የ33ኛው ኦሊምፒክ አዘጋጇ ፓሪስ ከሳምንታት እረፍት በኋላ 17ኛውን የፓራሊምፒክ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመቀበል ላይ ትገኛለች። ውድድሩ ከነገ በስቲያ በርካታ የዓለም ሀገራትን በተለያዩ የጉዳት ዓይነቶችና ስፖርቶች ለማፋለም በይፋ ጅማሬውን ያደርጋል። የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከተሳታፊ ሀገራት አንዱ ሲሆን በሀገር ቤት የነበረውን የሁለት ወራት ዝግጅት አጠናቆ ወደ ውድድሩ ሥፍራ አቅንቷል።
እአአ በ1960 ሮም ላይ የተጀመረውን ፓራሊምፒክ ፓሪስ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስተናግዳለች። ኢትዮጵያ ዘንድሮ በመድረኩ ለ 6ኛ ጊዜ በአራት አትሌቶችና በሁለት አሯሯጮች ትሳተፋለች። በ2020ው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በሶስት አትሌቶች ተሳትፋ በአንድ የወርቅ ሜዳሊያ ከዓለም ሀገራት 56ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ቡድን ለተሳትፎው በሆቴል ተሰባስቦ ዝግጅቱን ከጀመረ የቆየ ሲሆን በሚደረግለት ውስን ድጋፍ ልምምዱን ሲያጠናክር ቆይቷል። ለመገናኛ ብዙሃን የቡድኑን ዝግጅት በተመለከተ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ በነበረው የዝግጅት ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሜዳ መምና በተለያዩ ቦታዎች የአየር ንብረቱን እና የውድድር ሥፍራውን ያማከለ ልምምድ ሲደረግ ቆይቷል። ቡድኑ ምንም እንኳን እንደሌሎቹ መድረኮች ሰፊ ትኩረት ባይሰጠውም፤ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች የተሻለ ውጤት በማምጣት በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተመዘገበውን ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።
ኮሚቴው ስለ ቡድኑ ዝግጅት ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ያልቻለበትን ምክንያት ለውድድሩ የሚያስፈልገው ገንዘብ በወቅቱ ባለመለቀቁና ስለ ጉዞው እርግጠኛ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። ዝግጅቱን በማጠናቀቅ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና በፓራሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አማካኝነት ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም ይፋዊ ሽኝትና የባንዲራ ርክክብ በማድረግ ትናንት ምሽት ፓሪስ ገብቷል።
ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በፓራ አትሌቲክስ ውድድር የምትሳተፍ ሲሆን በአራት የጉዳት ዓይነቶች አራት አትሌቶችን አሳትፋ በውጤት ለማጠናቀቅ ትፎካከራለች። በዚህም መሠረት በ1 ሺ 500 ሜትር ርቀት በአራት የጉዳት ዓይነቶች ትወከላለች። በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በጭላንጭል (T-13) ለውጤት ከሚጠበቁት ግንባር ቀደም አትሌቶች አንዷ ናት። ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ሀገርን የምትወክለው አትሌት ያየሽ ጌቴ ደግሞ በአይነስውር (T-11) ትወዳደራለች። አትሌት ይታያል ስለሺ ይግዛው በበኩሉ በአይነስውር ጭላንጭል (T-12) በተመሳሳይ ርቀት ይካፈላል። በቶኪዮው ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ሀገሩን የወከለው አትሌት ገመቹ አመኑ ብቸኛው የእጅ ጉዳት ምድብ ተወዳዳሪ (በT-46) በመሆን ለሜዳሊያ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም ሁለት አጋዥ አሯሯጮች ለነዚህ አትሌቶችን ድጋፍ ይሰጣሉ።
አብዛኞቹ አትሌቶቹ ልምድ ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር ከወራት በፊት ጃፓን ኮቤ ከተማ በተካሄደው የዓለም ፓራሊምፒክ ቻምፒዮና 2 ወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ በማምጣት ለዚህ ውድድር መመረጥ ችለዋል። በወቅቱ ኢትዮጵያ አራት አትሌቶችን አሳትፋ 2 የወርቅ፣ 1 ብር እና 1 ዲፕሎማ በማስመዝገብ ከዓለም 24ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች። ከውድድሩ መልስ ወደ ሀገር ሲመለሱ ባስመዘገቡት ውጤት ልክ አቀባበልና ድጋፍ ባለመደረጉ አትሌቶች ቅር እንደተሰኙ ጠቅሰው፣ በዚህኛው ውድድር የተሻለ ድጋፍና አቀባበል መኖር እንዳለበት አሳስበዋል። በአሠልጣኝ ንጋቱ ሀብተማርያም አማካኝነት ላለፉት ሁለት ወራት ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን በአሠልጣኙና በአትሌቶቹ ትጋት ጠንካራና ለውጤት የሚያበቃ ዝግጅታቸውን በማድረግ በውድድሩ ሥፍራ ከትመዋል።
የክረምት ፓራሊምፕክ ጨዋታዎች ዓለም አቀፍና ብዙ ስፖርቶችን በማቀፍ የሚከናወን ውድድር ሲሆን በተለያዩ የጉዳት ዓይነቶች ውስጥ ያሉ አትሌቶች ይካፈሉበታል። እነዚህ የመንቀሳቀስ ችግር፣ የተለያዩ የአካል ክፍሎች ጉዳት፣ የአይነ ስውርነት እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ስፖርተኞችን አቅፎ ለደረጃና ሜዳሊያ የሚያፎካክር የስፖርት መድረክ ነው።
ውድድሩ እአአ ከነሐሴ 28 እስከ መስከረም 8/2024 ዓ.ም በመካሄድ ፍጻሜውን ያገኛል። ዘንድሮ በሁሉም የጉዳት ዓይነቶች 186 ሀገራት ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ውድድር ከ4ሺ በላይ የፓራ ስፖርተኞች በ22 ስፖርቶችና 529 የውድድር ዓይነቶች ለአስራ ሁለት ቀናት የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል። እስከ አሁን በተካሄዱ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች አሜሪካ በ808 ወርቅ፣ 736 ብር እና በ 739 ነሐስ በጥቅሉ 2ሺ283 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ትመራለች። እንግሊዝ በ 1ሺ 914 ሜዳሊያዎች እና ቻይና በ1ሺ237 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ተቀምጠዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም