶችን በመደበቅ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ በማንሳት፤ ምርትን በሚደብቁና የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ጥቂት ነጋዴዎች የሚፈልጉት የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ቀውስ እንዳይከሰት በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት መጋዘን በቂ የምርት ክምችት በማድረግ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረጋ ሥራ ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በመዲናዋ በበዓላት ወቅት የሚከሰትን ያልተጠበቀ የኑሮ ውድነት ለማርገብ አምራችና ሸማችን በቀጥታ የሚያገናኝ ኤግዚቢሽን እና ባዛር የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
በበዓልም ሆነ በአዘቦት ወቅት የሚገጥምን የምርት እጥረት፣ የዋጋ ንረትና የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ ያለው ሥራ በመጪው አዲስ ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የለሚ አዲስ ዩኒየን ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ፈለቀ ሞላ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሸማች ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በኩል ምርትን በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሸማች ኅብረት ሥራ ሱቆች እና በሰንበት ገበያዎች በየአካባቢው እንዲቀርቡ በማደረግ የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት በተጨማሪ ማህበረሰቡን ከትራንስፖርት ውጪ የማዳን ሥራ እየተሠራ ነውም ይላሉ፡፡
በአንዳንድ ክልሎች ያለው የፀጥታ ችግር ምርት ወደ መዲናዋ በቀጥታ ለማስገባት ፈተና መሆኑን የሚጠቅሱት ፓስተር ፈለቀ፤ ያለውን ተግዳሮት በተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ማለትም ሰላም ከሆኑ ክልሎችና ከአዲስ አበባ አቅራቢ ከሚገኙ አምራቾች የግብይት ትስስሮሽ ፈጥሮ ችግሩን መፍታት መቻሉን ያብራራሉ፡፡ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
የሸማቶች ማኅበራት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋና በጥራት ተደራሽ በማድረግ በኩል እየሠራ ያለው ሥራ ማህበረሰቡ በነጋዴዎች የሚደርስበትን የዋጋ ጫና እየፈታ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
በበዓላት ወቅት በመዲናዋ የሚከሰተውን የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ግሽበት ለመከላከል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች የማከማቸት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በመጪው የዘመን መለወጫ በዓልም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች የአቅርቦት ችግርና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እየሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ሲሉ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የዩኒየኖች የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ታረቀኝ ለማ ነግረውናል፡፡
በመዲናዋ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የመጣውን የምርት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በሸማች ኅብረት ሥራ በኩል ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለውም ሥራ ገበያውን ማረጋጋት የቻለ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የተስተዋለውን ምርት የመበደበቅና የዋጋ ጭማሪን በመከላከል ገበያን የማረጋጋት ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሠርቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ነጋዴዎች ምርትን በከፍተኛ ዋጋ ለማህበረሰቡ በማቅረብ የኑሮ ውድነት እያባባሱ መሆኑን ጠቁመው፤ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ሸማች ማህበራት እየሠሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ይላሉ፡፡ መንግሥትም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም