አረንጓዴ ተስፋ

የአየር ንብረት ጉዳይ እንደዋዛ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ ልክ እንደ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የብዙዎች አጀንዳ መሆን ነበረበት፡፡ የአየር ንብረት በቀጥታ የኢኮኖሚ ጉዳይ ማለት ነው፡፡ የተስተካከለ የአየር ንብረት ሲኖር ነው ውጤታማ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚኖረው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚው በግብርና ላይ ለተመሰረተ ሀገር የአየር ንብረት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

የአየር ንብረት መዛባት ዓለም አቀፍ ችግር ሆኖ ዓለምን ለስጋት እየዳረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም አሳሳቢ ጉዳይ የአየር ንብረት ነው፡፡ ጦርነት አሳሳቢ የሚሆነው እንደ አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ላሉ ሀገራት ነው፡፡ የሰለጠኑ ናቸው የሚባሉ ሀገራት ስጋት አድርገው የሚያዩት የአየር ንብረት መዛባትን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ሀገር ናት፡፡ ከዓመት ዓመት ፀሐይ የምታገኝ፣ ዓመቱን ሙሉ ዳሎል እና ራስ ዳሽን ያላት፣ ሁሉንም የአየር ንብረት የያዘች ብዝሃ ባህል ብቻ ሳይሆን ብዝሃ ተፈጥሮ የሆነች ሀገር ናት፡፡

ታዲያ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በሕዝብ ቁጥር እያሻቀበ መምጣት፣ የእርሻ መሬት ማነስ እና በግንዛቤ አለመኖር ምክንያቶች የደን ሽፋኗ እየተመናመነ መጥቷል፡፡ ይህ የደን ሽፋን መመናመን ለድርቅ እየዳረገን ነው፡፡ ለአየር ንብረት መዛባት እየዳረገን ነው፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራበት ነው፡፡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን ችግኞች ውሃ የማጠጣትና የመንከባከብ ሥራ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሲሰጠው አይተናል፡፡ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክረምት በመጣ ቁጥር በልዩ ትኩረት እየተሠራበት ነው፤ በዚሁ ዘመቻ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝታበታለች፤ የአየር ንብረት አያያዝ ምሳሌ ትደርጋለች፡፡ ትናንት ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ‹‹በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ›› በተሰኘው ዘመቻም፤ ከአሜሪካ፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የጀመረችው ተነሳሽነት ሌሎች ሀገራትን የሚያነሳሳ ነው ማለታቸውን አይተናል፡፡

ይህን የዓለም ምሳሌነት ለማስቀጠል ግን አሁንም ያልቀረፍናቸው ችግሮች አሉ፡፡

ዛፍ እየጠፋ በረሃማነት የተስፋፋው መሬቱ ዛፍ አላበቅል ብሎ ነው? ወይስ የዛፍ ዝርያ ከምድረ ገጽ ጠፍቶ ነው? ይሄ ሁሉ የሆነው በግዴለሽነታችን ነው፡፡

የክረምቱን መግባት ተከትሎ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ የተለመደ ቢሆንም ከ2011 ዓ.ም ወዲህ ያለው የተለየ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው ያስጀመሩት፡፡ እርሳቸው በተከሉት ችግኝ ብቻ ሀገሪቱ አረንጓዴ በአረንጓዴ ትሆናለች ተብሎ አይደለም፤ መሪ ናቸውና አርዓያ ለመሆን ነው፡፡ ሕዝብ መሪውን ተከትሎ እንዲህ አይነት በጎ ነገሮችን ያደርጋል፡፡ መሪ ማለት እንግዲህ የሚመራ፣ የሚያሳይ ማለት ነው፡፡

ይህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በየዓመቱ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ይታያል፡፡ አጀንዳነቱ ግን ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መጥቷል። ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎቹም ከችግኝነት ያለፈ ጉዳይ ያስመስሉታል፡፡ እስኪ የሁለቱንም ወገን እንታዘብ።

ተዋቃሚ ነን በሚሉት በኩል ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳየውን ፎቶ ለምስጋና ሳይሆን ለወቀሳ ሲጠቀሙበት በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ለችግኝ ተከላ ‹‹ተቃዋሚ›› የሚል ቃል መጠቀም ልክ አልነበረም፡፡ ‹‹ሀገሪቱ ስንት ችግር እያለባት እሱ ችግኝ ይተክላል›› ተብሏል፤ የሀገሪቱ ምድረ በዳ መሆን ችግር አይደለም ማለት ነው? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ መትከል በምን መመዘኛ ሊያስወቅስ እንደሚችል አይገባኝም! በዚህ ችግኝ ተከላ ውስጥ ምን አይነት ማጭበርበርና ሕዝብን ማታለል ይኖረዋል ተብሎ ነው? ችግኝ መትከል ምን አይነት ስውር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይኖረው ይሆን? ስለተውነው ተዓምር ሆነብን እንጂ ችግኝ መትከል የዕለት ከዕለት ተግባር ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየው እነዚህ ወገኖች ከመቃወም ውጪ ምክንያታዊ ሃሳብ እንደሌላቸው ነው፤ ችግኝ መትከል በራሱ የተቀደሰ ሃሳብ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ መቃወም የነበረብን ቆሻሻ የሚጥሉትን እና ችግኝ የሚያበላሹትን ነበር፡፡ የአየር ንብረትን ጉዳይ እንደ ቀላል የሚያይ ተቃዋሚ ለሀገር አስባለሁ ቢል ከልቡ አይደለም ማለት ነው!

በደጋፊዎቻቸው በኩል ያለውንም እንታዘብ፤ ይሄ እንግዲህ በብዛት የሚታየው በመንግሥት ተቋማት ላይ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ነገሩ ገብቷቸውና አምነውበት አይደለም የሚያደርጉት፤ ሲደረግ ስላዩ ብቻ ወይም አድርጉ ስለተባሉ ብቻ ነው፡፡ ከችግኝነቱ ይልቅ ታይታውን ይፈልጉታል፡፡ ይህ ከልብ ያልሆነ የሀገር ፍቅር ነው፡፡

እንዲያውም በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንደታ ዘብኩት፤ ለችግኝ ተከላ በተዘጋጁ ጉድጓዶች ዙሪያ፤ የጠወለጉ፣ ጭራሹንም የደረቁ፣ የተገነጣጠሉ… የዕፅዋት አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ዕፅዋት የደረቁትና የተገነጣጠሉት በእርግማን አይደለም፤ እንክብካቤ አጥተው ነው፡፡ እንኳን እንክብካቤ ማድረግ እንዲያውም በተቃራኒው የደረሰባቸው ጥፋት ነው፤ ለዚያውም የእንስሳት ሳይሆን የሰው ጥፋት! እነዚህ ዕፅዋት ጋ ነው ችግኝ የሚተከለው! በወቅቱ ‹‹አሁን የሚተከሉ ችግኞችም ነገ ይደርቃሉ›› እያልን ነበር፡፡

አንዳንድ ሰዎች የመንግሥት ተቋማት ይህን የሚያደርጉት በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታዝዘው ይመስላቸው ይሆናል፤ ግን አይሆንም፡፡ የራሳቸው አስመሳይነት ነው፡፡ ማስመሰል የምንልበት ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የጠቀስኩት አይነት አተካከል ነው፡፡ ለምን እንደሚተከል፣ የት እንደሚተከል፣ እንዴት እንደሚተከል ካልታወቀበት ማስመሰል ነው፡፡ አልኩ ለማለት ብቻ የሚደረግ ማለት ነው፡፡

የሚተከልበት ቦታ እና ሁኔታ ካልተጠና እኮ ችግኝ መትከል ግዴታ አይደለም አይደል? አልኩ ለማለት ብቻ ለምን ወጪ ይወጣል? ችግኙ የሚተከለው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኝ ነው። አውቀን እና አምነንበት ከሆነ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ነው ማስመስከር! አለበለዚያ አስመሳይነት ነው፡፡ ቦታ እና ገንዘብ ማባከን ነው፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት በተሰጠው የችግኝ ተከላ ላይ በወቅቱ ከተሞች ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም የሚል ትዝብት ነበረኝ፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ግን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መሄድ ችሏል፡፡ አሁን ችግር የሆነው ገጠራማ አካባቢዎች በቂ ግንዛቤ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም በከተሞች ብቻ ሳይሆን ትኩረቱ በገጠራማና ተራራማ አካባቢዎች መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆቱት እነዚያ አካባቢዎች ስለሆኑ፡፡ የመንግሥት አካላት በገጠራማ አካባቢዎች ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል፤ ሀገር የጋራ ነውና ለዚህ ደግሞ ሁሉም በትብብር ሊሠራ ይገባል!

የዛሬ አረንጓዴ አሻራ ለነገ ትውልድ ነው፤ የነገ አረንጓዴ ተስፋ ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You