የነሀሴ ወር ልጅነታችንን በሚያስታውሱ፣ የአዲስ ዓመትን መምጣት በሚያበስሩ ሁነቶች የተሞላ ነው። ይህን ወር በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንስቶች በናፍቆት ይጠብቁታል። ዋና በዓላቸው ነውና። ይህ ከነሀሴ 16 ጀምሮ የሚከበር በዓል፣ መጠርያው እንደየአካባቢው ይለያያል። አሸንዳ፣ ዓይንዋሪ ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ ፣ ሶለል የሚሉ ስያሜዎች አሉት ።
መነሻው ሃይማኖታዊ ታሪክ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ በዓል ልጃገረዶች በፍጹም ነጻነት ከእኩዮቻቸው ጋር በመሆን እንደልባቸው የሚጫወቱበትና የሚያጌጡበት ነው። በሚሄዱባቸው ሁሉ በእንግዳነት ይስተናገዳሉ፤ በሚጫወቱበት ጊዜም ወንድሞቻቸው የእነሱን ደህንነት ለመጠበቅ አብረዋቸው ይሆናሉ።
በዚህ በዓል ሰሞን ልጃገረዶች የሚያዜሙት ዜማ፣ የሚጠቀሟቸው ግጥሞች እና ሥነ-ቃሎች ለዚህ በዓል ራሳቸውን የሚያስውቡበት መንገድ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል።
በዛሬው የፋሽን ገጻችን በትግራይ አካባቢ የዚህ በዓል ትውስታ ዛሬም ውስጣቸው እንዳለ የሚናገሩ እናቶች ልጃገረዶች በበዓሉ ሰሞን የሚያጌጡባቸውን መዋቢያዎች እና የሚጠቀሟቸውን አልባሳት በተመለከተ አጫውተውናል።
ወይዘሮ ሕይወት አርኣያ አሁን የሶስት ልጆች እናት ናቸው። የአሸንዳ ጨዋታ የሚካሄድበት ወቅት በጉጉት የሚናፈቅ እና የማይጠገብ መሆኑን ያስታውሳሉ። የአሸንዳ በዓል ወጣቶች የሚተጫጩበት መሆኑንም ይገልጻሉ። በአሸንዳ ወቅት ሁሉም ልጃገረዶች እጅግ ተውበው እና አምሮባቸው ነው የሚወጡት። ሁሉም አንድ አይነት እስከመምሰል እንደሚደርሱም ጠቅሰው፣ ከአንዳቸው አንዳቸውን ለመምረጥም ይቸግራል ሲሉ ወይዘሮ ሕይወት ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለአሸንዳ ዝግጅት የሚጀመረውም ከሁለት እና ከሶስት ሳምንት በፊት ቀደም ብሎ ነው። ለበዓሉ አሸንዳ በናፍቆት የሚጠበቅ ስለሆነ ሁሉም ሴቶች የመረጡትን ባህላዊ ልብስ ያሰፋሉ ወይም ወላጆቻቸው ያሰፉላቸዋል፤ ያም ካልሆነ ደግሞ እናቶቻቸው በቤት ውስጥ ይጠልፉላቸዋል።
የአሸንዳን በዓል ለማክበር አሁን የተለያዩ አይነት ጨርቆች ጥቅም ላይ ቢውሉም ትክክለኛው ባህል ግን የሀገር ባህል ልብስ የምንለው ፈትል ወይም የአቡጀዲ ጨርቅ በተለያየ ዲዛይን የተጠለፈ እና ጀርሲ ተብሎ የሚጠራ የሻማነት ባህሪ ያለው ልብስ ለአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች ይጠቀሙበታል ሲሉም ያብራራሉ።
ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ ዓለም ብርሃነ ሲሆኑ ይህ የአሸንዳ በዓል በአክሱም ከተማ ዓይንዋሪ እየተባለ እንደሚጠራ ይገልጻሉ። እሳቸው እንደሚሉትም፤ አሸንዳን በዋናነት የሚጫወቱት ልጃገረዶች ወይንም ያላገቡ እንስቶች ሲሆኑ፣ ልጃገረዶቹ ከመካከላቸው ያገባች ጓደኛቸው ካለች የእሷን መዋቢያ እና ልብስ ለዓመቱ ለመዋስ ቀደም ብለው ቀጠሮ ያስይዛሉ።
ከልብሱ በተጨማሪም ከነሀስ የተሰሩ የአንገት እና የጆሮ ጌጦች እንዲሁም በተለያየ ቀለም ባላቸው ጨሌዎች የተሠሩ የአንገት ግንባር ላይ እንዲሁም ጸጉራቸው ላይ የሚያደርጓቸውን መዋቢያዎችን እንዲሁም ጫማ ወደ ገበያ ወርደውም ይሸምታሉ።
