“ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው“ የሚባል እድሜ ጠገብ አገላለፅ አለ። ሁሉም እስከተቀበለው፤ እቁብ ጣዮችን ሁሉ እስከ ጠቀመና “ሰው እስካደረገ“ ድረስ ብያኔውን ከመቀበል፣ አፅድቆ ከማለፍና የተግባሩ ተሳታፊ ለመሆን ከመጣር ውጪ ምርጫ የለም።
ልክ እንደ “ሰውን ሰው ያደረገው እቁብ” ሁሉ፣ ቁጠባም ሰውን ሰው ሲያደርግ እየተመለከትን ሲሆን፤ ይህም እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ•ም በንፋስ ስልክ- ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው የዘመናዊ ኦቶሞቢሎች ርክክብ ሥነሥርዓት ላይ በግልፅ ታይቷል እና ቁጠባም (ልክ እንዳደጉት ሀገራት ሁሉ) እኛም ጋ ባሕል፤ ከባሕልም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተራማጅ ባሕል በመሆን ላይ መሆኑን ለመጠራጠር ምንም ባዶ ቦታ የለም።
እንደሚታወቀው፣ መንግሥታት (የኢትዮጵያን ጨምሮ) ቁጠባን ለማለማመድና ቆጣቢውንም ሆነ አገርን የኢኮኖሚው ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ቁጠባን ከማበረታታትም አልፈው “በዚህ ዓመት ይህንን ያህል ፐርሰንት (— %) እናደርሳለን” በማለት እስከ ማቀድ ሲሄዱ ይታያሉ። ይህንን ወደ ሀገራችን ስናመጣው ደግሞ በታላቁ ዓባይ ግድብ ግንባታ ምክንያት ተጀምሮ እየተሠራበት ስለመሆኑ በቅርብ የምናውቀው ሆኖ እናገኘዋለን።
የንፋስ ስልክ-ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ካቋቋሙትና ካፒታሉ ከብር 85 ሚሊዮን የዘለለው “ማኅደር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃ/ የተ/ሕ/ሥ/ማ ማየትና መገንዘብ የተቻለውም ይህንኑ በመቆጠብ ያሰቡትን የማድረግ አቅም መገንባት የሚቻል መሆኑን ነው። (እዚህ ጋ፣ በ2009 በጀት ዓመት ብር 1.8 ቢሊዮን በማሰባሰብ ከነበረው 8.7 ቢሊዮን ብር 10.5 ቢሊዮን ለማድረስ ታቅዶ ነበር።
በዚህ መሠረት የተለያዩ የኅ/ሰብ ክፍሎች፤ ማለትም የመንግሥት ሠራተኛው፣ አርሶ/አርብቶ አደሩ፣ ባለሀብቶች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ዲያስፖራው በአጠቃላይ ምዕላተ ሕዝቡ በቦንድ ግዥ፣ በልገሣ እና በገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ላይ እያደረገ ያለው ተሣትፎ በየጊዜው እየጨመረና የቁጠባ ባሕሉን እያሣደገ ነው።
በዚህም መሠረት ከ2008 ዓ.ም. ከነበረው ብር 8,785,540,678.82 ወደ ብር 10,058,979,968.01 ከፍ ብሏል። በዚህም 1,273,439,289.19 ብር በበጀት ዓመቱ በመሰብሰብ የእቅዱን 72.22% ማሳካት ተችሏል። የሚለውን የወቅቱን የመንግሥት ሪፖርት በማሳያነት ጠቅሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናል።)
በሀገራችን የተለያዩ ዘርፎች (መደበኛ ቁጠባ፣ የፍላጎት ቁጠባ፣ የልጆች ቁጠባ ወዘተ) ያሉት ቁጠባ በተለያዩ የቢዝነስ ተቋማትም እየተለመደ የመጣና ታታሪና ባለ ዕድለኞችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለ የቢዝነስ እንቅስቃሴ አካል ስለ መሆኑ ከንግድ ባንክ “ይቆጥቡ ይሸለሙ” ጀምሮ ሌሎች ማስታወቂያዎችና ቁጠባን አበረታች እንቅስቃሴዎች መገንዘብ ይቻላል።
በተለይ በአሁኑ ፈጣንና በአንድ ጊዜ ከኪስ ውልቅ አድርጎ የፈለጉትን የራስ ማድረግ፤ ከባንክ ላጥ አድርጎ በራስ አቅም ብቻ ያሻን መፈፀም ወዘተ እጅግ ከባድ በሆነበት፤ ፈጣንና ለደሀ ቁብ በማይሰጥ ዘመንና ዓለም – – – ውስጥ ልክ እንደ እቁብ ሁሉ ቁጠባም የፈለጉትን ለማድረግ ቀዳሚና አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ከላይ በጠቀስነው ክፍለ ከተማ የሚሠሩትና የቆጠቡት ትጉኃን ሠራተኞችም ያደረጉት ይህንኑ ነው።
ምንም እንኳን፣ በሌላው ዓለም ቁጠባ (saving) እንደ ማንኛውም የቢዝነስ እንቅስቃሴ የእለት ተእለት (ካገኙት ላይ የመቆጠብ) ተግባር ቢሆንም፣ እኛ አገር ግን ቁጠባ የጥቂት ብልሆች ብቻ በመሆን ሺህ ዘመናትን አስቆጥሯል። “ምን አለና ነው፤ ከምኑ ላይ ነው የምንቆጥበው?“ ስንል የነበርን የዋሃን ተጎዳን እንጂ አልተጠቀምንም።
በተለይ “ከሳንቲም ጀምሮ በመቆጠብ የፈለጉት ላይ መድረስ“ እንደሚቻል በሚነገርበት በዚህ “ገንዘብ፣ ገንዘብ- – -“ ባይ ዓለም የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙን ከየትም አምጥቶ መግለፅ አይቻልም። በተለይ በመንግሥት ሠራተኛው አካባቢ ይህ ከምኑ ላይ ነው – – -??አስተሳሰብ ስር ሰድዶ የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን በአንዳንድ ተቋማት ታታሪዎች አማካኝነት አስተሳሰቡን ሰብሮ በመውጣት ለሌሎች አርዓያ መሆን የተቻለበት ሁኔታ እየታየ ይገኛል።
ለዚህ ደግሞ የቅርብ ምሳሌዎቻችን ወደ ኢንቨስትመንት ያደጉ የቁጠባ ማኅበራት መኖራቸው፤ እንዲሁም ዘመን አመጣሹንና የሐሰት የኢንተርኔት ቁማር (ይሄንን ይጫኑና በየቀኑ 100ሺህ ዶላር ያግኙ የሚለውን ገዳይ ማስታወቂያ ልብ ይሏል) በመጠየፍ ወደ ውስጥ፣ ወደ ራሳቸው ያዩት፣ – – – የብድር ተቋሙ ቆጣቢና ተጠቃሚ አባላት ናቸው።
በተለይ ለእኛ የመንግሥት ሠራተኞች መቆጠብም ሆነ ቆጥቦ የዘመናዊ ኦቶሞቢልና ሌሎች ንብረቶች ባለቤት መሆን ልክ “ርቆ የተሰቀለ ዳቦ“ (እንዲል ትያትሩ)፤ የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ከቶም የማይደረስበት መስሎ ለሚታየን ማኅደር የቁጠባ ማኅበርና አባላቱ የሚያስተምሩን ቁም ነገር አለና ያንን አጥብቀን ልንይዘው፤ አርዓያነቱንም ልንከተልና በ“ይቻላል!!!“ መንፈስ ልንንቀሳቀስ ይገባል።
የጠቀስነው ክፍለ ከተማና ሌሎች ደመወዝተኛ ሠራተኞች ከቻሉ ሌሎቻችን የማንችልበት ምንም አይነት ምክንያት የለምና በጉዳዩ ላይ ልንወያይ፣ ልንነጋገርና ልንመካከር፤ ሀሳባችንንም ወደ መሬት ልናወርደው ይገባል። በተለይ በየተቋሞቻቸው በሠራተኞች የቁጠባ ማኅበራት አማካኝነት ከፍ ያለ ተቀማጭ ያላቸው ተቋማት ዝቅ ብለን ከምንጠቅሳቸውና መሰል የቢዝነስ ተቋማት ጋር በመቀራረብ ምን በማድረግ ሠራተኛውን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል መመካከር ይቻላልና ጉዳዩ ቢታሰብበት አዋጭ ከመሆን አያመልጥም።
በተለይም፣ ገንዘብ ባለገንዘቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መንቀሳቀስ ያለበት ከመሆኑ አንፃር እንደነዚህ አይነቶቹን አካሄዶች መመልከቱ የተሻለ መሆኑ በባለሙያዎች ይመከራልና ይህችን ሀሳብ እንደ መንጠላጠያ መጠቀሙ አይከፋም። እለቱ፣ “የሚጠበቅባቸውን የመኪና ብድር አገልግሎት ቅድመ ቁጠባ ላጠናቀቁ አባሎቻችን የመጀመሪያ ዙር የኤሌክትሪክ መኪና ርክክብ“ የሚደርግበት ቀን መሆኑ በተነገረለት መድረክ በርካታ የቢዝነስ ዓለሙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ አንዱም ባሉት 23 ድርጅቶቻችን ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎችን እንሠራለን፤ የሀገር ኢኮኖሚ መገንባቱ ላይም ዐሻራችንን ማኖር እንፈልጋለን“ ያሉት የበላይነህ ክንዴ ድርጅት ተወካይ ናቸው።
እንደ ተወካዩ ንግግር ድርጅታቸው “ማኅደር”ን ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጎን ይቆማል፤ ያበረታታል፤ ይደግፋል፤ የአቅርቦትና ርክክብ ሥራዎችንም ይሠራል። ጎሸር ትሬዲንግም እንደዚሁ። በእለቱ የተገኙ የተለያዩ ዕድሮች ሥራ ኃላፊዎችም ማኅደርን ለመቀላቀልና የብድርና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ቃል የገቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም በዚሁ መድረክ ላይ የቁጠባና ብድር ተቋሙን መቀላቀላቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።
በመግቢያችን በጠቀስነው ስፍራና ቀን በተካሄደ “የመኪና ቁልፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት“ ላይ እንደ ተመለከትነው ተፈላጊውን የቅድመ ክፍያ መጠን ያሟሉ የቁጠባ ማህበሩ አባላት ከ1ነጥብ5 እስከ 2ነጥብ5 ድረስ ዋጋ ያላቸውንና ዘመን ያፈራቸውን፣ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ ኦቶሞቢሎችን ተረክበዋል።
በእለቱ በሁሉም (ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የማኅበሩ ማኔጅመንትና አመራር አካላት፤ እንዲሁም ከአስተባባሪና አስተናባሪው አቶ ኢዮብ ሥዩም ጀምሮ በአስመጪና ላኪዎች፣ ድጋፍ አድራጊ ባንኮች፣ በየአካባቢው የሚገኙ እድሮች የሥራ ኃላፊዎች፣ ቆጣቢዎቹ የዘመናዊ ኦቶሞቢሎቹ ቁልፍ ተረካቢዎቹና ሌሎችም) እንደ ተነገረው ቁጠባን ባሕላችን ካደረግን ከዚህ በላይ መሥራት እንደምንችል ብቻ ሳይሆን፣ ከራሳችንም አልፈን የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልናፋጥን የምንችል መሆኑ ነውና ቁጠባን ባሕላችን እናድርግ!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም