የኤሌክትሪክ ተጣጣፊ ዊልቸር በወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ

የፈጠራ ሥራዎች እንዲተዋወቁ ምክንያት ከሚሆኑ አጋጣሚዎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ችግሮች ይጠቀሳሉ። ይህ የሚያመለክተን በአካባቢ ላይ ያሉ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የሚደረጉ የጥናት ሥራዎችን ለፈጠራ ሥራዎች ውጤታማነት መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። ለዚህ ነው የአንድ ጉዳይ ችግር ከታወቀ ከ50 በመቶ በላይ መፍትሄው እንደተገኘ የሚቆጠረው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች /startups/ የሚሰሩት የፈጠራ ሥራዎች ጭምር የኅብረተሰቡን ችግሮች መሰረት አድርገው ስለሚሰሩ ጊዜን፣ ጉልበትን እና ወጪን በመቆጠብ መፍትሔ ሲሰጡ ይስተዋላል። ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች /startups/ የተፈጠረላቸውን ምቹ ምህዳር ተጠቅመው ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን ሰርተው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ እየተደረገ ነው።

‹‹ሞቢክስ›› የተሰኘ ዘመናዊ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተጣጣፊ ዊልቸር የሰራው አቤል ማስረሻም ከእነዚህ የፈጠራ ባለቤቶች መካከል አንዱ ነው። አካል ጉዳተኞች እንደልባቸው ሊገለገሉበት የሚችሉበት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ዊልቸር የሰራው አቤል፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ አካል ጉዳተኛ ጓደኛው በዊልቸር ሲቸገር ባየ ጊዜ እሱን ለመርዳት በማሰብ በጊዜው ያለውን በማንዋል የሚሰራ ዊልቸር ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ሀሳብ ይመጣለታል። ይህን ሀሳቡን መነሻ በማድረግ የመመረቂያ ጽሑፉን በዊልቸር ላይ መስራት ችሏል።

አቤል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና የትምህርት ዘርፍ አግኝቷል። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የያዘውን ሀሳብ በማዳበር ዘመናዊ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ዊልቸር የመሥራት ሀሳቡን አጠናክሮ ገፋበት።

‹‹ጃይራቴክ›› የተሰኘ ድርጅት በመመስረት የጓደኛውንም ሆነ የሌሎች አካል ጉዳተኞችን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራ ጀመር። ሀሳቡ ሀሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በማሰብ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ባደረገው ጥናት በሀገር ውስጥ በቂ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ዊልቸር አለመኖሩን ይረዳል። ይህም በኤሌክትሪክ የሚሰራ ዊልቸር ለመሥራት እንደሚችል በማመን ሀሳቡ እውን እንዲሆን ቀን ከሌት እንዲተጋ ምክንያት ሆነው።

አቤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ጀምሮ የፈጠራ ሥራዎች መሥራት የጀመረ ቢሆንም፣ ድጋፍ የሚሰጠውና የሚያበረታታው በማጣቱ በመሀል ትቶት ነበር። አሁን ለፈጠራ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ እያገኘ መምጣቱ እንደገና ወደ ጥረቱ እንዲመለስ አድርጎታል።

የፈጠራ ሀሳቡን ይዞ ሲነሳ በቅድሚያ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፤ በዚህም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል ቢሆንም፣ ከውጭ ሀገር የሚገቡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ዊልቸሮች መኖራቸው ተመልክቷል። አቤል በዳሰሳ ጥናቱ እነዚህም ቢሆኑ የአገሪቷን መሠረተ ልማቶች ያገናዘቡና የሚመቹ አለመሆናቸውን ይረዳል፤ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ‹‹በእኛ ልክ መሥራት ብንችል እነዚህን ችግሮች መፍታት ይቻላል›› ብሎ በማሰብ ወደዚህ ሥራ እንደገባ ይናገራል።

ከውጭ የሚገቡት አብዛኛዎቹ ዊልቸሮች ተመሳሳይ አይነት ናቸው፤ የአገሪቱን መሠረተ ልማት ከግንዛቤ ያላስገቡና ዋጋቸውም ቢሆን ውድ ስለሆኑ የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ከግንዛቤ ያስገቡ አይደለም የሚለው ወጣት አቤል፤ አዲሱ ዊልቸር ግን የአገሪቱን መሠረተ ልማት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚመረትና ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ እንደሚሆን ይገልጻል፤ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ ለመሥራት በማሰብ እንደ ጀመረው ይናገራል።

መረጃዎችን ዋቢ እንድርጎ እንደገለጸውም፤ በአፍሪካ ከ80 ሚሊዮን በላይ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ10 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ዊልቸር ተጠቃሚዎች ከአንድ በመቶ በታች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ የተቀሩት ደግሞ ካገኙ በእጅ የሚገፋውንና ካላገኙም ደግሞ ክራንች እንደሚጠቀሙ ተናግሯል። አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ደግሞ ምንም አይነት ዊልቸር መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው በቤት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አቤል ጠቁሟል።

አቤል እንደሚለው፤ ከእነዚህ የአካል ጉዳተኞች በአብዛኛዎቹ ዊልቸር የማይጠቀሙበትን ምክንያት ሲገልጹ ብዙ ጊዜያቸውን በዊልቸር ላይ ስለሚያሳልፉ በዚህም ምክንያትም ለሌላ የጤና እክል ያጋጥመናል ብለው ስለሚሰጉ ነው። የአገሪቱ መንገዶች ለዊልቸር አመቺ አለመሆናቸውም ሌላው ምክንያታቸው ነው።

አዲሱ ፈጠራ ግን እነዚህን ነገሮች ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ አካል ጉዳተኞች ብዙ ጊዜያቸውን በዊልቸር ላይ በማሳለፋቸው ሳቢያ የሚያጡት ምቾት እንዳይኖር ተደርጎ ወይም ምቾት እንዲሰማቸው ተደርጎ ነው የተሰራው። አዲሱ ዊልቸር በኤሌክትሪክ የሚሰራና ተጣጣፊ በመሆኑ እንደልብ ከቦታ ቦታ ይዞ ለመንቀሳቀስ የሚያስችልና ቀላል ነው። በኤሌክትሪክ ባትሪ የሚሰራ መሆኑም ባትሪው በቀላሉ ቻርጅ ስለሚሆን ተመራጭ ነው ሲል ያብራራል።

በተጨማሪም አዲሱ የፈጠራ ሥራ በአስፓልትም ሆነ በኮብልስቶን መንገዶች እንደልብ መንቀሳቀስ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በማይመቹ መንገዶች ላይ ጭምር ምቾትን እንዲሰጥ የሚያስችል መሣሪያ የተገጠመለት ነው። በተለያዩ እክሎች ምክንያት አካል ጉዳተኞች በራሳቸው ዊልቸር መንዳት ባይችሉ እንኳ ሌላ ሰው እንዲነዳላቸው የሚያስችል ገመድ አልባ መቆጣጠሪያ/ ሪሞት/ ተገጥሞለታል። ይህ መቆጣጣሪያ ስለ ዊልቸሩ ሙሉ መረጃ ይሰጣል። ለምሳሌ ስለፍጥነቱ፣ ስለመብራቱ፣ መቆጣጣሪያው ሁሉንም ነገሮች በግልጽ የሚያሳይ ዳታ አለው። አገልግሎቱን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግም የሞባይል መተግበሪያ/አፕሌኬሽን/ተሰርቶለታል።

አቤል እንዳብራራው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ ከፕላስቲክ፣ ብረትና ኤሌክትሪክ ቁሶች የተሰራ ነው። አሁን በፕሮቶታይፕ (በሙከራ) ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ ባለበት ደረጃም የኤሌክትሪክ ዊልቸሩ 30 ኪሎ ግራም ወይም የአሥር ዓመት ልጅ የመያዝ አቅም አለው።

አንድ አካል ጉዳተኛ ዊልቸሩን ለመጠቀም ሲፈልግ ባትሪውን በመንቀል ቤት ውስጥ ባለ ማንኛውም ሶኬት ቻርጅ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፤ ባትሪው አንድ ጊዜ ከተሞላ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ማገልገል ይችላል። አካል ጉዳተኛው ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የመሄድ አቅም / ፍላጎት/ ካለው ተጨምሮ መሥራት ይቻላል። የባትሪው መጠንና ስንት ኪሎ ሜትር መሄድ እንደሚያስችለው የሚያሳውቅ መሣሪያ ተገጥሞለታል። ይህ ደግሞ አካል ጉዳተኛው የሆነ ቦታ ላይ መቆም ቢፈልግ ፍጥነቱን ዜሮ ላይ እንዲሆን አድርጎ ባትሪውን ለመቆጠብ ያስችላል ሲል አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሌላ እስከ 120 ኪሎ ግራም ድረስ መያዝ መሸከም የሚችል /ለአዋቂዎች የሚሆን/ዊልቸር ዲዛይን ተሰርቶ መጠናቀቁንም ተናግሯል። ‹‹ ይህን ዊልቸር ለመስራት የሚያስፈልጉ እቃዎችን ለመግዛት ካፒታል እንደሚጠይቅ ጠቅሶ፣ ድጋፍ የሚያደርግ አካል ከተገኘ መስራት እንደሚቻል አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን ሥራ ብቻውን ሆኖ እየሰራ ሲሆን፣ ሥራውን ለመስራት የሚያስፈልገው የበጀት ድጋፍ ከተገኘ ወደ ሥራ በመግባት ምርቶቹን ማምረት እንዲሁም ለብዙ ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችል ይናገራል።

ለአዋቂዎች የሚሆነውን ዊልቸርም ሆነ እስከ አሥር ዓመት ልጅ የመያዝ አቅም ያለውን ዊልቸር ለመስራት ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች መካከል በሀገር ውስጥ የሚመረቱ እንዳሉም አስታውቆ፣ የተወሰኑት ደግሞ ከውጭ የሚመጡ መሆናቸውን አቤል አመልክቷል። ዊልቸሮቹ በሀገር ውስጥ እንዲመረቱና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ ከውጭ የሚመጡትንም ሀገር ውስጥ ባሉት ቁሳቁስ ለመተካት መታሰቡንም አንስቷል። ከውጭ የሚመጡት ተፈላጊ ግብዓቶች ደግሞ ከባለሀብቶች ጋር በመሆን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነስ እንደሚቻል ይናገራል።

አቤል እንደሚለው፤ ዘመናዊ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ዊልቸር በሀገር ውስጥ መሰራቱ ሁለት አይነት ጠቀሜታ አለው። የመጀመሪያው ጥቅሙ የዊልቸሩ ዋጋ እንዲቀንስ እና ከውጭ ከሚገባው ከግማሽ በታች ቅናሽ እንዲኖረው ያደርጋል። ሁለተኛው ደግሞ ከውጭ የሚመጡት በሙሉ ቢበላሹ እዚህ መጠገን አይቻልም፤ እዚህ መፍታትና መጠገን የሚችል ባለሙያም የለም ሲል ጠቅሶ፣ ይህ ዊልቸር ግን ሀገር ውስጥ በመሰራቱ ቢበላሽ በቀላሉ መጠገን ይቻላል ብሏል።

ዊልቸሩ ሲሰራ አንድ ተጠቃሚ የተወሰኑ ጊዜያት ያለምንም አይነት ችግር እንዲገለገል ለማድረግ ታስቦ መሆኑን የሚናገረው አቤል፤ አሁን ላይ ዊልቸሩን ለመስራት አስፈላጊ የሆኑ ዋና ዋና የሚባሉት መሳሪያዎች ከውጭ ለማስመጣት እየሰራ መሆኑን ይናገራል። ከተወሰኑ ጊዜያቶች በኋላ ግን እነዚህም በሀገር ውስጥ እንዲተኩ እንደሚደርግ ይገልጻል። ይህም የሚደረገው የአገልግሎት ጊዜውን ለማራዘም መሆኑን ያስረዳል።

‹‹ብዙውን ጊዜ እቃዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚያጥረው በቂ ጥገና እና የቴክኒክ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ነው›› የሚለው አቤል፤ እነዚህ በሀገር ውስጥ መመረታቸው ደግሞ ተጠቃሚዎች በቀላሉ የቴክኒክ ድጋፍ የጥገና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ብልሽት ያጋጠመው ዊልቸር በቀላሉ የማይሰራ አይነት ከሆነ ደግሞ በባለሙያዎች እንዲታይ የሚደረግበት ሁኔታዎች እንዳለም ተናግሯል። ይህ ደግሞ የዊልቸሩ የአገልግሎት ዘመን በራሱ ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ገልጿል።

ይህን ሥራ ሠርቶ ካጠናቀቀ ሦስት ወራት እንዳስቆጠረ የሚገልጸው አቤል፤ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማግኘት ሂደት መጀመሩን ይገልጻል። የፈጠራ ሥራ በየጊዜው የሚሻሻል እንደመሆኑ መጠን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህን የፈጠራ ሀሳብ አይቶ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ካገኘ ሥራዎች ለመጀመር እንዳሰበ ይናገራል። አዲሱን የፈጠራ ሥራ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አቅርቧል፤ መስሪያ ቤቱም ድጋፍ ሊያደርግለት ቃል ገብቶለታል።

አቤል እንደሚለው፤ በቀጣይ ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ከተገኘ ወርክሾፕ በማቋቋም ወደ ሥራ በመግባት ዊልቸሩን በፍጥነት ማምረት ይቻላል። ሥራው ሲጀመር ደግሞ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። ምርቶቹን በብዛት በማምረት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይደረጋል። ከዚያ ደግሞ የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን ከተቻለ ወደ ውጭ ኤክስፖርት እስከማድረግ እንደሚሰራ ታቅዶ ይሰራል።

‹‹አሁን ላይ አቅሜ በፈቀደው መጠን የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅሜ ይህንን የፈጠራ ሥራ መስራት ችያለሁ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ትንሽ ጊዜ ወስዶብኛል። ወደፊት ደግሞ መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች በማሻሻል ከዚህ የበለጠ ሥራ ለመስራት እፈልጋለሁ›› የሚለው አቤል፤ የፈጠራ ሥራው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ተፈላጊ እንዲሆን እንደሚሰራም ይገልጻል። ይህ የፈጠራ ሥራ ሀገር ውስጥ መሰራቱ የተለያዩ ነገሮችን በመቀያየር ለሌላ ሥራ የሚውሉ ሌሎች ፈጠራዎች መሥራት እንደሚቻል ያመላክታል። በዚህ ብዙ ዘርፎች ላይ ያሉ ችግሮች መፍታት የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ይገልጻል።

አቤል ‹‹የፈጠራ ሥራ ብዙ ጥረትን ይጠይቃል፤ ካልተሰራና ካልተደከመ ለውጤት መብቃት አይችልም። በፈጠራው ዙሪያ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ይህንን ሥራ እኔ ካልሰራሁት ማን ሊሰራ ይችላል፤ ስለዚህ የሚመጡብኝን ፈተናዎች ሁሉ በመቋቋምና በብልሃት ማለፍ ይጠበቅብኛል›› ይላል። ዊልቸሩ አንድ ችግር ፈቺ የሆነ ምርት ሊሆን ይችላል። እንደ ባለሙያ ደግሞ ከዚህ በላይ መስራትን ይጠይቃልና ሌሎች የሰዎችን ሕይወት ቀላልና ምቹ የሚያደርጉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች በናሙና ደረጃ ሠርቶ ያስቀመጠ ሲሆን፤ በቀጣይ እነዚህ ቴክኖሎጂዎችን በመሥራት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚያደርግ ይገልጻል።

እሱ እንደተናገረው፤ ይህን የፈጠራ ሥራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት በተካሄደው በስትራይድ ኢትዮጵያ ላይ ማቅረብ ችሏል። እንደገና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በኤግዚቢሽን ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ቢኖሩም ወደሥራ ሲገቡ ግን ያለውን ተግዳሮት በብዙ መልኩ ቢሻገሩትም ወደ ገበያ ሲገቡ ግን አይታዩም። የቴክኖሎጂ ዘርፍ ገና ብዙ ያልተነካ በመሆኑ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። በመሆኑም በዘርፉ ለመሰማራት ያሰቡም ሆነ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ሳይሰስቱ አውጥተው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እየተጋፈጡ እስከመጨረሻው ጥግ ሊጓዙ ይገባል ሲል አቤል ምክሩን ይለግሳል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You