በአንገት ላይ የሚደረጉ ጌጣጌጦች የተለያዩ አይነቶች መሆናቸውን የሚያነሱት ወይዘሮ ዓለም፣ አንደኛው ‹‹ጎባጉብ›› ተብሎ የሚጠራው ጌጥ ሲሆን፣ ሶስት ጥንድ ጌጦችን በአንድ ላይ ይዞ ከአንገት ላይ በጣም ሳይጠብቅ በጥቁር ክር የሚያደርጉት ነው፤ ይህንን ጌጥ ያደረገች እንስት ሌሎች በአንገት ላይ የሚደረጉ ጌጦችን ማድረግ አይጠበቅባትም ይላሉ።
ሌላኛው በአንገት ላይ የሚደረገው ጌጥ የተለያየ ዲዛይን እና መጠን ያላቸውን በጥቁር ክር የተያያዙ መስቀል መሳይ ጌጦች ያሉት ‹‹ሕንቆ›› ተብሎ የሚጠራው ነው። ልጃገረዶቹ ይህን ጌጥ በአንገታቸው ላይ ጥብቅ በማድረግ ያስሩታል ፤ መካከለኛ መጠን ያለውን ደግሞ ቀጥሎ የሚያደርጉት ሲሆን፣ እንደየደረጃጀቸው ወደ አንገታቸው ወረድ እና ረዘም በማድረግ ያጌጣሉ።
በጆሯቸው ላይ የሚያጌጡበት ጉትቻም እንዲሁ የተለያየ መጠን እና ዲዛይን ያለው ሲሆን፣ የእጅ አምባር እና የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን መስቀሎች ይጠቀማሉ። ሌላኛው የሚያጌጡበት ደግሞ ከክር ተገምዶ የሚሠራ ነው። በአንገታቸው አስገብተው ነገር ግን በቀኝ እና በግራ ወገባቸው አጠላልፈው ይጠቀሙበታል። በአብዛኛውም ጥቁር ክር ይጠቀማሉ፤ ስያሜውም ‹‹ሐሪ›› የሚሰኝ ሲሆን፣ እሱም ሐር እንደማለት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንስቶቹ የሚሠሩትን የጸጉር አሠራር በተመለከተ ወይዘሮ ሕይወት ሲያብራሩ፣ ‹‹ያላገባች ከሆነች ጋሜ የሚባል አሠራር ነው ምትሠራው፤ እሱም በመሃል አናቷ ላይ ጸጉሯ የተላጨ ሲሆን፣ ከፊት እና ከኋላ ግን ሹሩባ ትሠራለች›› ሲሉ አብራርተዋል።
ያገቡ እንስቶች አሸንዳ የሚጫወቱ ከሆነ ደግሞ በሚያደርጉት ጌጥ ይለያሉ ይላሉ። ‹‹ያገባች ከሆነች ስታገባ የተሰጣትን ከብር የተሠራ አንድ አይነት የአንገትና የጆሮ ጌጥ ታደርጋለች። በላይኛው የጆሮ ክፍሏም ሸቋር ተብሎ የሚጠራ ጌጥ ታደርጋለች›› ሲሉ ወይዘሮ ሕይወት ያብራራሉ።
ነሀሴ 16 ጨዋታውን ሲጀምሩም የባህሉ ስያሜ እንዲሆን ያደረገውን አረንጓዴ የአሸንድዬ ቅጠል በወገባቸው ላይ አስረው ፣ በአካባቢው ካሉ እኩዮቻቸው ጋር በመሆን ጨዋታቸውን ይጀምራሉ። ልጃገረዶቹ ከቤት ከመውጣታቸው አስቀድመውም በአናታቸው ላይ በስሱ በቤት ውስጥ የተዘጋጀ ንጹህ ቂቤ በእናቶቻቸው እንደሚቀቡ ወይዘሮ ዓለም ተናግረዋል።
ሌሎች እንስቶች ደግሞ በዚህ ቀን የሚያጌጡት አሁን ላይ የምንመለከታቸውን ሰው ሠራሽ መዋቢያዎች ላይሆን ይችላል፤ ባህላቸውን በጠበቀ እና ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ የመጣውን ተፈጥሯዊ መዋቢያ ይጠቀማሉ። በተለምዶው ስር ኩል ተብሎ የሚጠራውን በትግርኛ ደግሞ ኩሕሊ በአካባቢው የሚገኝ የከበረ ማዕድንን በመፍጨት ነጭ ሽንኩርት ካስነኩት በኋላ በእናቶቻቸው በታላቅ እህቶቻቸው አልያም አብረዋቸው አሸንዳ በሚጫወቱ እኩዮቻቸው በአይናቸው ሽፋሽፍት እና ቅንድባቸው ላይ ይኩላሉ ሲሉ ወይዘሮ ሕይወት አብራርተዋል።
ይህ በዓል ከነሀሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሀሴ 21 በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እስከ ነሀሴ 24 ድረስ ይከበራል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም