የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ዞን ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለሦስተኛ ጊዜ ለዋንጫ ደርሷል።የፍጻሜው ጨዋታ በነገው ዕለት ከሰዓት በኋላ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም የሚካሄድ ሲሆን፤ አሸናፊው ክለብ ዞኑን በመወከል በአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል፡፡
ለአራተኛ ጊዜ ከነሐሴ 11/2016 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ ዞን ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታም ነገ ይጠናቀቃል።ለፍጻሜው የደረሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ከኬንያ ፖሊስ ቡሌት ለዋንጫ ይጫወታል።ዘጠኝ ክለቦች በሁለት ምድብ ሲፎካከሩበት በቆየው ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፎ ለፍጻሜው ፍልሚያ መብቃት ችሏል።በምድብ አንድ ሦስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሮ ሦስት ብቻ ሲቆጠሩበት የግማሽ ፍጻሜውን ጨዋታም በሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች አስቆጥሮ በመርታት ለዋንጫው ደርሷል።
በደረጃ ጨዋታ ደግሞ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ከታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ ጋር ነገ ከረፋዱ 5፡00 ላይ ይጫወታሉ።ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዞኑ የቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ብርቱና ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ለሦስተኛ ግዜ የፍጻሜ ተፋላሚ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም እአአ በ2021 ውድድሩ በተጀመረበት የመጀመሪያ ተሳትፎ ለፍጻሜ ደርሶ ባለቀ ሰዓት በተሰጠበት የፍጹም ቅጣት ምት በኬንያው ቪጋ ክዊንስ ተሸንፎ ዋንጫውን ማንሳት እንዳልቻለ ይታወሳል።
አምናም በተመሳሳይ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው ውድድር ጉዞ አድርጎ በታንዛኒያው ጄኬቲ ኩዊንስ በመለያ ምት ተሸንፎ ከዋንጫ ውጪ መሆኑ ይታወሳል።ክለቡ ዘንድሮ በሀገሩ እንደ መጫወቱ እስከ አሁን ባሳየው ጥንካሬ ዋንጫውን አሸንፎ ቁጭቱን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ አህጉር አቀፍ ውድድር መሳተፍ የሚያስችል ትኬቱን እንዲቆርጥ ያደርገዋል።በምድብ ማጣሪያ ያሳየውን ብቃት ማስቀጠልና ከአሁን በፊቶቹ የፍጻሜ ውድድሮች ላይ የታዩ ድክመቶችን በመቅረፍ እንደሚቀርብም አሰልጣኙ ተናግሯል፡፡
ከትናንት በስቲያ በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ክለብ ጋር ፈታኝ ጨዋታ አድርጎ 2 ለ 1 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜ የደረሰው ንግድ ባንክ፣ ግቦቹን መሳይ ተመስገን በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲሁም እመቤት አዲሱ በሁለተኛው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ አስቆጥረው ለፍፃሜ አብቅተውታል። በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታው የንግድ ባንክ አጀማመር መልካም የሚባል ቢሆን እየተዳከመ የመሄድ፣ የቅንጅት ችግር፣ እድሎችን ማባከን እና የመዳከም ሁኔታዎች ተስተውለውበታል።
የቡድኑ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፣ ጨዋታው ከባድ ከመሆኑ ባለፈ ለዋንጫ ለማለፍ የሚደረግ እንደመሆኑ በተጫዋቾቹ ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጿል።ቡድኑ ግብ አስቆጥሮ እየመራ በነበረበት ወቅት በተፈጠረ ውጥረትም ግብ አስተናግዷል።ይህም የተፈጠረው በጥቂት ቀናት ብዙ ጨዋታዎችን በመጫወቱና የመጨረሻው የምድብ ጨዋታው ከባድ በመሆኑ ምክንያት ነው ሲል አስረድቷል።
የዋንጫው ተፋላሚ የሆነው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ አጨዋወት የአካል ብቃት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተጫውተው ሦስቱን እንዳሸነፉና ጠንቅቅው እንደሚያውቋቸውም አሰልጣኙ ይጠቁማል።ኬንያ ላይ በተካሄደው የ2021 የሴካፋ ዞን ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ንግድ ባንክ በቪጋ ኩዊንስ ተሸንፎ ዋንጫውን ቢያጡም አሁን ግን አሸንፈው ዋንጫውን እዚህ እንደሚያስቀሩ ገልጿል።
ሁለቱ ቡድኖች በአንድ ምድብ እንደነበሩና ከጠንካራ ምድብ አልፎ ለፍጻሜ እንደመብቃታቸው ቡድኑ ዋንጫውን ለማንሳት ዝግጁ ነው።ክለቡ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ተሳትፎ ለሦስት ጊዜያት ለዋንጫ ደርሶ ማሳካት ያልቻለው የዋንጫ ጉጉትና ከአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ ጨዋታዎቹን ፈታኝ አድርጓቸዋል።በአራቱ ውድድሮች ዋንጫ ያነሱ ቡድኖች ሦስት ጊዜ እንኳን ግማሽ ፍጻሜ መድረስ አለመቻላቸው የውድድሩን ጥንካሬ ያሳያል፤ በዚህም መሰረት ንግድ ባንክ ካለፉት ልምዶች በመነሳት ዋንጫውን የሚያነሳበትን ሁኔታ ይፈጥራል።የዋንጫ ጨዋታ የራሱ የሆነ ባህሪ የሚኖረው በመሆኑ እግር ኳስ የሚፈቅዳቸውን ሁሉ በመተግበር ዋንጫውን ለመውሰድ እንደሚጫወቱም አሰልጣኝ ብርሃኑ ገልጿል፡፡
የሴካፋ ዞንን በመወከል በአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍ አንድ ቡድን ለመለየት ዘጠኝ ቡድኖች በሁለት ምድቦች ተከፍለው ውድድራቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የዋንጫው አሸናፊ ቡድን ሴካፋን ወክሎ በ2024 የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የሚሳተፍ ይሆናል።በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች የሚገኙ የሴት ቡድኖች የማጣሪያ ውድድር ካደረጉ በኋላ ዞኖቻቸውን በመወከል የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይካፈላሉ፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም