የአነስተኛ ታዳሽ ኢነርጂ ግሪዶች ልማትን ለኤሌክትሪክ ተደራሽነት

የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም የመሠረተ ልማት የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እንዲሁም በፀሐይ ኃይል፣ በንፋስ ኃይል፣ በጂኦተርማል፣ የባዮ ኢነርጂ ማመንጫዎች ከታዳሽ የኃይል ምንጮች መካከል ይገኛሉ።

ሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል በአብዛኛው የምታገኘው ከኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ነው። በቀጣይም በዚህ አማራጭ በርካታ ግድቦችን በመገንባት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የውሃ አቅም አለ፡፡ የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ ሌሎች ታዳሽ የኃይል ማመንጫ አማራጮችም ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀም የግድ ይሆናል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት 54 በመቶ ያህል ሕዝብ ነው። ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል እና አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ በሀገራችን የአጭርና የረጅም ጊዜ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ አኳያ በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመብራት ኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም መውጣቱን ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በአገራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይ የሚሰራው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በየዓመቱ የሚደርስበትን ግብ ይዞ ሰፋፊ ሥራዎችን ይሰራል። ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰራጫ መስመር በኩል ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ከ10 በላይ ሌሎች ባንኮችም ያሉበት የሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፎች ፋይናንስ እያበደሩ መሰረተ ልማቱን የማስፋፋት ሥራ ይሠራል። የግልና መንግሥታዊ ተቋማትም በጋራ እየሰሩ ናቸው። የኃይል ማመንጫ ግሪድ ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሌሎች የታዳሽ ኃይል ምንጮች ላይ ያተኮሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ይሠራሉ።

ከፀሐይ፣ ከንፋስ፣ ከእንፋሎት እና ሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች አኳያ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። ግሪዱ ሊደርስ ከማይችልባቸው በተለይ ተራርቆ ከሰፈረው ሕዝብ አካባቢ ለመድረስ የተሻለው አማራጭ የሶላር ኃይል ነው። እነዚህ አካባቢዎች ግሪዱ ሊደርሳቸው የሚችለው እስከ 2030 ነው። በመሆኑም ኦፍግሪድ ወይም ከግሪድ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ያለውን ሕዝብ ለመድረስም ሌሎች የኃይል አማራጮች ላይ እየተሰራ ነው።

ይህ ሥራ ግን ከፍተኛ አቅምና ፋይናንስ እንደሚፈልግ ጠቅሰው፤ እንዲያም ሆኖ መንግሥት ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የልማት አጋሮችም ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተለይ አሁን በጣም አዋጭ የታዳሽ ኢነርጂ እየሆነ የመጣው ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጨት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም እየታየ ኃይል ከማመንጨት ጀምሮ፣ ኃይል እስከ ማስተላለፍና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ትላልቅ ፕሮግራሞች ተቀርጸው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ከፍተኛ የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት እንዳለ ጠቅሰው፤ ይህን ለማልማት ኢንቨስትመንት እንደሚፈልግና ወጣቱን በማሳተፍ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሶላር ቴክኖሎጂ ማዕከል የተቋቋመ ሲሆን፤ እነዚህ ለውጦች አሁን ያለውን የኢነርጂ አቅርቦት በቀጣይ በከፍተኛ ደረጃ ይለውጡታል የሚል ዕምነት እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

አማካሪው እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ አነስተኛ የሶላር ኃይል ማመንጫ ግሪዶች በስፋት እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው። መብራት በማዳረስ ከጨለማ ማውጣቱ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ህይወቱ እንዲሻሻል ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ በፀሐይ ኃይል በመታገዝ ውሃ በማውጣት ለመጠጥ ውሃ ማቅረብ፣ የመስኖ ልማት ማካሄድ፣ ወፍጮ ማንቀሳቀስ እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ የገጠር ኢንዱስትሪ ስራዎች ማስፋፋት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚከናወነው የመስኖ ልማት ሥራ በናፍጣ የሚሰሩ ጀነሬተሮችን ታዳሽ በሆኑ የሶላር ኃይል ምንጮች ለመቀየር እየተሰራ ነው። ይህም አርሶአደሩ ሁለት ሦስት ጊዜ ማምረት ያስችለዋል። በአንድ በኩል ዘመናዊ የመስኖ ልማቱን በሌላ በኩል ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያገኘ፣ ኅብረተሰቡም ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሠራ፣ የሚያስችሉ ፓኬጆችን ጨምሮ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ሚኒ ግሪድ የተወሰነ ድጎማ እንደሚፈልግ ተናግረው፤ ዓለም ባንክን ከመሳሰሉ አጋሮች ጋር የተወሰነ ፋይናንስ ለሶላር ኢነርጂ አልሚዎች የማበረታቻ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።

