ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ በአረንጓዴ ዐሻራና በዓባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ስለተገኘው ስኬት ለመላው ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል
በብዙ ተዓምራት በሰው ልጅ አዕምሮ ሊታመኑ በማይችሉ ክንውኖችና የታሪክ አንጓ ላይ እንገኛለን። አሁን ያለንበት የታሪክ አንጓ ወደኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያን ታሪክ ብናጠና እና ያለፍንበቸውን መንገዶች በቅጡ ብንመረምር፤ አሁን የምንገኝበት ዘመን አሁን የምንገኝበት አጠቃላይ የልማት ፣የፖለቲካ ሂደት ለዘመናት አንቆ ከያዘን ምዕራፍ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለመሸጋገር አንጓው ላይ ያለን ይመስለኛል።
600 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀንበር እንትከል ብለው፤ ኢትዮጵያውያን ወስነው ከዚያ በላይ ማሳካት እንደሚችሉ ያሳዩበት ቀን ነው። 600 ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀንበር ቀላል ሥራ አይደለም። 29 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወስነው ፀሐይ፣ ቁር፣ ዝናብ፣ውርጭ፤ ዳገት መውጣት አያግደንም፤ለኢትዮጵያ ልማት ለልጆቻችን ለምንጥለው መሠረት ብለው ባይወስኑ 600 ሚሊዮን ችግኝ አንዳንድ ሀገራት በዓመት መትከል አይችሉም። ይሄ ኢትዮጵያውያን ካለንበት አረንቋ ለመውጣት፣ ካለንበት ሁኔታ ተሻግሮ የሚቀጥለውን ምዕራፍ ለመጨበጥ ያላቸውን እጅግ የጠነከረ እምነትና ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው።
በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት እስከዚህ ዓመት ክረምት መጨረሻ ድረስ 40 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል፤ በዚህ ዓመት ደግሞ 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ነው ያቀድነው። 600 ሚሊዮኑ ከእቅዳችን በላይ ተሳክቷል። 7.5 ቢሊዮን ያልነው ከእቅዳችን በላይ ተሳክቷል። በድምሩ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ኢትዮጵያ ተክላለች።
40 ቢሊዮን ችግኝ ከጅምሩ ዘሩን ከማዘጋጀት ጀምሮ ጉድጓድ መቆፈር ፣ መትከል ያለውን ሂደት አንድ አንድ ዶለር ብለን ብንወስድ 40 ቢሊዮን ዶላር ለልጆቻችን ኢንቨስት አደረግን፤ለነገ ኢንቨስት አደረግን፤ነገ ለምናያት ኢትዮጵያ አሁን ካለን ችግር፣ አሁን ካለን ቅሪት፣ አሁን ካለን አንጡራ ሀብት ቀንሰን የነገው ስለሚበልጥና ስለሚልቅ 40 ቢሊዮን አኖርን ማለት ነው።
ነገን ታሳቢ አድርጎ ኢንቨስት የሚያደርግ የትኛውም ሀገር፣ ኢንቨስት የሚያደርግ የትኛውም ቤተሰብ፣ የትኛውም ትውልድ፣ የትኛውም ዜጋ የተሻለ ብሩህ ነገን ለልጆቹ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያውያን ዛሬ የዕለት ጉርስ ጉዳይ፣ የእርዛት ጉዳይ፣ የመጠለያ ጉዳይ፣ የሚጠጣ የሚባለው ነገር ጉዳይ አሳሳቢ ቢሆንም፤ እንደ አንድ ሰው ሳይሆን ተደምረን በተሰበሰበ የኢትዮጵያዊነት ስሜት / የሆነ ሀብት ለነገ ኢንቨስት የማድረጉ ልምምድ ከዚህ ቀደም እምብዛም ያልነበረ ቢሆንም/ ኢንቨስት ማድረግ ችለናል።ይህንን ካስቀጠልነው ይህ ለልጆቻችን ምን ሊያመጣ እንደሚችል በቀላሉ መገመት ይቻላል።
እዚህ ውስጥ የምናያቸው ድንቃ ድንቅ እሳቤዎችና ተግባራት አሉ። አንደኛ ለትውልድ በመትከል መሠረት እንጣል የሚለው ሀሳብ በራሱ በጣም ትልቅ ነው። ሀሳብ ስለሆነ የሁሉ ነገር መጀመሪያ ነው፤ ሀሳቡ መጀመሪያ ብቻውን መተንተን አለበት፤ እንዴት ታሰበ ? እንዴት ተጀመረ ? የሚለው ጉዳይ በራሱ አቅልለን የምናየው ነገር አይደለም።
ሁለተኛ ከሀሳቡ በኋላ ደግሞ ሀብት ያስፈልጋል። አንድ ነገር ማሰብ ይቻላል፣ ማቀድ ይቻላል፣ ግን ለመተግበር ሀብት ያስፈልጋል፤ ሀብቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ሀብቱ የተደመረ ክንድ ነው። ሀብቱ የእኛ መሰባሰብ የሚያመጣው ነገር ነው ብሎ ማሰብ፤ ከመንግሥት ቋት የሚታሰብ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ሊከውኑት ይችላል የሚለው ሀሳብ፤ሀሳቡም የሀብቱም ምንጭ በጣም አስደማሚ ነው።
ሦስተኛ ይህንን ሀሳብ እራሱ ለኢትዮጵያውያን በወጉ ሸጦ ሁሉ እንዲገዛው አድርጎ ጉልበቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን እንዲሰዋ ማድረግ። አራተኛ መቶ ሰላሳ ሺህ የሚገመቱ የሚታወቁ ነርሰሪዎች በሀገር ደረጃ መገንባትና በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ የማምራት አቅም በተግባር መፈጠሩ ያስደምማል ፣ እነዚህን ኢኒሼቲቮች ለየት የሚያደርጋቸው በዘመቻ መልክ ሳይሆን አንድ ጊዜ ይጀመሩና በየዓመቱ እየሰፉ እየጎለበቱ ብዙ ሰውም እያቀፉ በጥራትም በብዛትም እያደጉ የሚሄዱ ናቸው።
ስንጀምር የተተከለው ችግኝ መጠን ይህንን አያካልም። ስንጀመር የተከልነው ችግኝ በሬሾ ቢታይ ከሃምሳ በመቶ በላዩ እንደዛሬው ለልዩ ልዩ ጥቅም መዋል የሚችል አልነበረም። አሁን ሃምሳ አራት በመቶ የሚሆነው ለብዙ ጥቅም የሚውል ችግኝ እየተተከለ ይገኛል። ይህንን የበለጠ እያስቀጠልነው የምንሄድ ይሆናል።
ስድስት፤ በየዓመቱ ሳናቋርጥ ስለሠራን ነው አርባ ቢሊዮን የደረስነው። አንድ ዓመት ብናቋርጥ ኖሮ እዚህ አንደርስም ነበር። አርባ በመድረሳችን ያገኘነው ጠቀሜታ በችግኝ ተከላ ሰው እየተለማመደ መሄዱን ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ከአሶሳ ወደ ጉምሩክ ስንሄድ የምናያቸው በግሪን ሌጋሲ ዘመን የተተከሉ ችግኞች ጫካ እየሆኑ ነው። በተመሳሳይ በአዲስ አበባና በሌሎችም አካባቢዎች ስንዘዋወር የምናያቻውና በየሰው ጓሮ እየተፈጠሩ ያሉ አረንጓዴዎች እየጨመሩ ሲሄድ አንዱ አንዱን እየደገፈው የሚታይ የሚጨበጥ ውጤት እየሆኑ መጥተዋል።
እኛ በዚህ ረገድ በቡና እና በፍራፍሬ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተመልክተናል። ይህንን በአይን ብቻ ለሚያዩ ሰዎችም የሚያስደምም ውጤት መገኘቱ የሚታይ ነው። ኢትዮጵያ በርሃማ፤ገላጣ ነች ብለው የሚያስቡ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጣ ብለው ማየት ይችላሉ። በጣም የሚያስደምሙ ጫካዎች አሉ ይህ ደግሞ እያበበ እየጎመራ እየመጣ ስለሆነ የአረንጓዴ አሻራው ሥራ ቦግ እልም የሚል ሳይሆን ባህል እየሆነ ያለ ነው። ይህም በቅድሚያ ሀሳብ …ቃል ……ጅማሮ….. ድግግሞሽ…. ባህል እየሆነ ሲሄድ የምናስበውን፤ በደንብ የለበሰች ለአይን የምታምር የምታጓጓ በቂ ምግብ፤ በቂ ዝናብ የምታመርት ሀገር ለመፍጠር በእጅጉ የሚያግዝ ይሆናል።
በእውነት የተሠራው ሥራ የሚያስደምም ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ማመስገን ትብብራቸውን ማድነቅ፣ እንደዚህ አይነት ትልልቅ ነገሮችን በጋራ አቅዶ የመሥራት ልምምዳችንን ማስፋፋት ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ታድጋለች፤ትበለጽጋለች። ከተደመርን ከተሰበሰብን ሁላችንም ልማታዊ በሆነ መንገድ ከተሰባሰብንና አስበን ከተገበርን ከለፋን ማለት ነው።
አንዳንድ ሰው አንድ ችግኝ ሳይተክል ስለ ችግኝ ብዙ ያወራል። አሁን ማውራት ሳይሆን አፈር መንካት ፣መትከል፣ ሥራ መሥራት ይጠበቃል። ለምሳሌ አስር ችግኝ ተክዬ ሦስት ከበቀለ ሦስት መሆን የለበትም አራት መሆን አለበት፤ ለዚህም ደግሞ አፈር መንካት ያስፈልጋል። ቁጭ ብሎ ሰባቱ ተበላሹ እያሉ በመተረት የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። ይልቁንም አራት አምስት ስድስት እያሉ ከተተከለው አብዛኛው እንዲያድግና ፍሬያማና ውጤታማ እንዲሆን በተደጋጋሚ መሥራት ያስፈልጋል፤በመተንተን ሳይሆን ፤በተግባር መሥራት ይጠይቃል።
አንዱ አስደማሚ ምእራፍ ብለን የምንወስደው ሌሎች ሀገራት በቀላል መንገድ በጥቂት ዓመታት አርባ ቢሊዮን ችግኝ ተከልን ማለት የማይችሉትን እኛ በስድስት ዓመት ለማሳካት ችለናል። ሌሎች ሀገራት የተለየ ሀብት “ሪሶርስ” ሳያስቀምጡ ሰው በገዛ ፈቃዱ ገንዘቡን አውጥቶ ለነገ ኢንቨስት የሚያደርግበት ልምምድ እምብዛም የለም።
ከእኛ በላይ የተከሉ ሀገራት በረዥም ጊዜ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ መንግሥት ብዙ ገንዘብ አፍስሰውበት እንጂ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ጊዜና ገንዘብ አውጥቶ የሠራበት አይደለም። ይህንን ስናይ የኢትዮጵያውያን ልዩ ባህሪ ነው። ይህንን ልዩ ባህሪ መጠበቅ ማስፋት ያስፈልጋል። ማናናቅ ፣ማራከስ አያስፈልግም። ምክንያቱም ውጤት ስላለው ብቻ ሳይሆን ልምምዱ በራሱ መጎልበት ስላለበት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በቀጥታ ከህዳሴ ጋር ይያያዛል ዘንድሮ በተጨበጭ ያየነው ውጤት ምን ያክል ትስስር እንደላቸው የሚያሳይ ነው።
ህዳሴ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ስንመጣ ምንም ውሃ አልያዘም። ይሄ ግድብ እንደዚህ አይነት ምልከታና እይታ አልነበረውም። ጫፍና ጫፍ ላይ የተሠሩ ግድቦች አሉ መሀለኛው ፓርት በጣም ዝቀ ያለ ነው። ውሃ ልክ እንደ ኖርማል ሂደቱን ጠብቆ የሚጓዝ ስለነበረ ከሚተላለፈው ውሃ ያለፈ የመያዝ ሙከራም ልምምድም አልነበረም። ግደቡ ያለበት ደረጃ ለዚያ እድል የሚሰጥ አልነበረም።
ዛሬ የህዳሴ ግድብ ወደ ኋላ ከ205 እስከ 210 ኪሎ ሜትር ተኝቷል። ዛሬ የህዳሴ ግድብ ወደታች ጥልቀቱ መቶ 133 ሜትር ደርሷል። ዛሬ ህዳሴ ግድብ የጣናን ሀይቅ እጥፍ አድጓል። ጣና እስከ 30 ቢሊዮን ነው።
ይሄ 62 ነጥብ አምስት ነው፤ደብል አድርጓል። የጣና ውሃ ስፋቱ ብቻ ሳይሆን በጣም ሻሎው ነው። 13፣ 14 ሜትር ነው ጥልቀቱ። ይሄ 133 ገደማ ሜትር ጥልቀት አለው። በጣም ጥልቅ ነው ማለት ነው። ወደታችም ወደኋላም ወደጎንም በጣም ሰፊ ስለሆነ የጣናን እጥፍ /ደብል ውሃ ሆኗል።
ምን ማለት ነው ይሄ 62 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ማለት ምን ማለት ነው፤ ውሃ ገድብን ያዝን ማለት ነው፤ በገንዘብ በጊዜ ቢሰላ በሰው ሕይወት ድጋፍና ምክንያነት ቢሰላ ምን ማለት ነው የሚለውን ደግሞ ማየት ያስፈልጋል። አንድ ኪዩብ ማለት አንድ ሺ ሊትር ማለት ነው። ይህ እንደ አንድ ተቆጥሮ 62 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው።
አሁን በመጠጥ ውሃ እናስበው አንድ ሰው በአማካኝ ሦስት ሌትር ውሃ በቀን ይጠጣል ብለን ብናስብ አንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ በወር ሦስት ጊዜ 30 ብንል 90 ስለሆነ በ12 ብናስብ አንድ ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በቀን አንድ ሰው ይጠጣል ማለት ነው። ይሄ በሰዎች ስናስበው አንድ ሰው ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ቢጠጣ 62 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሰው ለአንድ ዓመት የሚጠጣውን ውሃ ይዘናል ማለት ነው። የዓለም ሕዝብ 62 ቢሊዮን አይሞላም። ከስምንት በላይ ነው ግድ የለም አስር እናድርገውና 10 ቢሊዮን ሕዝብ በቀን ሦስት ሊትር ውሃ ቢጠጣ ለስድስት ዓመት የዓለም ሕዝብ ይሄንን ውሃ እየጠጣ ሊኖር ይችላል።
የዓለም ሕዝብ በርካታ የሚጠጣው ውሃ ስላለው ከኛ አይሻም ብለን ካሰብን ያንን 10 ቢሊዮን ወደኛ 100 ቢሊዮን ብናሳንሰው 100 በ10 ፣ በ100 በ10 እያደረግን ምን ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍሬሽ ውሃ በጣም ንጹህ ውሃ / የተፈጥሮ ንጹህ/ ውሃ ምን ያህል ዘመን ሊጠጣ እንደሚችል ማሰብ ይቻላል። ኢነርጂውን ትተን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ብቻ እንኳን ቢሰላ እጅግ አስደማሚ (ሚራክለስ) የሆነ ውጤት ነው።
በጣም የሚደንቅ ውጤት ነው። ያው እንዳያችሁት ህዳሴ እንኳን ሥራው ከአንዱ ጫፍ አንዱ ጫፍ ተጉዞ ማየትም እጅግ አድካሚ ነው። ሰዎች በቲቪ እንደሚያዩት አይደለም ህዳሴን በንግግር ሊገለጥ አይችልም፤ በቪዲዮ ሊገለጥ አይችልም። ህዳሴ ከንግግርም ከቪዲዮም በላይ ነው። ብዙዎች አይተውም ነክተውም ካላዩት በስተቀር ምንያህል ግዙፍ ሥራ እንደሆነ መገንዘብ ያስቸግራል።
ከመጠጥ ውሃ ባሻገር በገንዘብም ብናስበው 1ሺ ሊትር ውሃ አንድ ዶላር ነው ብለን እናስብ። አሁን ያየዝነው ውሃ 62 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ይዘናል። አንድ ሰው አንድ ዓመት የጠጣው ውሃ በአንድ ዶላር ታሰቦ በትክክል ቢሰላ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። 62 ቢሊዮን ውሃ ከያዝን 40 ቢሊዮን ችግኝ ከተከልን መቶ ቢሊዮን ለነገ ኢንቨስት አደረግን ማለት ነው። መቶ ቢሊዮን ለምግብ ለልብስ ለመኪና ለአስፓልት ለቤት ግንባታ አሁን ለምንገለገልባቸው ጉዳዮች እንገለገልበታለን።
አስፓልት ዛሬ ገንብተን ነገ እንገለገልበታለን። ቤት ዛሬ ገንብተን ነገ እንገለገልበታለን። በእንደዚህ መንገድ በሆነበት ሰዓት እና የተከማቸ፣ የተቀመጠ ወረት ሲሆን ለየቅል ነው። ዛፉም ዛሬ ብንጠቀምበትም በቅድሚያነት ለነገ የሚሠራ ነው። ውሃውም ዛሬ ብንጠቀምበትም በቅድሚያነት ለነገም የሚሠራ ነው። ሲሰናሰል 100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ለልጆቻችን ኢንቨስት አደረግን ማለት ነው።
ይሄ በጣም በጣም አስደማሚ ነገር ነው። በድህነት ለተሳለቁብን ከዚያ ካላችሁበት የድህነት አረንቋ አትወጡም፤ የብልጽግናን ሽታ አታዩትም፤ መልማት አይቻላችሁም፤ መሻገር አይሆንላችሁም፤ ለናንተ የተገባ እና የተፈቀደ አይደለም፤ ላሉን ግለሰቦች እና ቡድኖች ሕዝብ ከወሰነ ሀገር ከወሰነ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ህዳሴም የአረንጓዴ ዐሻራም ያሳያሉ።
በጣም በርካታ ልንገልጻቸው የምችላቸው ሥራዎች አሉ። እነዚህ ሁለቱን የማተኩረው ተሳሳቢ ስለሆኑ እና ለአንድ ግብ የሚሠሩ ስለሆኑ ነው። ይሄ ግድብ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሊገነዘቡ የሚገባቸው ሀሳብ እና ገንዘብ እንዲሁም ጊዜ ብቻ አልገነባውም፤ ደምም ጭምር ነው የተገነባው። ይሄንን ግድብ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በተለያየ ነገር ፣በተለያየ ግንባር ፣ በተለያየ አቅጣጫ ተይዛ ሳለች ቢበዛ ወይም ቢያንስ 15 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ቡድኖች፣ የውጭ ኃይሎች አሰልጥነው በህዳሴ ጉዳይ ብቻ አሰማርተውብናል፤ በህዳሴ ብቻ።
ሲሚንቶ ከማምረት አጓጉዞ እዚህ ቦታ እስካለው ሥራ 15 ሺህ የሚጠጋ የተለያየ ስም ያላቸው በመነሻነት የኛ የሆኑ፤ ግን የተገዙ ፣የተሸጡ ሰዎች ይሄ ሥራ አሁን ያለበት ደረጃ እንዳይደርስ፣እንዳይቋጭ ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ ሕይወት አጥፍተዋል።
ብዙ አልተናገርንም፤ ምክንያቱም ለንግግር አይመችም። አሁንም ዘርዝሬ አልገልጸውም። ነገር ግን ሰው ለግንዛቤ እንዲያመቸው አንድ ተርባይን ሲመረት፣ ሲገዛ፣ ከፋብሪካው ጅቡቲ እስኪደርስ ያለውን ጣጣ ትቼ ያው ገንዘቡም ችግር ነው። ከተመረተም በኋላ ጅቡቲ ማድረሱም ከባድ ነገር ነው። እሱን ትቼ ከጅቡቲ ወደብ ያለውን ሂደት ጨርሼ እዚህ ቦታ ለማድረስ ምን ያክል ቀን የሚወስድብን ይመስላችኋል፤ በትንሹ 45 ቀናት አካባቢ ይፈጅብናል።
አንድ ተርባይን ከጅቡቲ ተነስቶ እዚህ እስኪመጣ በዝቅተኛ 25 ኪሎ ሜትር በቀን ይጓዛል በጣም በከፍተኛ ከተጓዘ 40 ኪሎ ሜትር በቀን ይጓዛል። በየ40 ኪሎ ሜትሩ እያደረ ነው የሚመጣው፣ ከዚህ ጅቡቲ ስንት እንደሆነ ማስላት ይቻላል። በየ40 ኪሎ ሜትሩ አንድ አንድ ቀን ይፈጅበታል። ትልቅ ነው መኪናው የተለየ ነው። በፍጥነት መጓዝ አይችልም በጣም ሳይፈጥን እንደሰው ቀስ እያለ ነው የሚጓዘው አንድ ተርባይን ከጅቡቲ አንቀሳቅሰን እዚህ ለማድረስ 45 ቀናት ይፈጅብናል።
ይህ በመደበኛው መንገድ መኪኖቹ ምንም እንቅፋት ሳይገጥማቸው ሲጓዙ ነው። ነገር ግን ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ተርባይኑ ቀርቶ ሲሚንቶ ከደርባ እዚህ ስናመጣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እያዳንዱን መንገድ አስፓልት ስላልሆነ ለእያንዳንዱ ትራክ ፈንጂ እየለቀመ አልፎ አልፎም አደጋ ሲያጋጥም እየተጋፈጠ ፈንጂ እየለቀመ ነው የሚጓዘው። ከደርባ ተጭኖ ዝም ብሎ እዚህ አይደርስም።
አንዳንድ ጊዜ 20፣30ና 40 መኪና እየጫነ፣ እያዳንዷን መኪና እየፈተሸ ነው ትራንስፖርት አድርገው እዚህ የሚደርሱት። ፈንጂ ስለሚቀበር በየመንገዱ። መሀል ላይ መንገድ ተበላሽቶብን ነበር መንገዶቹ ፒስታ ስለነበሩ ተበላሽተው ጠጋኝ ኮንትራክተር አላገኘንም፣ ብዙዎቹ ኮንትራክተሮች ካለው መሠረታዊ ችግር አንጻር አልፈለጉትም። መከላከያ መንገድ እየጠገነና እየሠራ ፈንጂ እየለቀመና ትራንስፖርት እያደረገ በየቦታው ደግሞ የሚያጋጥመውን ችግር እየተዋጋ ነው ይህንን ግድብ ያጠናቀቀው። ብዙ አልቅሰንበት፣ ደክመንበት፣ ደምተንበት ነው የሠራነው።
እኛ ያለ የሌለ አንጡራ ሀብታችንን ሰብስበን፣ ለምነን ተለቅተን ዜጎች ያላቸውን አዋጥተው ይህን መልካም ነገር እንሥራ ሲሉ፣በሌላው አንግል ደግሞ ያላቸውን ሀብት ጊዜ አውጥተው በዓለም አቀፍ ጫና ለመፍጠር በሀገር ውስጥ ለማስታጠቅና አስፈላጊውን ሎጅስቲክስ ለማሟላት ሀብት መድበው የሚሠሩ አሉ። አንደኛው ለልማት ሌላኛው ለጥፋት። በዚህ ሁሉ ውስጥ ነው ይሄ ግድብ ዛሬ እንዲህ አስደማሚ በሆነ መንገድ ወክ እያደረገ ውሃውን ይዞ ያየነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ መገንዘብ ያለበት ሁለት ቁልፉ ጉዳዮች ናቸው። አንደኛው ለማደግ፣ ለመለወጥ ፣ ለመቀየር ስንወስን እኛ መልካም ነገር ስላሰብን ዓለም ሁሉ በዚያ መልካም ነገር አጨብጭቦ የሚቀበለን ስላልሆነ ከወትሮ በተለየ መንገድ መደማመጥ፣ መናበብ ለጋራ አላማ አብሮ መቆም፣ ባለን ጉልበትና አቅም ገንዘብ ሁሉ መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ ያን ካላደረግን በቀር ስንዴውም ግሪን ሌጋሲውም ኮሪደሩም ህዳሴውም በዋዛ ፈዛዛ ሊሳካ አይችልም፤ በጣም በጣም አድካሚ ነገር ነው። ትብብሩ መደመሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። በሌላ መንገድ ሁለተኛው ኢትዮጵያውያን ቢያስተውሉ ቢማሩ ብዬ የማስበው ይሄ ግድብ ወይም ግሪን ሌጋሲ ከኛ መንግሥት ጋር ምንም ትስስር የለውም። ይሄ ግድብ ቀጥታ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቀጣይነት ካለው የትውልድ ቅብብሎሽ፣ሀገርን ከማስቀጠል ፣የሀገር ህልውናን ከማስቀጠል ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው።
የፖለቲካል ዓላማ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንም አላፊ አግዳሚ ዜጋም ቢሆን ነገ የሚረከባት ሀገር፤ ነገ የሚኖርባት ሀገር እሱ እንኳ ባይኖር ልጆቹ የሚኖሩባት ሀገር የተሻለች ፣የላቀች እንዲሆን መመኘቱ ግድ ነው። የፖለቲካ ዓላማ ይዞ ሲያበቁ የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ ፍላጎት፣ የጋራ የሆነ ህልም፣ የጋራ የሆነ ራዕይ ሰዎች ህሊና ስላላቸው ማስተዋልና የጋራ የሆነውን ነገር ከታክቲካል ፍላጎት መለየት አለባቸው።
እንደ ህዳሴ ግሪን ሌጋሲ ባለ ጉዳይ ሁሉም ሰው መረባረብ አለበት። የሌላ ጠላት ምክርና መሻት እየሰማ የልጆቹን እጣፈንታ የሚያበላሽ መሆን የለበትም። አይቀርም ተቃርኖዎች ፣ ጭቅጭቆች፣ ክርክሮች አንዱ በአንዱ ላይ ይኖራል። የሰው ልጅ ባህሪ ነው። የሰው ልጅ ከወረሳቸው ክፋቶች አንዱ በወንድሙ ላይ ባልተገባ መንገድ መነሳት ነው። አይቀርም ይሄ፤ ነገር ግን የጋራ የሆነ የመጨረሻ ትልቁን ህልም በማደናቀፍ ደረጃ መረባረብ ተገቢ አይደለም።
ለምሳሌ ህዳሴ 50፣60፣ 100 ዓመት የሚቆይ ነገር ነው። እኛ ግን 50 ዓመት አንቆይም። ልጆቻችን ከነሱም በኋላ የሚፈጠረው
ትውልድ የሚጠቀምበት፣ ያ ትውልድ ማን እንደሆነ አሁን መወሰን አይቻልም። የኔ ነው ፤የሱ ነው፤ ያንተ ነው ማለት አይቻልም፤ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙበታል። እና ለጠላት ስንገዛ ፤ከጠላት ስናብር ፤የጠላትን ሃሳብ ስናራምድ በታክቲክ ደረጃ / ሌቭል የሚጎዳን ነገርና በስትራቴጂ ደረጃ/ ሌብል የኛኑ ጥቅም መልሶ የሚጎዳ መሆኑ በጣም መለየት ያስፈልጋል።
ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ህዳሴ ላይ የከፈልነው ዋጋ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቁምነገሩን ስትራቴጂክ እሳቤውን በወጉ ተገንዝቦ ቢሆን በዚያ ደረጃ ባልከፈልን ነበር። ከዚህ መማር ያስፈልጋል። ገና ትላልቅ ህልሞች ትላልቅ ሃሳቦች ስላሉ ሲወጡ በነዚያ ጉዳዮች ላይ ትብብር ያስፈልጋል።
በእኛ በኩል ችግር የለም። ወስነናል፤ በዛው መሠረትም እየሠራን ነው። ተኝተን አናድርም። አናንቀላፋም። ያንን እስክንሠራ ድረስ እንተጋለን። ብዙው ኢትዮጵያዊ ያንን ተረድቶ እየሠራ ነው። ትላልቅ ሀሳቦች አሉ። እነዛ ሲወጡ መተባበር ያስፈልጋል። ሕዝቡ ከጎናችን ቆሞ ያው እንደሚታየው አስደማሚ ሥራ ይሠራል። ነገር ግን ከዛ መሻገር አለበት። ይህ ለአፍሪካ ሁሉ ብርታት ነው። ለአፍሪካ ሁሉ ኩራት ነው። ለካ እኛም እንችላለን የሚል ተነሳሽነት መፍጠሪያ ነው። ይህ በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ስለሆነ ማለት ነው። የያዝነው ውሃ፤ የያዝነው ሀብት ምን እንደሆነ ቅድም ተናግሬያለሁ።
አፍሪካ ሲባል የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራትንም ጭምር ማለት ነው። ሱዳንና ግብፅ በጣም መደገፍ ያለባቸው ግድብ ነው። የሰሞኑን የዳታ መረጃ ብንወስድ ይህ ግድብ በቀን እስከ ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብክ ውሃ በየቀኑ ይይዛል፤ ይህ ማለት በየቀኑ አንዳንድ ቢሊዮን ከያዘ ይህ አጠቃላይ አቅሙ 74 ቢሊዮን ስለሆነ በ74 ቀን ውስጥ ሙሉ ግድቡን መያዝ እንችላለን ማለት ነው። እንደው አንዳንዴ ሽርፍራፊ ስላለ፣ በ100 ቀን ውስጥ ይሄ ግድብ ከዜሮ ሙሉ መሆን ይችላል።
መቶ ቀን ይህንን የሚያክል ውሃ አይገኝም ያው ጊዜው ስለሚወጣ ስለሚወርድ ሀሳቡን ለመጨበጥ እንዲመቸን ነው። በመቶ ቀን እንደዚህ አይነት አስር አስራ አምስት ግድቦች ኖረውን ውሃ ብንይዝ በማንኛውም ሰዓት የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ተጨማሪ ውሃ ቢያስፈልጋቸውና ወንድሞቻችን ሆይ ለዚህ ለዚህ ጉዳይ ፈልገናል እርዱን ብለው በቀላሉ መጠቀም ይችላሉ። ይህ ግን ሊሆን የሚችለው ከያዝነውና ካለን ነው።
አንድ ምሳሌ ላንሳ በዚህ ዓመት ከላይ ከግድቡ መፍሰስ የለበትም፤ የመጨረሻ ከላይ የሚፈሰው ባለፈው ዓመት ነው ተባብለን ነበር፤ ያን ያልንበት ምክንያት በመካከለኛው ግድቡ ክፍል ላይ እንደምታዩት የግድቡ ክፍል አልቋል። አሁን የቀረው የሚተከሉ ፒላሮች ናቸው፤ ከሱ በላይ የሚኖረው ብረት ነው፣ ድልድይ ነው የሚኖረው።
አሁን በዚህ ዓመት አረንጓዴ ዐሻራ ተጨምሮ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እና ውሃ ስላለ በየቀኑ የምንይዘው ውሃ በጣም ትልቅ ነው። ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን በጣም ትልቅ ነው። ዛሬ ለማስተንፈስ ባንከፍተው አሁን ባለው ሂደት ብንቀጥል የቀረን ስድስት ሜትር ገደማ ስለሆነ በአስር ቢበዛ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ውሃው ከግድቡ በላይ ይፈሳል። በአስራ አምስት ቀን ውስጥ።
ይህ የጠበቅነው አይደለም። ከወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር በሦስት አራት ዓመት ቢበዛ አምስት ዓመት ሊሞላ ይችላል። ውሃው በቂ ነው ስንል እነሱ ሰባት አስር ዓመታት አድርጉት ሲሉ፣ ይቻላል ስንል የነበረው ይሄ ነው። እኛ ግን ዛሬ ቅድም እንዳያችሁት በሰከንድ 2ሺ 800 ሜትር ኪዩብ ውሃ እየለቀቅን ነው፤አስተንፍሰናል፤ በደቂቃ ሲሆን በስልሳ አብዙት፤በሰዓት ሲሆን በ60 አባዙት ፤በቀን ሲሆን በ24 አባዙት ምን ያክል ውሃ እየሄደ እንዳለ ፤ይሄን በተርባይን ከሚሄደው ውሃ ተጨማሪ ነው። ይህን ያህል ውሃ የምንለቀው ለሁለት ዓላማ ነው።
አንደኛው ዓላማ አስር ቀን ብንቆይ እና ውሃው በመካከለኛው ሞልቶ ቢፈስ የኛ ሥራ ኖቬምበር ዲሴምበር አካባቢ ድልድዩ ያልቃል ብለን ያቀድነውን እቅድ ያበላሽብናል ። ምክንያቱም ውሃው ከፍ እያለ ሲሄድ ከፍተኛ ኃይል ስላለው በሥራ ሊያሠራ አይችልም፤ያሥራ የማይሠራበት ወቅት ደግሞ አንድ ሳምንት አይደለም፤አሁን ዛሬ ቢደፈርስ ሦስት አራት ወር አምስት ወር ጭምር ያውሃ ይፈሳል።ያ ውሃ ፈሶ ዝቅ እስኪል ድረስ ድልድዩ የሚባለውን ነገር አንሠራውም ማለት ነው። እኛ ደግሞ ድልድዩን መጨረስ እንፈልጋለን።
አንድ! ሁለተኛ ብዙ አይመከርም ፤በድልድይ ላይ ውሃ ማለፍም ከዚህ ጊዜ በኋላ አይመከርም። ወይ በተርባይን ማለፍ አለበት፤ ወይም ከዛም ካለፈ በማስተንፈሻው መውጣት አለበት። ሁለተኛው አንጓ ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተርባይን ከሚያገኙት ውሃ በተጨማሪ ያን የሚያክል ውሃ የምንለቅላቸው የእኛ መሻት ፣የእኛ ፍላጎት ውሃ ታች በማሳነስ እኛ ልዩ ተጠቃሚዎች ለመሆን አይደለም።
ይሄ ውሃ የጋራ ሀብታችን ነው። የእኛ ኃላፊነት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ የሚገባንን ያህል ተጠቅመን የሚገባቸውን ያህል ደግሞ ለወንድሞቻችን ማካፈል ነው። አሁን እናካፍል ያልነው ውሃ ነው። ታስታውሳላችሁ ‹‹ግሪን ሌጋሲ›› ን እናካፍል ብለናል። ሲድ ሊንግ ችግኞችን በነጻ እንስጥ ብለናል። ነገ በጣም በቅርቡ ስንዴ እናካፍላለን።
ኢትዮጵያ አድጋ፣ ኢትዮጵያ በልጽጋ፣ ኢትዮጵያ ተለውጣ ወንድሞቻችን እንዲራቡ የሚፈቅድ እሳቤ ካለን ብልጽግና አልገባንም ማለት ነው። ብልጽግና ከገንዘብ በላይ ሆኖ ማሰብ ነው። የራስን ብቃት ማወቅ፤ ያን ብቃት ተጠቅሞ ማሳደግ ያን ያደገን ብቃት መንዝሮ ለብዙዎች እንዲተርፍ ማድረግ እንጂ አቅምን ማወቅ ብቻ አይደለም። አቅምን ማሳደግና መጠበቅ ብቻ አይደለም።ያ አቅም ለብዙዎች ማካፈል ካልቻለ፣ ብዙዎችን መለወጥ ካልቻለ ፣ ብዙዎችን መድረስ ካልቻለ ዋጋ የለውም።
የብልጽግና እሳቤ ገንዘብ ሰብስቦ ምግብ መብላት አይደለም። የብዙዎችን ህይወት መቀየር ነው። በሀገር ውስጥም። ከዛም ባሻገር። ውሃ የምናካፍለው ፣ችግኝ የምናካፍለው፣ ስንዴ እናካፍል የምንለው ነገ የተማረ ሰው ዕወቀት ፣ ልምድ ሌሎችም ሀብቶች የምናካፍለው ዕድገት በጋራ መሆን ስላለበት ነው። እና ለታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ትልቅ በረከትና ሲሳይ ነው።
ዛሬ አሁን በሰከንድ ይሄን የሚያክል ውሃ ተጨማሪ ስንለቅላቸው እነሱ መጠበቅ ከቻሉ ለረጅም ጊዜ የሚጠቀሙበትን ንጹህ ውሃ እየሰጠናቸው ነው። ይሄ ነገር ፣ ይሄ ልምምድ ወደፊትም ይቀጥላል። ሌላው መንገድ ደግሞ እኛ 74 ቢሊዮኑን በአስር ቀን በአስራአምስት ቀን መያዝ አንፈልግም። ተጨማሪ ሥራዎች ስላሉን ያንን ሥራም እንዲያደናቅፍብን አንፈልግም። ለሁለቱም ‹‹ዊን ዊን›› ነው ማለት ነው።
የእኛን ሥራ በሚመለከት እንዳያችሁት በአሁኑ ጊዜ ዛሬ አራት ተርባይን ኢነርጂ እያመረቱ ነው። ባለፈው ሁለት ነበሩ አሁን ደግሞ ሁለት ተጨምሮ እየሰራ ነው። ምንአልባት በሦስት ቢበዛ አራት ወር ገደማ ቢበዛ ዲሴምበር ላይ ተጨማሪ ሦስት ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ። ሰባት ተርባይን ማለት ነው።
ተርባይን ማምረት ጀኔሬተር ማምረት ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ የሚወስደው ጊዜ አለ። ባለቀ ሰዓት እየመጣ እየመጣ የሚገጠም ይሆናል። ነገር ግን “ፔኒስቶኩን“ ካያችሁ ሁሉም “ፔኒስቶኮች “ ተገጥመው አልቀዋል። “በፓዎር ሃውስ“ የሚሠሩ ሥራዎች አብዛኛዎቹ ሥራዎች ተሠርተዋል። ጀኔሬተሮች ሲመጡ እየገጠሙ እየገጠሙ እና እየፈተሸ /ቴስት እያደረጉ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እንደየአመጣጡ የሚቀጥል ይሆናል።
ታህሳስ ላይ ሰባት ተርባይን ኢነርጂ ያመርታሉ፣ ታህሳስ ላይ ቢያንስ ሰባ፣ ሰባ አንድ ቢሊዮን ሜትሪክ ውሃ እንይዛለን። ታህሳስ ላይ ድልድዩ ሙሉ ለሙሉ ገጥሞ እናያለን። ከሞላ ጎደል ታህሳስ ላይ ያለው ሥራ ያልቃል ። በእርግጥ እስከሚቀጥለው ክረምት ድረስ ተጨማሪ የማጠቃለያ /ሪፋይንድ ሥራዎች ይኖራሉ።
አጠቃላይ ሥራው ያልቃል ተብሎ የሚታሰበው የዛሬ ዓመት ክረምቱ ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል። ግን ዲሴምበር ላይ አለቀ ብንልም ችግር የለውም። የቀረው የድልድዩ ሥራ ብቻ ነው። ድልድዩ እንዳያችሁት ምሶሶው ቆሟል። ብረቱን እየበየዱ ማሻገር ነው የቀረው ሥራ። ያ ሲያልቅ የሲቪል ሥራው ታህሳስ አካባቢ መቶ ፐርሰንት ይደርሳል።
ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን በተመለከተ “ፔኒሰቶኩ“ ተገጥሟል፤ ታች ያለው አብዛኛው ሥራ አልቋል፤ ጄኔተሩን እያመጡ የመግጠም ሥራ በገባበት የጊዜ ደረጃ ስለሚሄድ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት አብዛኛው ነገር መልክ እየያዘ ይሄዳል።
ኢነርጂ ማምረትን በሚመለከት ሁለት ሦስት ቁም ነገሮች መያዝ አለባቸው። ለምሳሌ ዛሬ ሁሉም ተርባይን ቢነሳና ብናመርት ለእኛ ፋይዳ የለውም፤ ምክንያቱም አሁን እየተመረተ ያለውን ኃይል በበቂ እየተጠቀምን ስላልሆነ ዝምብለን ብናመርተው የሚፈሰው ውሃ ነው የሚሆነው፤ ኪሳራ ነው የሚሆነው። ፍላጎት /ዲማንድ እየፈጠርን ያንን ለመመለስ በሚያስችለን ደረጃ ነው የምናመርተው።
ሁለተኛ ስርጭት ላይም ችግር ስላለብን አሁን በየቦታው ኢንቨስት እያደረግን ነው። ትራንስሚሽን፣ ሰብስቲሽን እያስፋፋን ስንሄድ የተጠቃሚ ፍላጎት ይኖራል፤ ባመረትነው ልክ ግን ማድረስ ስላልቻልን በማድረሱ በኩል ኢንቨስት ስናደርግ ኢንዱስትሪው እያደገ ሲሄድ ነው የምናመርተው እንጂ ማምረት ስለቻልን ብቻ አምርተን አናፈሰውም።
ያም የራሱ ሆነ የወጪና ገቢ ትንታኔ /ኮስት ቤኔፊት አናሊስስ/ አለው ማለት ነው። አሁን ብናመርት ምን እናገኝበታለን? ነገ ብናመርት ምን እናገኝበታለን? አምርተን ውሃው ቢፈስ፤ ኢነርጂው ቢፈስ፤ ምን ፋይዳ አለው? የሚለው ነገር አብሮ ቴክኒካሊ የሚታይ ነው የሚሆነው።
በድምሩ ህዳሴን ከሞላ ጎደል ጨርሰነዋል። ከእንግዲህ በኋላ ህዳሴ ላይ ሥጋት የለም። ፋይናንሻሊ ስጋት የለንም፤ ቴክኒካሊም አምብዛም ስጋት የለንም። ሊያደናቅፉን የሞከሩ ኃይሎች ገድለውን ሊሆን ይችላል፣ ሰዎችን አፍነውብን ሊሆን ይችላል፣ አንዳንድ መኪና ጎድተውብን ሊሆን ይችላል፤ ግን አላቆሙንም ሥራውን ጨርሰነዋል።
ስለዚህ ያ ሁሉ ጉልበት፣ ገንዘብና ድካም ከንቱ ሆነ ማለት ነው። ያንን ገንዘብ እኛን ለመደገፍ አውለውት ቢሆን ኖሮ በተሻለ ቀና ትብብር ብዙ ነገር ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። እኛን ለማደናቀፍ ገንዘብ ማውጣት ተጨማሪ ሀብትና ጊዜ አባከንን እንጂ አጠቃላይ ሥራው እንዲቆም አላደረገውም።
ህዳሴ ዲሴምበር ላይ / በፈረንጆች የዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ሰባት ተርባይን ኢነርጂ እያመረተ የሲቪል ሥራው ተጠናቆ፣ ጥቂት ሪፋይን የሚደረጉ የፊኒሺንግ ሥራ እየተሠራ በቀዳሚነት የተርባይን እና የፓወር ሃውስ ሥራ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ተጨማሪ ስድስት ወር ፤ሰባት ወር የሚወስዱ ይሆናል ማለት ነው።
እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እንኳን ተባበርን፣ እንኳን ጨከንን፣ እንኳን አብረን ቆምን፣ እንኳን ለሀገራችን ክብርና እድገት የሚገባውን መስዋዕትነት ከፈልን፤ ምክንያቱም ፍሬው ጣፋጭ ነው። መስዋዕትነት ከፍለን ገንዘብ አባክነን መጨረሻ ላይ ይህን መመልከት ባንችል ኖሮ ኪሳራ ነበር።
ነገር ግን ከዛ ሁሉ ጭቅጭቅና መከራ መጨረሻ ላይ ለልጆቻችን 62 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ውሃ ለማኖር ነው። ያን አሳካነው፤ ዛሬ በቂ የሚባል ኢነርጂ አፍሪካ ማምረት እንደምትችል ማሳያ ነው። ይህንን ዛሬ አሳካነው።
እዚህ ቦታ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ስትንቀሳቀሱ እንዳያችሁት ሁሉም ቦታ ጥቂትና በመቶ የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው የውጭ ሰዎች ያሉበት። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላለፉት አስራ ሦስትና አስራ አራት ዓመታት እዚህ ቦታ ቆይተዋል። አንዳንዱ 6 ፣አንዳንዱ 5 እና 3 ዓመታት እየቆዩ ሠርተዋል።
ሥራ ብቻ አይደለም የተሠራው ፤ ይህ ሁሉ ሰው ሰልጥኗል። ለአፍሪካም ብዙ ቦታ ችግር መፍታት የሚችሉ ሙያተኞችን አፍርተናል። ነገ ለምናስባቸው ተጨማሪ ሥራዎች ከባለፈው የተሻለ እርሾ ፣ልምድና አቅም ፈጥረናል። ይህ ነገር እየቀጠለ ከሄደ ኢትዮጵያንም ፣ሱዳንንም ግብፅንም አፍሪካንም ይጠቅማል።
ምክንያቱም የኢነርጂ ቀውስ በአፍሪካ ደረጃ፣ በዓለም ደረጃ አጠቃላይ የእድገት ማነቆ የሆነ ነገር ነው። ኢነርጂ ላይ በበቂ ሁኔታ ኢንቨስት ማድረግ ለማንኛውም ሀገር ለትላልቆቹም ጭምር በጣም ወሳኝ ነው። ኢነርጂ ብቻ መሆኑ ሳይሆን ንፁህ /ክሊን ኢነርጂ መሆኑ ነው። ሃይድሮ በጣም በጣም ጥሩ ኢነርጂ ምንጭ ነው። እንደዚህም ሆኖ ደግሞ ካለን አጠቃላይ ሀብት አንፃር መመንዘር ያለበት ሀብት ስለሆነ ጠቃሚ ነው።
ከኢነርጂ ባሻገር ውሃ በሚቀጥለው ዓለም ውስጥ በጣም በጣም ቁልፍ ነገር ነው። ባለፈው ዓመት ውስጥ ነዳጅ ቁልፍ እንደነበረው በሚቀጥለው ዓመት ውስጥ ውሃ በጣም ቁልፍ ነገር ነው። ውሃን ማባከን ለአፍሪካ ጎጂ ነው። እንደ ሀገርም ጎጂ ነው።
ውሃን በትክክሉ አንድ አርሶ አደር በቤቱ ደረጃ መቆጠብ ከቻለ፤ አንድ ማህበረሰብ በሰፈር ደረጃ ውሃን መቆጠብ ከቻለ፤ አንድ ሀገር በሀገር ደረጃ መቆጠብ ከቻለ፤ ልክ ብር ያላቸው ሀብታም ሀገራት እየተጋገዙ ችግርን እንደሚያልፉት፤ ውሃም ከተቀመጠ ተጋግዘን የችግር ወቅት ማለፍ ይቻላል። ውሃ መቀመጡ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይደለም። ልክ እንደ ኢነርጂ ጠቃሚ (important) ነገር ነው።
ግን እኛ ግድብ ባንገድብ ፣ ውሃ ባይዝ ፣ የግሪን ሌጋሲው (green legacy) ሥራ ባይሠራ ኖሮ ሌላ ኪሳራ ነበረበት። በቂ ዝናብ አናገኝም፣ ውሃው ሲሄድ በከፍተኛ ደረጃ አፈር ይሸረሸራል። ብዛት ያለው አፈር እየተሸረሸረ ይሄዳል። ተራሮች ገላጣ ይሆናሉ። በረሃማነት ይፈጠራል። ወደፊትም የሰው ልጆች ለመኖር የሚቸገሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። አሁን አፈራችንን እንታደጋለን፣ ግሪን ሌጋሲው ስላለ፤ ተጨማሪ ዝናብ እናገኛለን፣ ውሃ እንቆጥባለን።
ከዚያ ግን እናስፋው ካልን ዓሳውን ተመልከቱ። 60፣ 70፣ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ዓሳዎች አሉ። ወደፊት የዓሳ ፋብሪካ እዚህ ስናቋቁም፤ ዓሳዎች በቀላሉ እያወጣን፣ እያዘጋጀን እያሸግን (packed) በሀገር ደረጃም፣ ከሀገር ውጭም ለመጠቀም በእጅጉ ያግዛል። የተራራው አስደማሚ የተፈጥሮ ትእይንት (scenery)፣ ተፈጥሮ ሀብቱ እዚህ አካባቢ ያለው፣ የተፈጠሩ ደሴቶች (highlands) ወይም በርካታ ደሴቶች ተፈጥረዋል። ሪዞርት፣ መዝናኛ እያደረግን ስንሄድ፤ በአገልግሎት ኢንዱስትሪው ተፅዕኖ (impact) አለው። እራሱ በኢንዱስትሪ ተፅዕኖ (impact) አለው። ትልቅ ኢንዱስትሪ ስለሆነ።
በተፈጥሮ (naturally) ከግሪን ሌጋሲው ጋር ተያይዞ በቢሊዮን የተከልነው በዚህ በተፋሰስ ቀጣናው ላይ፤ እሱም በከፍተኛ ደረጃ ውሃው እየጨመረ፤ ግን ደግሞ አፈር ደለል እየሞላ እንዳይሄድ ያደርጋል። ያ ኢንቨስትመንታችን፣ ግድባችን እንዲከላከል ያደርጋል።
በጥቅሉ ከላይ በመግቢያዬ እንዳነሳሁት አስደማሚ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነው ያለነው። ህዳሴን የሚያህል ነገር አንድ ሺህ አንድ ፈተና እያለ ተቋቁሞ መጨረስ መቻል፤ ግሪን ሌጋሲን የመሰለ ነገር ተቋቁመን መጨረስ መቻል፤ ኮሊደር ልማት ብለን በአጭር ጊዜ ውስጥ ትላልቅ ታሪኮች መሥራት፤ ስንዴ ብለን ዛሬ ለብዙ ሀገራት ልምድ የሚሆን ነገር መፍጠር፤ አሁን ሩዝ ላይ፣ ሻይ ላይ፣ ቡና ላይ የጀመርነው ነገር፣ በትምህርት ቤት ግንባታ የጀመርናቸው ጉዳዮች አሁን ባይታዩንም ነጠብጣቦቹ (dots) ሲገናኙ የምናስበውን ብልጽግና ለማረጋገጥ በእጅጉ መሠረት የሚጥሉ ይሆናሉ።
ጅማሮዎቻችን ፍሬ እያፈሩ ሲሄዱ፤ ልምድ እየቀሰምን ስንሄድ አንድ ተለቅ ያለ ሀሳብ እንዴት ማሰብ እንዳለብን፤ ይቻላል? መቼ? በማን? እንዴት? የሚለውን በቅጡ ማሰብና ማዘጋጀት እንድንችል፤ የኢትዮጵያን አቅም ለመመንዘር የሚያስችል ዘዴ (approach) ለመከተል፤ ያን ደግሞ በታማኝነት (devotion) ፣ በየቀኑ በመሥራት እንዴት ማሳካት እንደሚቻል የተሻለ ልምድ አግኝተናል።
እኔ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያ የብርሃን፣ የኢትዮጵያ የለውጥ፣ የኢትዮጵያ የመሻገር ዘመን ጅማሮ ስለሆነ በዚሁ አግባብ ተግተን ከሠራን ያለምንም ጥርጥር ልመናን ታሪክ እናደርጋለን፤ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን፤ መናቅን ታሪክ እናደርጋለን፤ እነሱ ይችላሉ እንዴ የሚለውን ታሪክ እናደርጋለን። ትናንት አባቶቻችን ተዋግተው ዋጋ ከፍለው ነጻነት እንዳስረከቡን ዛሬ ደግሞ እኛ ተዋግተንም፣ ሠርተንም፣ ከፍለንም፣ እንደዚህ አይነት አስደማሚ ታሪክ ለአፍሪካ ማኖር እንችላለን።
አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እዚህ ቦታ መጥተው ማየት አለባቸው፤ መማር አለባቸው፤ እነሱም ይችላሉ። ከተባበሩ ይችላሉ፤ ሀብት ሕዝብ ነው። ለዚች ግድብ አንድ ዶላር ብድር ማግኘት አልቻልንም። አበዳሪ በሙሉ ስላልፈለገ፣ ስላልፈቀደ። ትልቅ ሀብት ነው የወጣው፤ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ነው እዚህ ቦታ ላይ የወጣው። ይሄ ሀብት የወጣው ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ሀብት ነው።
ነገም ለምንሠራቸው ሀብት ማመንጨት እንችላለን። አንደኛ ሌብነት ከቀነስን፤ ተግተን ከሠራን፤ አንዱ የአንዱን እግር እየጎተተ ማደነጋገር ካቆመ፤ መሰብሰብ፣ መተጋገዝ ከቻልን፤ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማሳካት ማከናወን እንችላለን ማለት ነው።
ለዚህ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኘውን ድል፣ያገኘውን ፍሬ በወጉ አገናዝቦ፤ አርክሶ አራክሶ ሳያይ የተከፈለውን ዋጋ በልኩ መመዘን አለበት። አላስፈላጊ ግነት አያስፈልግም፤ በልኩ ማየት ያስፈልጋል። የእርካታ መንፈስ እንዳያጠቃው ነገን አርቆ አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል። ለዚያ ግን ቀን ከሌሊት የሚሠራ፤ የቆረጠ፣ ወቅት/ ሲዝን የገባው። ወቅት/ ሲዝን የማያባክን። የተሰጠውን ጊዜ በሥራ በውጤት ለመተርጎም የሚጥር ከሆነ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የሚጨበጥ ነገር ሀገራችን ውስጥ እናያለን።
በዚህ ሁሉ አስደማሚ ሥራ ውስጥ የፈጣሪ ክንድ፣ የፈጣሪ እጅ ያስደምመኛል። በነበረው ፈተና፣ በነበረው መከራ፣ በነበረው መሳሳብ እንደዚህ አይነት ትልቅ ነገር ሊታሰብ አይችልም። ፈጣሪ በብዙ ነው የረዳን፤ በብዙ ነው ያገዘን፤ በብዙ ነው የቆመልን፤ በብዙ ነው የሠራልን። ለዚያ እጅግ አድርገን ልናመሰግነው ይገባል።
በብዙ ምስጋና፤ በብዙ አድናቆት የተሞላ ውስጣዊ ማንነት ነው ያለን። እናደንቃለን ያንን ደግሞ እንናገራለን። እናመሰግናለን ያንን ደግሞ በጓዳም በአደባባይም እንገልጣለን። ምክንያቱም ብቻችንን ያደረግነው የእኛ ጭንቅላት ነው ያደረገው የሚል የተሳሳተ እሳቤ የለንም። ካለእሱ እርዳታ አይሆንም።
ኢትዮጵያውያን አሁንም መጸለይ አለባቸው፤ አሁንም ማገዝ አለባቸው፤ አሁንም መደገፍ አለባቸው፤ አሁንም ከአሉባልታ ከወሬ መጠለፍ እራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። በየቦታው ያሉ ጉቶዎች፣ እንቅፋቶች፣ ጠላፊ ገመዶች ያስቀሩናል። የድህነት ታሪካችን እንዲቀጥል ስለሚያደርጉ ለሰላም እጃችን የተዘረጋ መሆን አለበት።
በትክክል ልካችንን እና የሌሎችን ልክ የምናውቅ መሆን አለብን፡፤ ዝም ብሎ መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ መመኘት ብቻ ሳይሆን ማወቅ አለብን። በዚህ አግባብ ብንሄድ ይጠቅመናል ብዬ አስባለሁ። እኛን ያገዘን ነገር የረጅም ዘመን ዝግጅት ነው። ረጅም ዓመት ገብቶን ይህንኑ ለማሳካት ረዘም ላለ ጊዜ ሥንሠራ ራሳችን ላይ ሥንሠራ ራሳችን ላይም ከባቢያችንም ላይ ሥንሠራ ስለቆየን አሁን የምናደርጋቸው ነገሮች ቆይተን ያሰብንባቸው ስለሆኑ መመንዘር ብቻ ነው። ሳንዘጋጅ እንደው ሮጥ ብለን የምናዘጋጀው ነገር ቢመጣም ዋጋ የለውም ኪሳራ ነው። አንዳንድ ነገሮችን ቆም ብለው ማየት ይጠበቅባቸዋል።
በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ጉዞ ተስፋ ሰጪ፣ አስደማሚ ነው። ይህንን ተስፋ ፈጣሪያችንን እያመሰገንን፣ እኛ እየተዛዘንን ይቅር እየተባባልን፣ እየታረቅን፣ ሰላምን እያበረታን፣ ሰላም እያበዛን፣ መትጋት መሥራትን ባህል እያደረግን፣ ክብር፣ ታይታ ምናምን ትተን በደንብ ወደ ሥራ እየገባን ከሄድን በጣም አስደማሚ ነገር ከፊታችን እንዳለ ይታያል። እንግዲህ ብልጽግናን እየጨበጥነው፣ እያየነው ነው። ብልጽግና ይህ ነው።
አፍሪካ ላይ የለም፣ ኢትዮጵያ ላይ የለም። ስንመጣ አልነበረም፤ በገንዘብም በሥራም ላይ አልነበረም። ብዙ ውሳኔዎችን ወስነን ሞተን ነው ያሳካነው። አናራክሰውም። ስንመጣ አንድ ሊትር ውሃ አልያዝንም። ዛሬ 60 ቢሊዮን ፕላስ ይዘናል።
ይህ ድል ነው። ብልጽግና ማለት እንደዚህ ዓይነቱን በየቦታው ማየት ማለት ነው። በተለያየ ዘርፍ በተለያየ ቦታ እንደዚህ ዓይነት በጣም ትልልቅ /ግራንድ የሆኑ ሥራዎች ማየት ማለት ነው። እሱን ማድረግ ከተቻለ ለሀገራችን፣ ለልጆቻችን በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ ነገር ነው። እጅግ እጅግ ደስ የሚል ድል ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ።
የሱዳን ወንድሞቻችን እንኳን ደስ አላችሁ። ተጨማሪ ውሃ አግኝታችኋል። ይህም ውሃ የጋራችን ነው ትጠቀሙበታላችሁ። የግብጽ ወንድሞቻችን እንኳን ደስ አላችሁ። ተጨማሪ ውሃ ዛሬ ጨምረንላችኋል። አረንጓዴ ዐሻራ በጣም ዝናብ ስላመጣ አፍስሰንላችኋል፤ ወደፊትም ይቀጥላል።
ተባብረን ተጋግዘን ቀጣናችንን እናሳድጋለን። በዚህ መንፈስ ከሄድን ለሁላችንም ጠቃሚ የሚበጅ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ለመላው የዓለም ሕዝብ፣ ድጋፍ ላደረጉ፣ ላደናቀፉ እንዲሁ አመሰግናለሁ። ያደናቀፉ አበርትተውናል፤ ያገዙ ምስጋና ይገባቸዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵውያን እንደመር፣ አርቀን ነገን እንመልከት፣ ነገን አሻግረን እንመልከት፣ ትልቁን ነገር እናስብ፣ ትልልቁን ነገር እናሳካ። በትንንሽ ነገር ዘመን እና ጊዜ እንዳይባክን እንጠንቀቅ። ያንን ማድረግ ከቻልን መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፤
ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁን። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመሰገነ ይሁን። ይህን የሠሩ እጆች ሁሉ የተመሰገኑ ይሁኑ። እዚህ ያሉ ኢትዮጵውያን ፈጣሪ ዘመናቸውን፣ እጆቻቸውን ይባርክላቸው። በጣም አስደናቂ ትጋትና ሥራ ነው ያየንባቸው። እነርሱም የተመሰገኑ ይሁኑ። ሳሊኒ ኮንስትራክሽን በብዙ ምስጋና ይገባዋል። ብዙ ኮንትራክተሮች እዚህ አሉ፤ ለሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል። ልጆቻችን በዚህ የተሳተፉ ሁሉ ኩራት ሊሰማቸው ይገባል። ሁሉም የከበረ ምስጋና እያቀረብኩ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ደስ ያለን፤ ተከናውኗል፣ ተሳክቶልናል፣ ሰምሮልናል፣ እናም ይቀጥላል ማለት እፈልጋለሁ።
እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም