
ዜና ሐተታ
ደመናው ጥጥ መስሎ በወረደበት የደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ፀጥ ያሉ ኮረብታዎች ይታያሉ። በዚያ ያለው የልማትና የሰላም ጠረን ደግሞ ከሩቅ ቦታ ተጉዞ የደረሰን ሳይቀር በቶሎ ይማርካል።
አካባቢው ከዚህ ቀደም እንደ አብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ገጥሞት ነበር። ሆኖም ዛሬ ላይ፣ የጸጥታው ችግር እንደ ጉም ተኖ የቀዬው ሕዝብ የልማትና የሰላም ዘር መዝራትን ተያይዞታል። መሬቱን እያለማ ሰላሙንም እየጠበቀ ይገኛል።
በስፍራው ቆሞ ላስተዋለ፤ በአረንጓዴ የልማት ባህር ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ ፅናት በአይኑ ላይ አይረሴ ትዝታን ይጥልበታል፡፡ መሬቱ ለም ብቻ አረንጓዴነቱ ያስቀናል። በሰዎች የሰላም ቁርጠኝነት የተገኘ የልማት አሻራ ጎልቶ ይታያል፡፡
ወጣቱ በተከላቸው ችግኞች መካከል ሲራመዱ ቅጠሎቻቸው በእርጋታ ነፋሻማ አየር ውስጥ ሲያብረቀርቁ፣ አየሩን ዘልቆ የገባው ጥልቅ ሀገራዊ የዓላማ ስሜት ይንጸባረቃል፡፡ ይህ ስለ አረንጓዴ ልማት ብቻ አልነበረም።ይህ ብዙዎች የተፈተኑበትን የጸጥታ ችግር በመቅረፍ ሰላምን ስለመመለስ የተገለጸ ውጤትም ጭምር ነው።
በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ጉዳይ ልማትን ለማከናወን ቢያስቸግርም ወረቦቦ ላይ ቆራጥነት ፣ አንድነት ፣ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ሌላ ታሪክ እየተጻፈ ነው፡፡
ወይዘሮ አይሻ ኢብራሂም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ “የፀጥታ ችግሮች አልፎ አልፎ ቢታዩም እጃችን ከልማትና ከሰላም አልተመለሰም” ሲሉ ቅንነትን ፍንተው አድርጎ በሚያሳየው ገጽታቸው ታጅበው ይናገራሉ፡፡
ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አይሻ ፤ ለረጅም ዓመታት ጀምሮ የችግኝ ተከላን ጨምሮ በአካባቢው በሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ያነሳሉ።ቁርጠኝነታቸው እንደ ዜጋ ለሀገሬ በልማቱም ሆነ በሰላሙ የራሴን ዐሻራ ማሳረፍ አለብኝ ከሚል ስሜት እንደሚመነጭም ይናገራሉ፡፡
በጎ እሳቤያቸው ደግሞ ከራሳቸው አልፎ ልጆቻቸው ላይ የተስተጋባ መሆኑን አንስተው፤ “በእርግዝናዬ ወቅት ዛፍ ለመትከል ወጣሁ፣ ዛሬ ደግሞ ዛፍ የምትተክል ሴት ልጅ አለችኝ” ይላሉ አይኖቻቸውን በኩራት ወገግ አድርገው፡፡
የልማት ሥራዎቻቸውን እየሠሩ በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወጣቶችን እየመከሩና ለሰላሙ ዘብ በመቆም አርዓያነታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ነው የተናገሩት፡፡ ይህ የሕይወት ተሞክሮ ሰላምን ለሚሻ ማንኛውም ዜጋ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በራስ መተማመን በተሞላበት መንፈስ “በዚህ ልማት ውስጥ ያለኝ ተሳትፎ መቼም አይቆምም፡፡ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሌን እወጣለሁ” በማለት ነው የሰላምና የልማት አካል የመሆን ቁርጠኝነታቸውን ያስረዱት፡፡
በወረባቦ ወረዳ 01 ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አሚና ሰይድ በበኩላቸው፤ ትዳር፣ ልጅ፣ ማህበራዊ ሕይወት የመሳሰሉ የሕይወት ስንክሳሮች ልማትን ከማከናወን አላገዳቸውም፡፡ በልማትና ሰላም ጉዳይ ያላቸው አመለካከት ግልጽና ጥልቅ ነበር፡፡ “ሰላምና ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” በማለት ነው የሚገልጹት፡፡
በዓመታት የሕይወት ልምድ ላይ የተመሰረተው ልማትን የመከወን ጉዟቸው በአባቢው የጸጥታ ችግር ባጋጠመበት ወቅት እንኳን እንዳልተስተጓጎለ ይናገራሉ።
“ከዚህ ቀደም የጸጥታው ሁኔታ የልማት ስራዎችን ለመሥራት አስጊ ነበር፤ በእያንዳንዱ የልማት ተነሳሽነት ባለው ልብ ላይ መጥፎ ጥላ አሳርፎ ነበር፤ የወረባቦ ሕዝብ ግን ባለው ጽናት ሰላሙን አረጋግጧል፤ አሁን ኅብረተሰቡ ለልማትና ለሰላም እጁን ዘርግቷል” ይላሉ።
በተለይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብርን በመሳሳሉ ሁነቶች ላይ በመሳተፍ ችግኞችን እንደሚተክሉ የገለጹት ወይዘሮ አሚና፤ “ችግኞች፣ በአንድ ወቅት ይተካላሉ፤ እንክብካቤ ሲደረግላቸውም ይበቅላሉ፤ ሰላምም እንዲሁ ኅብረተሰቡ ከልቡ ከፈለገው ሰላምን ዘርቶ ከሰላም ፍሬ ይመገባል” በማለት፤ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ወጣቶች ከልማቱ ጎን ለጎን የጀመሩትን የሰላም ሥራ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ነው የሰላምን ክብደት በተረዳው አንደበታቸው የተናገሩት።ሰላም የሁሉም መሠረት እንደመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀው ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡
ከወረባቦ ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ፋንታው መሀመድ፤ ሰላም ከልማት ጋር ጥልቅ ግንኙነት ያለው ነው ይላሉ፡፡ “በልማት ሥራዎች ችግኞችን በመትከል አፈሩን ከመሸርሸር ታድገናል” ሲሉ የሥራቸውን ተጨባጭ ፋይዳ ይገልጻሉ።የኅብረተሰቡ ጥረት አካባቢውን ከማስዋብ ባለፈ ከድርቅና ከአፈር መሸርሸር አስከፊ ችግር መታደጉን ይጠቁማሉ፡፡
“ሰላምና ልማትን ሁልጊዜ ለየብቻ አንመለከትም፡፡ ሁለቱንም እንደ አይናችን ብሌን እንይዛቸዋለን” የሚሉት አቶ ፋንታው፤ ሌሎችም በዚህ መርህ በመገዛታቸው የወረባቦንና አካባቢውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ማድረግ እንደቻለ ያስረዳሉ፡፡
አቶ ፋንታው እንደሚሉት፤ ሰላም በጥንቃቄ እንደሚን ከባከቡት ችግኝ የማያቋርጥ እንክብካቤና ትኩረት ይሻል፡፡ የወረባቦ ሕዝብም ችግር ቢያጋጥመውም ተቋቁሞ በማለፍ ሰላም መፍጠር እንዲሁም አልምቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ረቡዕ 22 ቀን 2016 ዓ.ም