‹‹የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል!››

ማህበረሰባችን ስግብግብነትን እና ማጭበርበርን የሚያነውርበት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ ማህበረሰባዊ ስነ ቃል አለው። ‹‹የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል›› የሚለው አንዱ ነው። የራሱ ያልሆነ ነገር አጭበርብሮ የሚወስድ ሰው ፈጣሪ አይባርክለትም፣ የራሱንም ጭምር ይቀጣዋል ተብሎ ይታመናል። በዘመናዊው የሕግ ቋንቋ ካየነውም አንድ ሌባ ሲያዝ የሰረቀውን ነገር ብቻ ተቀምቶ አይለቀቅም። ቅጣት አለው።

‹‹የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች›› የሚለውም ከሚገባን ውጭ ለማግኘት መሞከራችንን የሚያነውር ነው። ‹‹አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል›› የተባለውም ይህንኑ የስግብግብነት በሽታ ለመግለጽ ነው። በሳይንስ እንኳን ብናየው ከልክ በላይ የሚበላ ሰው ጨጓራው መያዝ ከሚችለው በላይ ስለሚሆንበት ለሌላ በሽታ ይዳርገዋል።

በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ያደግን ሰዎች ታዲያ ምን ነክቶን ይሆን በዚህ ልክ ነውረኞች የሆንነው? የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ነገር አይገርምም ወይ? የት ሆነው ሊበሉት ነው? እነርሱ ብቻ በሕይወት የሚተርፉ እየመሰላቸው ይሆን?

እናቴ ስታወራ የሰማሁት አንድ የ1977 ዓ.ም ታሪክ ትዝ አለኝ። በ1977 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ረሃብ ተከስቶ ነበር። አንዲት የአካባቢያችን ሴትዮ ጤፍ በጎተራ (ከጭቃ የሚሰራ የእህል ማስቀመጫ) አስቀምጣ መረገችው። መምረግ ማለት የጎተራውን አፍ በባህላዊ መንገድ ማሸግ እንደማለት ነው። ሴትዮዋ ጤፉን ጎተራ ውስጥ አሽጋ ረሃብ ይቆላታል። ጨክኜ መተው አለብኝ ብላ ተወችው። የባሰ ቀን ሲመጣ ብላ ማስመቀጧ ነው። በእሷ ቤት ሳይበሉ ከመዋልና ከማደር በላይ ክፉ ቀን አለ ማለት ነው። አንድ እግሩን ጅብ እየበላው ጓደኛውን ‹‹ዝም በል! ዝም በል! የእኔን እግር ነው›› አለ እንደተባለው ሰውዬ ማለት ነው።

ያቺ ሴትዮ ጤፉ ከጎተራ ውስጥ ተመርጎ ተቀምጦ እሷም በረሃብ ተመርጋለች። እንዲህ እንዲህ እያለች በረሃብ ወደቀች። ጤፍ ጎተራ ውስጥ ማስቀመጧን ያወቁ ሰዎች ተቆጥተው መብላት ጀመረችና እንደምንም ዳነች። ይህ አንድ ጎበዝ ደራሲ የፈጠረው ልቦለድ እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይመስልም አይደል?

የዚች ሴትዮ ነገር አንዳንድ የሀገራችንን ስግብግብ ነጋዴዎች ያስታውሱኛል። እንኳን የዶላር ዋጋ ጨመረ ሲባል ሰምተው ይቅርና በሀገራዊ ቀውስ ወቅት ራሱ ለማትረፍ የሚስገበገቡ ናቸው። የት ሆነው ሊበሉት ነው? ሀገርና ሕዝብ ከሌለ በምን ሊያጌጡበት ይሆን? የሌሎች ሰዎች መቸገር እንዴት ለአንዳንዶች እንጀራ ይሆናል?

የሆነ ነገር ሆነ በተባለ ቁጥር የተጋነነ ዋጋ መጨመር ልማዳችን ሆኖ ቀረ። ከሁኔታቸው የምንረዳው የተጋነነ ዋጋ የሚጨምሩት የሚያመጡበት ዋጋ ስለተወደደ ብቻ አይደለም። ሰበብ ፈልገው ማጭበርበር የሚፈልጉ አሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፤ የዶላር ምንዛሬ ዋጋ ጨመረ በተባለ በማግስቱ ዋጋ መጨመር የጀመሩ ነበሩ። ያ ዋጋ የጨመሩበት ዕቃ ግን ከወራት በፊት በነበረው ዋጋ የመጣ ነው። የተፈለገው በብዙ እጥፍ ማትረፍ ነው እንጂ ተገቢውን ትርፍ ማግኘት አይደለም። ህሊና ላለው ሰው በዶላር መጨመር ምክንያት ሊጨምር የሚችለው ከጭማሪው በኋላ በገዛው ዕቃ ላይ ነው። አንድ ዓመት አልሸጥለት ብሎ የቆየ ሱሪ በምን አግባብ ነው በአሁኑ ዋጋ የሚሸጠው?

ነጋዴ የሚነግደው ለትርፍ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህን ማንም እንዲያስረዳን አንጠብቅም። ነዋሪ በመሆን ብቻ የሚታወቅ ነው። የሆነ ነገር ስንገዛ እንኳን ‹‹ይህን ያህል እንግዛችሁ›› ብለን ዋጋ ስንሰጥ ‹‹አይ! በዚህ ከዚያ ራሱ አልመጣም!›› ይሉናል። ለትርፍ መሆኑን በግልጽ ስለምንተዋወቅ ማለት ነው። ካመጣበት ዋጋ ጨምሮ እንደሚሸጥልኝ ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ምክንያቱም እሱ ብዙ ለፍቷል፣ ሲያመጣውም ወጪ አለበት። ይሄ አልጠፋንም!

ችግሩ ግን ግልጽ የሆነ ማጭበርበር ማድረጋቸው ነው። ከአንድ ዕቃ ብቻ ሙሉውን ማካካስ የሚፈልጉ አሉ። ማግኘት ከሚገባቸው ትርፍ በላይ የሚያገኙ አሉ። ይሄ አልበቃ ብሎ ምርት በመደበቅ ሌላ ተጨማሪ የገበያ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

እኔ የሚገርመኝ፤ የገበያ ቀውስ ሲፈጠር እነርሱንስ አይጎዳም ወይ? አርቆ ማስተዋል ስለተሳነን እንጂ ራስን  በራስ እንደማጥፋት ማለት እኮ ነው። ማህበረሰብ ሲቃወስ እኮ ብዙ ነገር አብሮ ይቃወሳል። ሀገርና ሕዝብ ይተረማመሳል፤ ታዲያ ይሄ በተዘዋዋሪ አይጎዳቸውም ወይ?

ባለፈው ረቡዕ እንደተገለጸው፤ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በየክልል ከተሞች ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ 1 ሺህ 671 የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል። ከዚህ ቀደም በሰሩት ሕገ ወጥ የንግድ ተግባራት ምክንያት ታሽገው የነበሩ 18 ሺህ 789 ድርጅቶች ደግሞ የውል ስምምነት ፈፅመው ወደ ሥራ ተመልሰዋል። ከዚሁ ሕገ ወጥ ጉዳይ ጋር በተያያዘ 82 ነጋዴዎች በዚያን ቀን ብቻ ታስረዋል። በድምሩ ደግሞ 628 ነጋዴዎች ታስረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 182 ነጋዴዎች ከእስራት የተፈቱ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

እንግዲህ ልብ በሉ! ‹‹አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል›› ማለት ይሄው ነው። ከልክ በላይ ሲስገበገቡ ታሰሩ። ጊዜና ገንዘባቸውን አባከኑ። ምናልባት እንደ ጥፋታቸው ደረጃ ታስረው የሚቆዩም ይኖራሉ። ንግድ ቤታቸው ታሽጓል። ሲታሸግ ደግሞ ሥራ ያቆማል ማለት ነው። ሥራ ሲያቆሙ የሚደርስባቸውን ክስረት ማሰብ ነው። ታዲያ ይሄን ድርጊታቸውን ‹‹አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል›› የሚለው የማህበረሰባችን አባባል በትክክል አይገልጸውም ወይ?

ህሊና የሚባለውን ነገር እንተወው! ቢያንስ ግን ሀገርና ሕዝብ ካልተረጋጋ በሰላም ሀብታም መሆን ይቻላል ወይ? አይቻልም እኮ! በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የነበረውን ማስታውስ ቀላል ነው። ስግብግብ ነጋዴዎችን ብዙዎች ሲታዘቧቸው የነበረው ‹‹መኖራችሁን አውቃችሁታል ወይ?›› በሚል ነበር። በዚያው ልክ ደግሞ ቤታቸውን በነፃ የሰጡ፣ የአንድና የሁለት ወር የቤት ኪራይ አንቀበልም ያሉ ነበሩ። ችግር ሲያጋጥም እንዲህ መረዳዳት ሲገባ እንዴት በተቃራኒው ግርግር አገኘሁ ተብሎ ለማጋበስ ይታገላሉ?

ሲቀጥል አሁን አጋጠመ የተባለው ነገር ‹‹የገበያ ቀውስ›› ለመባል የሚበቃ አይደለም። ድሮም የነበረ ነው። ራሳቸው ነጋዴዎች ግርግር ፈጠሩ እንጂ የተለየ የቀነሰም ሆነ የጨመረ ምርት አልነበረም፤ እንዲያውም እንደ ሽንኩርት ባሉት ምርቶች ላይ ቅናሽ ታይቷል ብሏል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር። ዳሩ ግን ሁሌም ሰበብ የሚፈልጉ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ገና ለገና ሲወደድ አትርፈን እንሸጣለን በሚል ሰበብ ምርት መደበቅ ጀመሩ። ደግነቱ የፖሊስ ኃይል ከቀበሩበት እየመነቀረ አውጥቶታል። እንዲያውም እዚህ ላይ አንድ የሰማሁት ፈገግ የሚያሰኝ ነገር አለ። ከዚህ በፊት ዘይት የማይሸጡ ሁሉ ሳይቀር ደብቃችሁ ነው እንባላለን በሚል ዘይት እየገዙ መደርደሪያ ላይ ማ ስቀመጥ ጀምረዋል።

ህሊና እና ሕግ ሊያስተዳድረን ካልቻለ የግዴታ ቁጥጥር ያስፈልገናል ማለት ነው። ‹‹የክፉ ጎረቤት መብረቅ ይመታዋል›› እንደሚባለው በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት በህሊና እና በሕግ የሚሠሩትም መጉላላቱ ይጎዳቸዋል ነው። የገበያ ቀውስ መፍጠር ጉዳቱ ለራሳችሁም ይተርፋልና አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ!

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You