አቶ ጎሳዬ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ለኅብረተሰቡ ዋናው ግሪድ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች አነስተኛ ግሪዶች በብዛት እየተሰሩ ናቸው። በዚህም እስካሁን ከስምንት ሺህ በላይ ለሚሆኑ የገጠር ከተሞች አነስተኛ ግሪዶች ተሠርተዋል፤ በዚህም የአካባቢው ኅብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ ነው።

ይሁንና ማህበረሰቡ ተበታትኖ በሰፈረበት አካባቢ ሌላ አማራጭ መከተል እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ፤ የከተሞች የአሰፋፈር ፕላንን ታሳቢ ያደርጋል ብለዋል። ኅብረተሰቡ በአንድ አካባቢ እንዲሰባሰብ መደረጉ ለኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገልግሎቶችም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን በተጀመረው አካሄድ 200 ያህል ከተሞች ላይ አነስተኛ ኃይል የሚያመነጩ ግሪዶችን ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ 100 በሚሆኑ ከተሞች ግማሹ ግንባታ እየተካሄደበት ሲሆን፤ ቀሪው የጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች መቶ ያህል ከተሞች ደግሞ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አማካሪው ገለጻ፤ በሀገሪቱ እየተሠሩ ያሉ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ አነስተኛ ግሪዶች ከሌሎች ሀገራት አንፃር ሲታዩ ትልልቅ እና አዋጭ ናቸው። ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ የሶላር ጥምረት አባል በመሆኗም ጥሩ ትሠራለች በሚል በሞዴልነት ተይዛ በጋራ እየተሰራ ነው። ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተደረገ ድጋፍም ከ25 በላይ አነስተኛ ግሪዶች እየተሰሩ ናቸው። በመሆኑም ከውሃ ኃይል ማመንጫ በተጨማሪ በሶላር ኢነርጂ ሥራዎች በስፋት እየተሰራ ነው። የንፋስ ኃይል ትልቅ በመሆኑ ከዋናው ግሪድ ጋር የሚገናኝ ነው ሲሉም ጠቅሰው፤ የንፋስ ታዳሽ የኃይል ምንጭ አዋጭ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየለማ ይገኛል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከጂኦተርማል ወይም ከእንፋሎት ኃይል አቅም አኳያም ኢትዮጵያ ከኬንያ ቀጥሎ ትልቅ ሀብት በመኖሩ በስፋት የማልማት ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሰራበት ይገኛል። ከዚህም አኳያ ጉድጓዶችን የመቆፈር ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ ዓለም ባንክም ለእዚህ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ የግሉ ዘርፍም በዚህ ላይ ተሰማርቶ እንዲሠራ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

ከታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ አኳያ የመሠረተ ልማት እጥረት ቢታይም፣ ከሌሎች ሀአንጻር የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት አቅም ስለመኖሩ አንስተው፤ እንደ ሩቅ ምሥራቋ ቻይና ከመሳሰሉ ሀገራት ብዙ ልምድ መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሀብቱ መኖሩ ብቻውን በቂ አይደለም፤ መልማትና ለኅብረተሰቡ የኃይል አቅርቦቱ መድረስ አለበት። አንዱ ትልቁ ፕሮግራምም ለኅብረተሰቡ ኤሌክትሪክ ማዳረስ ነው። አሁን እንደሚታየውም ግማሹ የማህበረሰቡ ክፍል ገና የመብራት አገልግሎት አላገኘም። የግሉ ዘርፍ ወይም የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ በምን መልኩ ሊሠራ ይችላል በሚለው ላይ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አቅም የማሳደግ ሥራዎች አሉ፤ አንዱ ትልቁ ተግዳሮት ፋይናንስ በመሆኑ በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደነበረ አስታውሰው፤ ከግሉ ባለሀብት አሁን በብዛት ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የውጭ ባለሀብቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል። የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬው ከማግኘት አኳያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እምብዛም ተሳትፎ እያደረጉ እንዳልሆነ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የሶላር አሶስዬሽን ማህበር በኩል የተቸገሩት ምን እንደሆነ ከታክስ አኳያ፣ ከግብር እፎይታ፣ ማበረታቻ ከማግኘት አንፃር፣ ከጉምሩክ፤ ከፋይናንስ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ከሶላር ኢነርጂ አገልግሎት የግብር ሀንድቡክ መዘጋጀቱንም አስታውሰዋል።

ይህም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባው ላይ ምን ያህል ማበረታቻ ማግኘት አለበት፤ ከታክስ ነፃ መሆን በሚችልበት እና ለኅብረተሰቡም የተሻለ የሶላር ኢነርጂ ማቅረብ መቻል አለበት።

በየከተሞቹም በየገጠሩም ያልተያያዙ እና በየቤቱ ያሉ የሶላር አሠራሮችን በብዛት የሚሠሩት የሀገር ውስጥ የሶላር ማህበር አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እዚህ ላይም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ሥራቸውንም ወደ አነስተኛ ግሪዶች ልማት እንዲያሳድጉ እና አቅማቸው በእነዚህ ላይ እንዲዳብር ካልሆነም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር እንዲሰሩ እያበረታታን ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ በተለይ ለምድጃ የሚያገለግል አቅርቦት ወይም ኅብረተሰቡ በቤት ውስጥ የሚገለገልባቸው ማብሰያዎች በጣም ኋላ ቀር እና ከጤና አንጻር ችግር የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ ኃይል ቆጣቢ ያልሆኑትን መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ላይ የምድጃ ስርጭት በተለይ ብቁ የሆኑ ምድጃዎችን ማምረት፣ እና ታዳሽ የኢነርጂ ምንጮችን ደግሞ በእነዚህ ምድጃዎች እንዲጠቀሙ ትልቅ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል። ይህም ኅብረተሰቡን መለወጥ ወደሚያስችል ሌላ የልማት ዘርፍ እንዲያተኩር የሚያደርግ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሀገራችን ነዳጅ አምራች ባለመሆኗ ከውጭ ታስመጣለች። ነዳጅ የሚጠቀሙ የሀገር ውስጥ የኢነርጂ ፍጆታዎችን በታዳሽ ኃይል መተካት አንዱ ትልቁ የኢነርጂ ስትራቴጂ አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ትራንስፖርት ላይ የኤሌክትሪክ መኪናዎች በሶላርም በሌሎችም የግሪድ በሆኑ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች በስፋት እየተሠራ ነው። ከዚህ አንጻርም ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የኃይል ዘርፎች ጋር በመሆን የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ እና ወደ ሥራ እየተገባ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ወደፊት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በታዳሽ ኢነርጂ የትራንስፖርት ዘርፉን የማዘመን ሥራ ትሠራለች። እንዲሁም ለወደፊት የአቪዬሽን ኃይል አቅርቦት ላይም የታዳሽ ኢነርጂ ያስፈልጋል። ለዚህም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የታዳሽ ኃይል በተለይም በፀሐይ የኃይል ምንጮች አማካይነት ኅብረተሰቡ 24 ሰዓት መብራት ለማግኘት ያስችለዋል። ለግብርና ስራዎች፣ ለመስኖ ሥራ፣ ወጣቶች በስፋት ለሚሰሩበት ለጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ጨምሮ ማህበራዊ ሕይወት ለሚለውጡ ሥራዎች የላቀ አገልግሎት እንዳለው አስገንዝበዋል።

የሊዳትኮ ሶላር ኢነርጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ዋለልኝ በበኩላቸው፤ ከሶላር ኢነርጂ አንፃር በሀገር ውስጥ ያለውን ተግዳሮትና መልካም አጋጣሚ አስመልክተው ሲያብራሩ፤ አብዛኞቹ የሶላር ኢነርጂ መሳሪያዎች፤ ሶላር ፓኔሎች፣ ኢንቨርተሮች፣ ባትሪዎች የመሳሰሉት ቀረጣቸው ዜሮ መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ አኳያ መንግሥት ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ መንግሥት ከዓለም ባንክ በተገኘ ፈንድ ባለፉት 10 ዓመታት የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኝ እና ለሶላር ዘርፉ እንዲውል የማመቻቸት ሥራ መሥራቱን አስታውሰዋል። በዚህም ቀደም ሲል 40 ሚሊዮን ዶላር አሁን ደግሞ ሌላ 40 ሚሊዮን ዶላር እንዲመጣ በማድረግ እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሶላር ሥራዎች እንዲስፋፉ ማበረታቻ መድረጉን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማ ውስጥ የሶላር ኃይል በመጠቀም ኤሌክትሪክ አምርቶ መሸጥ ገና በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የተካተተ አይደለም። በአውሮፓ እና ባደጉ ሀገሮች እንደሚታየው ከፀሐይ ኃይል የሚመረቱ የኤሌክትሪክ ኃይሎች የግድ ሜጋ ፕሮጀክት መሆን አያስፈልጋቸውም። ለምሳሌ በጀርመን በእያንዳንዱ የግለሰብ ጣሪያ ላይ የሶላር ፓነል እንዲተከል እና ጥቅም ላይ እንዲውል የተረፈውን ደግሞ ወደ ግሪድ መስመር በማስገባት ሀገሩን በሶላር መሸፈን ይቻላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳዩ በሕግ ማዕቀፍ ተይዞ መመሪያ የወጣለት ባለመሆኑ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም በማለት በፍጥነት መመሪያ ሊወጣለት እንደሚገባ አቶ ደረጃ አስታውቀዋል።

አነስተኛ የሶላር ፋኖሶች/አምፑሎች/ ላይ ቀደም ሲል ዜሮ የነበረው ቀረጥ 15 በመቶ መደረጉንም ገልጸዋል። ለአርሶ አደሩ ይበልጥ የሚደርሰው በመሆኑ ቀረጡ ዜሮ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። የኤሌክትሪከ መኪናዎችንም በሶላር ኤሌክትሪክ ቻርጅ ለማድረግ ሃሳብ እንዳለ ጠቅሰው፤ የሕግ ማዕቀፍ ግን እንዳልወጣ አመልክተዋል፡፡ ይህን መሰል የሕግ ማዕቀፎች ቶሎ መዘጋጀት አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ትላልቅ ሕንፃዎች ላይ የኃይል መቆራረጥ ሲታይ በናፍጣ የሚሠራ ጀነሬተር ጥቅም ላይ እንደሚውል አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ የናፍጣ ዋጋው መወደዱን ጠቁመው፣ መንግሥትም የናፍጣ መኪናን ወደ ኤሌክትሪክ እየቀየረ ነው። ይህም ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ መሆኑን ተናግረዋል። “እኔ ለምሳሌ እንደ የግሉ ዘርፍ አንድ ህንፃ ላይ የሶላር ጀኔሬተር ብተክለ ኤሌክትሪከ በሚቆራረጥበት ጊዜ ብቻ እየሠራ በየወሩ የተጠቀሙበትን ቢከፍሉ አዋጭና አማራጭ ነው።” ሲሉም በዚህ መልኩ የሶላር አማራጮችን በሀገራችን ማስፋፋት እንደሚቻል አመላክተዋል።

በመንግሥት በኩል 40 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ በልማት ባንክ በኩል ወደ ግል ባንኮች መጥቶ ከግል ባንኮች መውሰድ የሚቻልበት አሠራር መዘጋጀቱ መንግሥት ዘርፉ ላይ እምነት እንዳለው አመላካች ነው ብለዋል። አሁን ደግሞ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት በግል ባንኮቹ ጭምር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉ ትልቅ እድል እንደሆነ አመልክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You