የፓሪስ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ የኢትዮጵያን የ3ሺ ሜትር ክብረወሰን በእጁ አስገብቷል።
የ2024 የዳይመንድ ሊግ ውድድር ባለፈው እሁድ 12ኛው መዳረሻ ከተማ በሆነችው በፖላንዷ ቾርዞው ከተማ በሴሌሲያን ስቴዲየም ሲካሄድ ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊ የ3ሺ ሜትር ፉክክሩን ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። የረጅም ርቀት በርካታ ከዋክብት ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት ውድድር በሪሁ ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ ባይችልም ሁለተኛ ሆኖ ሲፈፅም ያስመዘገበው 7:21:28 ሰዓት የኢትዮጵያን ክብረወሰን መጨበጥ አስችሎታል። ይህ ሰዓቱም በርቀቱ የዓለም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖም ተመዝግቧል።
አስደናቂ ፉክክር በታየበት ውድድር ኖርዌዣዊው የ5ሺ ሜትር የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮን ጃኮብ ኢንግብሪግስተን የ3 ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን ሰብሯል። ጃኮብ 7:17.55 በሆነ ሰዓት ክብረወሰኑን ሲያሻሽል፣ እኤአ 1996 በታሪካዊው ኬንያዊ አትሌት ብሪያን ዳንዔል ኮመን በ7:20:67 ተይዞ ለ28 ዓመታት የቆየውን ክብር ተረክቧል። ለዚህም ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ ውድድሩን ከመጀመሪያ አንስቶ በማፍጠን ያሳየው ድንቅ ብቃት ትልቅ ሚና ነበረው።
ከፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ማግስት በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ የዳይመንድ ሊግ ፉክክር ለድል የተጠበቁ አትሌቶች ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በሦስት ሺ ሜትር የወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ዮሚፍ ቀጀልቻ 7:28:44 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፎካከረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ኃይሌ 7:30:97 አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ባለድሉ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ7:32:49 ሰዓት ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ፈፅሟል።
በፖላንዷ ቾርዞው ከተማ ሴሌሲያን ስቴዲየም በተለያዩ ውድድሮች የዓለም ክብረወሰኖችና ፈጣን ሰዓቶች በተመዘገቡበት ምሽት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሴቶች 1500 ሜትር ውድድር በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቋል። ኢትዮጵያዊቷ ወጣትና ትልቅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ድሪቤ ወልተጂ የ1500 ሜትሩ ፉክክር አሸናፊ ሆናለች። ወጣቷ አትሌት ርቀቱን 3:57:08 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ችላለች። ድርቤ ከፓሪስ ኦሊምፒክ መልስ ባለፈው ሳምንት በስዊዘርላንድ ሉዛን ዳይመንድ ሊግ በ3000 ሜትር ተሳትፋ የውድድሩን ክብረወሰን ጭምር በመስበር ማሸነፏ ይታወሳል። ይህም በዳይመንድ ሊጉ በአራት ቀናት ልዩነት በሁለት የተለያዩ ርቀቶች ጣፋጭ ድል እንድታጣጥም አስችሏታል።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በፓሪስ ኦሊምፒክ አስደናቂ ብቃት ላይ ሳለች ካለመሳተፋ ቁጭት በኋላ በዳይመንድ ሊጉ ድንቅ ፉክክር አድርጋ 3:57:88 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፣ እንግሊዛዊቷ ቤሊ ጂዮርጂያ 3:58:11 በመግባት ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች።
በተመሳሳይ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ሞሮኳዊው የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የርቀቱ ባለድል ሶፊያን ኤልባካሊ አሸንፏል። ኤልባካሊ ከፓሪስ ኦሊምፒክ የርቀቱ ድል በኋላ በዚህ ዳይመንድ ሊግ ብርቱ ፉክክር ቢገጥመውም ከኬንያዊው አሞስ ሴሬም ጋር እኩል በሆነ ሰዓት (8:04.29) አጠናቆ በፎቶ ፊኒሽ አሸናፊነቱ ሊረጋገጥለት ችሏል።
በፓሪሱ ኦሊምፒክ የርቀቱን የወርቅ ሜዳሊያ ለማሸነፍ ጥቂት ሲቀረው መሰናክሉ ጠልፎት የወደቀው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማ በዳይመንድ ሊጉ አልተሳተፈም። በዚህ ውድድር ቀደም ብሎ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ማሸነፍ አልቻሉም። ሳሙኤል ፍሬው 3ኛ፣ ሳሙኤል ዱጉማ 8ኛ እንዲሁም ጌትነት ዋለ 11ኛ ሆነው ውድድራቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን አብርሃም ስሜ ደግሞ አቋርጦ ወጥቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም