በዘመናዊው ዓለም በተለይም ባደጉት ሀገራት የስፖርት ሥልጠናዎች ሳይንሳዊ መንገድን ተከትለውና በቴክኖሎጂ ታግዘው እንደሚሰጡ ይታወቃል። በአንድ የስፖርት ቡድን ውስጥም ከአትሌቶችና ከአሠልጣኞች ባሻገር የጤና፣ የሥነ ምግብ፣ ሥነልቦና፣ የውድድር ትንተና ወዘተ ሙያተኞችን ማሰባጠር የተለመደ አሠራር ነው። ከአተነፋፈስ ሥርዓት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው የአትሌቲክስ ስፖርት ደግሞ የሥልጠና እና የውድድር ሁኔታን ከአየር ንብረቱ ጋር እንዲመጣጠን በማድረግ ረገድ የሚሠሩ ባለሙያዎችም የአሠልጣኞች ቡድን አካል ናቸው። አትሌቶች ምቹ በሆነ የአየር ሁኔታ ሥልጠናቸውን ከመከታተል ባለፈ በቤተሙከራ ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን አየር እየተነፈሱ እንዲለማመዱ በማድረግም ለውጤት ያበቋቸዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ኋላ ቀር የሚባል ሲሆን፤ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ተመሳሳይ ሊባል ከሚችል ተለምዷዊ የሥልጠና ስልት ሊላቀቅ አልቻለም። በውድድሮች ላይ ውጤታማ አለመሆን ዛሬም ድረስ የአየር ሁኔታ ሰበብ እንደሆነ ዘልቋል። በዚህም ምክንያት ተፎካካሪ አትሌቶች የታወቀውን የኢትዮጵያውያን መንገድ ጠንቅቀው በማወቅ የበላይነቱን በመረከብ ላይ ይገኛሉ። ከዘመናዊው ዓለም ጋር ሊያራምዱ የሚችሉ ሳይንሳዊ አማራጮችን ይዘው የሚቀርቡትንም የሚቀበል አለመሆኑን የዛሬው ቃለምልልስ እንግዳችን ተሞክሮ ማሳያ ነው።
በተቀናጀ የእርሻና ደን ጥምር ጥናት ዘርፍ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በተመራማሪነት ያሳለፉት አቶ ደቻሳ ጅሩ፤ ከሃገር ውስጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባለፈ በጣሊያን እና አውስትራሊያ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ሙያቸው እህል ማምረትን፣ ከብት ማርባትን እና ዛፍ ማልማትን ያካተተ ሲሆን፤ የሰው ልጅ ምድቡ ከእንስሳት ወገን በመሆኑ ከአየር እና ሥነምሕዳር ምቹነት ጋር በተያያዘ በርካታ ጥናቶችን ማከናወን ችለዋል። በልጅነታቸው ሩጫን የሚወዱ ቢሆንም ገፍተው መሄድ አልቻሉም፣ ነገር ግን በሙያቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርትን ከአየር ንብረት እና ሥነምሕዳር አንጻር በምን መልክ ቢሠራበት ውጤታማ መሆን ያስችላል በሚለው ላይ ምርምር አድርገዋል። በተለያዩ ጋዜጦች ሙያዊ ምክረ ሃሳቦችን በማሳተምም ለአትሌቲክሱ ይበጃል የሚሉትን ከመጠቆም ወደኋላ ብለው አያውቁም።
አዲስ ዘመን፡- አትሌቲክስን ከተቀናጀ የእርሻና ደን ጥናት ዘርፍጥምር ጋር በምን መልኩ ማያያዝ ይቻላል?
አቶ ደቻሳ፡- በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ መረጃ ግርድፍ በመሆኑ የአየር ተስማሚነትን በግልጽ ያንጸባርቃል ለማለት አያስችልም። የአየር ሁኔታ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ እርጥበት፣ ንፋስ፣ ደረቅ፣ … እየተባለ የሚለይ ሲሆን ይህንን በውል ለይቶ አለማወቅ አትሌቲክስን ጨምሮ በየትኛውም ዘርፍ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። በርካታ ጥናቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የአየር ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለይተው ስለሚያስቀምጡ ይህንን መለየትና መከታተል አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ይሁንና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችን በማሳተፍ ትክክለኛውን መረጃ በማግኘት ጥራት ያለው ሥራ ከመተግበር አንጻር ክፍተቶች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ምክንያት የአየር ንብረቷና መልክዓምድሯ መሆኑ ይነገራል። ይህ በባለሙያ ዓይን እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደቻሳ፡- በአፍሪካ 40 ከመቶ የሚሆነው ከፍተኛ ስፍራ መገኛው ኢትዮጵያ ነው። ይህም ቀዝቃዛ የሚባል የአየር ሁኔታ ሲያላብሰው ከአተነፋፈስ ጋር በተያያዘ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በከፍታማ ስፍራዎች ላይ ኦክስጅን እየሳሳ ስለሚሄድ አተነፋፈሱ እንደልብ አይሆንም። ስለዚህም ሰውነታቸው የሚያመነጨው የሄሞግሎቢን እንዲሁም የብረት ክምችት መጠን ከፍተኛ ነው። እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለን የመሰሉ ድንቅ አትሌቶች ደግሞ በተፈጥሮ ከተለመደው በእጥፍ የጨመረም ነው። በመሆኑም በከፍታ አካባቢ ያደጉ ሰዎች የትኛውንም የአየር ሁኔታ የመቋቋም አቅምን ያዳብራሉ። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ረጅም ርቀት አትሌቶች ውጤታማ የመሆናቸው ምክንያትም በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ያደጉ በመሆናቸው የተቸራቸው በረከት ነው።
ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውጤታማ የሆነችባቸው ከተሞች ከባሕር ጠለል በላይ ያላቸውን ከፍታ ብንመለከት፤ ሲድኒ 28 ሜትር፣ አቴንስ 23 ሜትር እንዲሁም ቤጂንግ ከ40-60 ሜትር ናቸው። ይህም ዝቅተኛ ቦታ መሆኑን ሲያሳይ፤ በዝቅተኛ ስፍራ ኦክስጅን እንደልብ መሆኑ ለአትሌቶቻችን ጠቅሟቸዋል። በመሆኑም አትሌቶችን ወደ ውድድሮች ከመላክ አስቀድሞ ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዘ መረጃ መመልከትና መለየት አስፈላጊ ነው። ሌላው ጉዳይ አመጋገብ ሁኔታ ነው፤ ‹‹አጃማ ብመገብ አሁን ማን ችሎኝ፤ ቀለቤ ገብስ ነው በሶ አደከመኝ›› እንደተባለው በከፍታማ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ምግቦች በአትሌቶች ውጤታማነት ላይ የራሳቸው ዋጋ አላቸው። በመሆኑም የአካባቢውን ባሕል መሠረት በማድረግ በምርምር ተደግፈው መቅረብ አለባቸው። ስፖርቱ ላይ ያሉ ባለሙያዎችም ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች በቂ ማብራሪያ እና ትንታኔ እንዲሰጧቸውም መጠየቅን መልመድ ይገባቸዋል። ከውጤት ጋር በተያያዘም በምን ምክንያት እንደተገኘ መገምገምና መከታተል ካልተቻለ ፉክክር በበዛበት በዚህ ዘመን ስኬታማ መሆን አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ከመልክዓ ምድርና የአየር ፀባይ አኳያ በሌሎች የስፖርት አይነቶችስ ኢትዮጵያን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ምቹ ሁኔታ የለም?
አቶ ደቻሳ፡– ከከፍታ ቦታዎች ወደታች ስንወርድ እንደ ዳሎል አይነቱን እጅግ ዝቅተኛ ስፍራ እናገኛለን። ከምድር ወገብ በጣም የራቁ ሃገራት የአየርና የመልክዓ ምድር ሁኔታው እጅግ እየተለየና ከባድ እየሆነ ይሄዳል። በዚህም ምክንያት ክረምታቸው እጅግ በጣም ቀዝቃዛና በበረዶ የተሸፈነ፤ በበጋ ደግሞ የሙቀት መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። በአንጻሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ለሁሉም ምቹ የሆነና የተመጠነ የአየር እና የቦታ አቀማመጥ አላቸው። ይህም በስፖርቱ በርካታ አማራጮች እንዲኖረን የሚያስችል በመሆኑ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። በአትሌቲክስም ከውድድር መልስ ውጤት ጠፋ በሚል የሚነሳ የጅምላ ምክንያትንም ያስቀራል። በመሆኑም ለ2028ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ይህንን ሁኔታ ለይቶ በቅንጅት ወደ ዝግጅት መግባት ያስፈልጋል። የተሰጠንን በረከት ማወቅ ካልቻልን መርገምት ነው የሚሆንብን።
አዲስ ዘመን፡- በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የኢትዮጵያ ውጤት ለመቀነሱ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ምክንያት አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል?
አቶ ደቻሳ፡- አትሌቶችን የምናሠለጥንበትን ስፍራ ለየትኛው ርቀት ይሠራል የሚለውን ለይተን አለማየታችን አንዱ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ከፍተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው በሲድኒ መሆኑ ይታወቃል። በዚያ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች ውስጥ ወርቅ ያስመዘገቡት ብዙም ልምድ የሌላቸው ወጣቶች እንዲሁም ከወሊድ መልስ በተወዳደረችው ደራርቱ ቱሉ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው ለአትሌቶቹ ውጤታማነት የሲድኒ ምቹ የአየር ሁኔታ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ነው። በመሆኑም በምልመላ፣ በአካላዊ ቅርጽ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በሳይንሳዊ ሁኔታ ታግዞ በመለየት አተኩሮ መሥራት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በተገቢው አየር አለመዘጋጀት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በአትሌቲክስ ውጤት ላይ ምን ዓይነት ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ሊያደርሱ ይችላሉ?
አቶ ደቻሳ፡– ቁመት፣ ፆታ፣ ክብደት፣ አለባበስ፣… የራሱ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ በቁመታቸው አጭር የሆኑ አትሌቶች በውድድር ወቅት ረጅም አትሌቶችን ተጠግተው ቢሮጡ እንደጥላ መከለልና ከነፋስ ማምለጥ ይችላሉ። በተለይ የአየር እጥረት ያለበትና ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አካባቢዎች ላይ ይህንን መሰል ቴክኒክ በመከተል ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ከፆታ አንጻርም ሴቶች በተፈጥሮ ሞቃታማ አካባቢዎች ይመቻቸዋል፤ ወንዶች ደግሞ በተቃራኒው። ዝግጅት በሚደረግበት ወቅትም እንደ ሱሉልታ ያሉ ቀዝቃዛ ስፍራዎች ለወንድ አትሌቶች በይበልጥ ተስማሚ ናቸው። ክብደትም ለመወርወርና አየር ላይ ለመንሳፈፍ የሚያግዝ በመሆኑ እንደየርቀቱ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። በአለባበስም ወንዶች ጥብቅ ያሉ ትጥቆችን አለመጠቀም ተገቢ ነው፤ ሴቶች ደግሞ ሙቀት ለሆነበት አካባቢ ነፋስን ሊያመጣ በሚችል መልኩ የፀጉር አሠራርን ማስተካከል። ይህ ሁኔታ ብቃትን የሚፈታተን መሆኑ ታውቆ ከምቹነቱ አንጻር ዝግጅቱንና ውድድሩን መወሰን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በጋዜጣ ባሰፈሩት ጽሑፍ ላይ የቡድን ሥራን ከአዕዋፋት መማር እንደሚገባ አስቀምጠዋል። ይህን እንዴት ያብራሩታል?
አቶ ደቻሳ፡- መረዳት ያለብን ነገር በምሕንድስና የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው የንብን ያህል ዲዛይን መሥራት እንደማይችል ነው። ወፎች ደግሞ በቡድን ሥራ የታደሉ ናቸው። አስቀድመው የአየር ሁኔታውን በመገንዘብ አንድን መስመር ተከትለው ያለኮምፓስ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሲሆን፤ በሌላ ጊዜም በዚሁ ሁኔታ ወደነበሩበት ይመለሳሉ። ቡድኑን የሚመራው ወፍ አየሩን እየሰነጠቀ (እየቀደደ) ሲበር ሌሎቹም ይህንኑ የተመቻቸ መንገድ ተከትለው ይጓዛሉ። የመሪነቱ ስፍራ አድካሚ በመሆኑም ከቆይታ በኋላ በሌላኛው ተተክቶ አቅም ያበጃል። በዚህ ሁኔታም እየተቀያየሩ ሃገር ማቋረጥ ይችላሉ።
አትሌቶችም ይህንኑ አካሄድ መከተል ይገባቸዋል፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀድመው በመሮጥ ስለሚታወቁ ተፎካካሪዎቻቸው እነሱን ከለላ ማድረግን ተለማምደዋል። ይህንን አካሄድ ለመተግበርም አቅማቸውን፣ የአየሩን ሁኔታና የሩጫውን ስሜት መለየትና ስልትን መቀያየር ያስፈልጋል። ተፎካካሪዎቻችን የኢትዮጵያውያን አትሌቶችንን ቀዳሚነት ተገን አድርገው በመሮጥና ትንፋሽ በመያዝ በመጨረሻው ሰዓት ወደፊት በመምጣት እየቀደሟቸው ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ከስፖርቱ ጋር በተያያዘ የሠራቸውን መሰል ጥናቶች የሚመለከታቸው አካላት ተመልክተው ሊጠቀሙበት ጥረት አድርገው ያውቃሉ?
አቶ ደቻሳ፡– በተለያየ መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን አፈላልጌ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። ነገር ግን ከአብዛኛዎቹ ጋር መግባባት አልቻልንም። ለዚህ እንደማሳያ የሚሆን አንድ ክስተት ማስታወስ እንችላለን፤ ሞምባሳ በተካሄደው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና በተመሳሳይ አካባቢ ተወልደው ያደጉና በስኬታማነት ደረጃ ላይ የሚገኙ አትሌቶች ተሳትፈው ነበር። በወቅቱ ቡድኑ ወደ ውድድሩ ከመጓዙ አስቀድሜ ልምምድ የሚሠሩበት ጃንሜዳ ድረስ በመሄድ ሁኔታውን ለመግለጽ ሞክሬ ነበር። ቅዝቃዜ የለመዱ አትሌቶችን በከፍተኛ መጠን ሞቃት ወደሆነ አካባቢ መውሰድ ከፍተኛ ጉዳት ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል ብናገርም ሰሚ ባለማግኘቴ እነቀነኒሳ በቀለን የመሳሰሉ ምርጥ ሯጮች መቋቋም አቅቷቸው ለማቋረጥ ተገደዱ። ይህ አቅምን መግደል ማለት ነው።
በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክም በተመሳሳይ ምክረ ሃሳብ ለአትሌቶች ሰጥቼ ነበር፤ ነገር ግን ሊሰሙኝ ስላልፈለጉ ማግኘት ከነበረብን ሜዳሊያ ያነሰ ነበር ያገኘነው። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ጋዜጣዎች ላይ ከሙያዬ አንጻር እንደ አንድ ሃገር ወዳድ ባለሙያ በተከታታይ በመጻፍ ግንዛቤ ከመፍጠር ወደኃላ አላልኩም። ከዚህ ቀደም በከፈልኩት መስዋዕትነት አልቆምም አሁንም ቢሆን በሙያዬ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፣ ይህንን የማደርገውም ለገንዘብ ብዬ ሳይሆን የዜግነቴን አስተዋፅዖ ለማበርከት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ማንሳት የሚፈልጉት ሃሳብ ካለ?
አቶ ደቻሳ፡- የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ቀናነትን ተላብሰን መሥራት ብንችል ለሁሉም የሚበጅና የሚረዳ ሥራ ማከናወን እንችላለን። በስፖርቱም ሆነ በሌላውም ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስም እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- አቶ ደቻሳ ለሰጡን ጊዜና ሙያዊ አስተያየቶች ከልብ እናመሰግናለን።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም