
አዲስ አበባ፡- በዞኑ በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ243 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስታወቀ።በሁለት ዓመታት በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎችና ወረዳዎች ከዋና ዋና መንገድና እርስ በእርስ በጠጠር መንገድ ለማገናኘት መታቀዱን ዞኑ ጨምሮ ገልጿል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ243 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ በተሠራው መንገድ በርካታ የገጠር ቀበሌዎች ከዋና ዋና መንገድ ጋር ማገናኘት ተችሏል ያሉት አቶ ላጫ፤ በዚህም የመንገድ ግንባታ በዞኑ ትልቅ መሠረታዊ ለውጦች ከመጣባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
መንገድ በተለይ ለቱሪዝም እድገትና ለኢኮኖሚው መነቃቃት ከሚኖረው ትልቅ ፋይዳ በተጨማሪ የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማዳበር አንድነትን ማጎልበት የሚቻልበት መሆኑንም ነው አቶ ላጫ ያመላከቱት።
እንደ አቶ ላጫ ገለጻ፤ ለመንገድ ግንባታው ኅብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበት እና ግብዓቶችን በማቅረብ በአጠቃላይ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።በቀጣይም አዳዲስ ከሚሠሩት በተጨማሪ ከዚህ በፊት የተሠሩት የመጠገንና አገልግሎት የማሻሻል ሥራ ይሠራል።
እንደ አቶ ላጫ ገለጻ፤ ያለ መንገድ መሠረተ ልማት የዞኑ ሁለንተናዊ እድገት እንደማይረጋገጥ ስለታመነበት የመንገድ መሠረተ ልማት ይበልጥ ትኩረት ተደርጎበታል። የመንገድ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባለሀብቱን፣ አርሶ አደሩን እንዲሁም መላው ማህበረሰብን በማነቃነቅ በመሠራቱ ውጤታማ መሆን ተችሏል።
በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው ከ30 እስከ 60 ኪሎ ሜትር የሚሆን የመንገድ ግንባታ ተሠርቷል ያሉት አቶ ላጫ፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት ለመሥራት በእቅድ የተያዙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዳሉ አብራርተዋል።
አቶ ላጫ፤ የመንገድ ግንባታው በዞኑ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ እድሎች ወደ ውጤት ለመቀየር በተለይ በሌማት ትሩፋት የተመረቱ ምርቶች ከቦታ ወደ ቦታ እንደልብ ለማንቀሳቀስና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም አርሶ አደሮች በአመረቱት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለሌሎች ዜጎችም የሥራ እድል እንዲፈጠር ማድረጉን አስረድተዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም