ከማጀት ወደ አደባባይ የወጣው የሀበሻ ድፎ ዳቦ

ኢትዮጵያ የቱባ ባህል ባለቤት እንደመሆኗ በዓለም መድረክ የምትታወቅባቸው በርካታ ባህላዊና መንፈሳዊ ክዋኔዎች አሏት፡፡ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብም የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ እምነት፣ አመጋገብ፣ አለባበስና የአኗኗር ዘይቤ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያን ልዩ ያደርጋታል፡፡ ከሀገሪቱ ቱባ ባህሎች መካከል የሀገር ባህል አልባሳት ፣ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ ድፎ ዳቦ ያሉት የሀገሪቱ ባህላዊ ምግቦች በተለይ በበአላትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ወቅት በእጅጉ ይፈለጋሉ፤ በስፋትም ይዘጋጃሉ፡፡ በተለይ በመንፈሳዊ በዓላት፣ በልደትና በመሳሰሉት ወቅቶች አድማቂና ቋሚ ተሰላፊ ናቸው፡፡ የሀበሻ ድፎ ዳቦን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን እንዲሁም መጠጦችን አዘጋጅተው የተጠቀሙ እንዲሁም ለትውልድ ያስተላለፉ ኢትዮጵያዊ እናቶች ምስጋና ይግባቸውና ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ መለያ ከመሆን ባለፈ ምግቦቹንና መጠጦቹን የማዘጋጀቱ ሥራ ለዜጎች አማራጭ የሥራ መስክ እስከመሆን ደርሷል፡፡

የዕለቱ ዝግጅታችንም ትኩረቱን ያደረገው የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ድፎ ዳቦ አዘጋጅታ ለገበያ በማቅረብ ስኬታማ በሆነች ግለሰብ ላይ ነው። በኢትዮጵያዊ እናቶች ሙያ መገለጫ የሆነው የጥንት የጥዋቱ ከስንዴ የሚዘጋጀው ድፎ ዳቦን ከነሙሉ ክብሩ ከማጀት ወደ አደባባይ ወጥቶ የቢዝነስ አማራጭ እንዲሆን ያደረገችው ይህች ግለሰብ ወይዘሮ ጊዜወርቅ ባርክልኝ ትባላለች፡፡

ወይዘሮ ጊዜወርቅ የሀበሻ ድፎ ዳቦን ጨምራ በርካታ የባህል ምግቦች አዘገጃጀትን ከወላጅ እናቷ ተምራለች፡፡ የተማረችውን በተግባር በማዋል ብዙ አትርፋለች፤ በተለይም ድፎ ዳቦን ጠበቅ አድርጋ መያዝ በመቻሏ ዛሬ ከዕለት ጉርሷ ባለፈ ለኑሮዋ ድጋፍና ለስኬቷ ምንጭ ሆኖላታል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ቄራ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ወይዘሮ ጊዜወርቅ፤ የጊዜ የሀበሻ ድፎ ዳቦ መሥራችና ባለቤት ናት፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምርቷን ዘረያዕቆብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላም የሙያ ሥልጠናዎችን ወስዳለች፡፡ በወቅቱ ይሰጡ በነበሩት የልብስ ስፌትና ታይፕ ሙያዎች የሠለጠነች ብትሆንም፣ በሙያው ሥራ ማግኘትም ሆነ ከዛ በላይ በትምህርቷ መግፋት አልቻለችም፡፡ ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከልም ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሆና ወላጆቿን በሞት መነጠቋ መሆኑን ትገልጻለች፡፡

የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኗ ትምህርቷን ከመግፋት ይልቅ የቤተሰብ ኃላፊነት በጫንቃዋ ይወድቃል፡፡ ታናናሽ ወንድምና እህቶቿን ለማሳደግ፣ ፍላጎታቸውን የማሟላትና የማስተማር ኃላፊነት ያረፈባት ጊዜወርቅ፤ ሙሉ ጊዜዋን እና የወጣትነት አቅሟን አሟጣ በመጠቀም በሥራና ሥራ ላይ ብቻ አሳልፋለች፡፡ በቤት ውስጥ አምባሻ ጋግራ ከመሸጥ ጀምራ በተለያዩ የግል ድርጅቶችም ተቀጥራ ሠርታለች፡፡

ከመኖሪያ አካባቢዋ ብዙ ርቀት ባልነበረው በፔፕሲ ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ በጊዜያዊነት ተመላልሳ ሠርታለች፤ የመኪና ዘይቶችና ቅባቶችን ለመሸጥም በግል ድርጅት ተቀጥራ በርካታ ዓመታትን አስቆጥራለች። ተቀጥሮ ከመሥራት ወጥታ የግል ሥራ ለመሥራት ስታስብ የህጻናት ልብስ መሸጥን ምርጫዋ አድርጋለች። ለሥራ እጅግ የላቀ ፍላጎት ያላት ጊዜወርቅ፤ የህጻናት አልባሳትን ቄራ ገበያ ውስጥ በመሸጥ ጥሩ ትንቀሳቀስ እንደነበርም ትናገራለች፡፡ ይሁንና ይህንንም በተለያዩ ምክንያቶች አልቀጠለችበትም፡፡

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ጊዜወርቅ፤ ከወላጅ እናቷ የተማረችውን የሀበሻ ድፎ ዳቦ ከመጋገር ቦዝና አታውቅም፡፡ በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሀበሻ ድፎ ዳቦ ጋግራ ወዳጅ ዘመዶቿንና ጓደኞቿን ትጠይቃለች፡፡ በቤቷ ለሚመጣ ማንኛውም እንግዳ ዳቦ መጋገር አይሰለቻትም፡፡ ዳቦውን የቀመሰ ሁሉ ጥፍጥናውን ሳይመሰክርና ሙያዋን ሳያደንቅ አያልፍም፡፡ ብዙዎች ‹‹የድሮ የእናታችን ዳቦ›› በማለት ያጣጥሙታል፡፡ ዳቦውን ባለበት ደረጃ ብዙዎች ዘንድም አድርሳለች፤ የሥራ አማራጭ ይሆናል የሚል እምነት ግን አልነበራትም፡፡

‘ጊዜ የሀበሻ ድፎ ዳቦ’ ከቤት ለቤት አልፎ በመሸጫ ሱቅ ይገኛል ብላ ያላሰበችው ጊዜወርቅ፤ ሥራ ፈታ በተቀመጠችበትና ምን ልሥራ እያለች በምታስብበት ወቅት አጋጣሚው መፈጠሩን አጫውታናለች።እርሷ እንዳለችው፤ ድፎ ዳቦውን ከሚወዱላትና ከሚያደንቁላት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የሀበሻ ዳቦውን እየተመገቡ ነው፡፡ ከመካከላቸው አንዷም ድፎ ዳቦውን ወደ ቢዝነስ መቀየር እንደምትችል ትነግራታለች። እሷም አላመነታችም ሃሳቡን በደስታና በድንጋጤ ተቀበለች።እንዴት የሚለውን ጓደኛሞቹ ከመከሩ በኋላም ዋጋ አውጥተው የመጀመሪያውን ትዕዛዝ እነሱ ሊወስዱ ተስማምተው ሁሉም በየተራ ለተለያዩ ፕሮግራሞች እንድትጋግርላቸው እያዘዙ አለማመዷት፡፡

‹‹በዚህ መልኩ በቤት ውስጥ የተጀመረው የጊዜ የሀበሻ ድፎ ዳቦ እግር እያወጣ ሄደ›› የምትለው ጊዜወርቅ፤ በተለይም ባለቤቷ ዳቦውን በሥራ ቦታው አካባቢ እየወሰደ በማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ እንደነበረውና አሁንም በብዙ እያገዛት እንደሆነ ገልጻለች፡፡ አንድ ሁለት እያለ የተለመደው የድፎ ዳቦው ቢዝነስ ብዙዎች ዘንድ እየደረሰ፣ ተፈላጊነቱ እየጨመረና እየተወደደ ሲመጣ ከእሷ አቅም በላይ ሆኖ የማምረቻ ቦታና ሠራተኞችም እያስፈለገው መጣ፡፡

በመሆኑም ሥራውን አስፋፍታ ለመሥራት በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀት የግድ ብሏታል፡፡ በዙሪያዋ ካሉና ሥራ ፈላጊ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመደራጀት 120 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የማምረቻ ሼድ ከመኖሪያ ቤቷ አቅራቢያ ያገኘችው ጊዜወርቅ፤ ድፎ ዳቦውን በስፋት እያመረተች ለገበያ ማቅረብ ጀመረች፡፡ የማምረቻ ሼዱ ከመኖሪያ ቤቷ አጠገብ መሆኑ በራሱ ለሥራዋ መቀላጠፍ ድርሻ ነበረው፡፡ ሥራው እየተስፋፋና ድፎ ዳቦው በከተማ ውስጥ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲመጣም ማስፋፊያ ጠይቃ አግኝታለች፡፡ ለዚህም በወረዳው ለሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የላቀ ምስጋናና አክብሮት አላት፡፡

አንድ ብቻዋን ሆና የጀመረችው የድፎ ዳቦ መጋገር ሥራ ሌሎች ሥራ ፈላጊዎችን ጨምሮ በድምሩ 50 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏታል። በአሁኑ ወቅትም በቤት ውስጥ ተጀምሮ አደባባይ የወጣው የጊዜ ድፎ ዳቦ በተለያየ መጠን፤ ግን ደግሞ በአንድ አይነት ጥራትና ጣዕም በገበያ ላይ ይገኛል። መጠኑ ከሶስት ኪሎ ጀምሮ እስከ ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን፤ በዋናነት የስንዴ ዱቄት ትጠቀማለች። ይሁንና አልፎ አልፎ የገብስ፣ የአጃ እና የፉርኖ ዱቄት በመጠቀም ልዩ የሀበሻ ድፎ ዳቦ እየጋገረች ለገበያ ታቀርባለች፡፡

ከቤተሰቧ ጀምራ በጓደኞቿ፣ በጎረቤቶቿና በቤተዘመዶቿ የተወደደው የጊዜ ድፎ ዳቦ፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መሸጫ ሱቆች አማካኝነት ለማህበረሰቡ ይደርሳል፡፡ ለሰርግ፣ ለልደት፣ ለምርቃትና ለተለያዩ ዝግጅቶች ጊዜ ድፎ ዳቦውን ገዝተው ይጠቀማሉ፡፡ ጥሩና የሚያበረታታ ግበረመልስም ታገኛለች፡፡ ከበዓላት ውጭ በአዘቦት ቀን ገበያው መጠነኛ ቢሆንም ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ሰዎች የሚጠያየቁበት ጊዜ በመሆኑ ሰፊ ገበያ እንዳለው አጫውታናለች፡፡

ድፎ ዳቦ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምግብ ነው የምትለው ጊዜወርቅ፤ እናቶቻችን የሚጠቀሟቸው ቅመሞች ለዳቦው የተለየ ጣእም እንደሚሰጡ ነው ያጫወተችን፡፡ እሷም ከወላጅ እናቷ የወረሰችውን ሙያ ተጠቅማ የድፎ ዳቦውን በዋናነት ስንዴ ተጠቅማ ታዘጋጃለች፡፡ ለልዩ ጣዕሙም የኢትዮጵያዊ እናቶች ሙያ የሆነውን ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድና አብሽ ትጠቀማለች፡፡

በኤሌክትሪክ ከሚጋገረው ድፎ ዳቦ ይልቅ በእንጨት የሚጋገረው የበለጠ ጣዕም አለው የምትለው ጊዜወርቅ፤ ጊዜ ድፎ ዳቦው የሚጋገረውም በኮባ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ሊጡን በተለመደው መንገድ ለማቡካት ከባድ በመሆኑ በማሽን ተቦክቶ ባህላዊ በሆነ መጋገሪያ በእንጨት እንደሚጋገር አመልክታለች፡፡

በልጅነት ዕድሜዋ የቤተሰብ ኃላፊነት የወደቀባት ጊዜወርቅ፤ አምባሻ ጋግራ ከመሸጥ አንስታ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡ ለታናናሽ እህትና ወንድሞቿ አርዓያ በመሆን ከዝቅታው ዝቅ ብላ፣ ከጭሱ ታግላ የሥራ ክቡርነትን አሳይታለች፡፡ በጥረቷም ጊዜ ባህላዊ ድፎ ዳቦ አደባባይ እንዲወጣና የሁሉም እንዲሆን አድርጋለች፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በቤት ውስጥ ሙያ ያደገችው ጊዜወርቅ፤ ዳቦው ለገበያ በመቅረቡ ብዙዎችን አሳርፏል ትላለች፡፡ በተለይም መጋገሪያ ቦታ እንደልብ በማይገኝበትና ሁሉም ሰው ጠዋት ወጥቶ ማታ በሚገባበት በዚህ የሩጫ ጊዜ የድፎ ዳቦው ተዘጋጅቶ ለገበያ መቅረብ መቻል ለብዙዎች እረፍት መሆኑን ትገልፃለች፡፡

ከማጀት ወጥቶ የሥራ አማራጭ የሆነው ጊዜ ድፎ ዳቦ ሁሉም ሰው በአቅሙ መግዛት እንዲችል ተዘጋጅቷል ስትል ጊዜወርቅ ተናግራለች፡፡ እሷ እንዳለችው፤ ትንሹ ሶስት ኪሎ ግራም በአራት መቶ ብር ፣ ትልቁ ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝነው ድፎ ዳቦ ደግሞ በሰባት መቶ ብር ይሸጣል፡፡

‹‹ሥራው እጅግ አድካሚ ቢሆንም ፣ አንድ ጊዜ መስመር ከያዘ ብዙ የሚያስቸግር አይደለም›› ስትል ገልጻ፣ ድፎ ዳቦውን በኤሌክትሪክ ስትጋግር በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ብዙ ድካምና እንግልት እንዲሁም ኪሳራ እንደደረሰባትም ገልጻለች፡፡ ያም ቢሆን ግን ችግሩን ሁሉ በጥንካሬ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት በቤት ውስጥ የተጀመረው የድፎ ዳቦ መጋገር ሥራ ‹‹እግር አውጥቶ አዲስ አበባን እያዳረሰ ነው›› የምትለው ጊዜወርቅ፤ በሶስት ሺ ብር መነሻ ካፒታል በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ ያስፋፋችው ሥራ አሁን ላይ 15 ሚሊዮን ካፒታል መድረሱን አስታውቃለች፡፡

በአካባቢው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ከሚሰሩ ሥራ ፈጣሪዎች መካከልም ውጤታማ መሆኗ ተመስክሮ ዕውቅናን አግኝታለች፡፡ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ውጤታማ ሥራ የሰሩ አምራቾችን ባወዳደረበት ወቅትም ‹‹ጊዜ የሀበሻ ድፎ ዳቦ›› የሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ ወይዘሮ ጊዜወርቅም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ እጅም ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ተሸላሚ ስትሆን፣ ከወረዳውም እንዲሁ በተለያየ ጊዜ የምስክር ወረቀት አግኝታለች፡፡

በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ያገኘችው ዕውቅና የሞራል ስንቅ እንደሆናትና በብዙ እንዳበረታታት የገለጸችው ወይዘሮ ጊዜወርቅ፤ ገበያ ውስጥ በስፋት የገባውና አሁንም ሰፊ ፍላጎት ያለውን ድፎ ዳቦ አዘጋጅቶ ለገበያ የማቅረቡን ሥራ አስፋፍቶ ለማስቀጠል ማቀዷን አጫውታናለች፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ወደ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ መሸጋገር መቻሉን ጠቅሳ፣ በዚህም መንግሥት የተሻለ የማምረቻ ቦታ ሊሰጣት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቃለች፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ፋብሪካ በመገንባት የድፎ ዳቦውን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በስፋት የማምረት ዕድቅ አላት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቆጮ፣ እንጀራና ኩኪሶችንና ሌሎች ባህላዊ ምግቦችንም በማዘጋጀት በመላው አዲስ አበባና በክልል ከተሞች ጭምር ተደራሽ ለማድረግ ተሰናድታለች፡፡

ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሥራና ሥራ ብቻ የኖረችው ጊዜወርቅ፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም በመኖሪያ አካባቢዋ በጎ ተግባራትን ትከውናለች፡፡ ለአብነትም 15 የሚደርሱ አቅመ ደካማ የአካባቢው ነዋሪዎችን በቋሚነት ትረዳለች፤ በበዓላት ወቅት ቅድሚያ በመስጠት ጓዳቸውን ሞልታ ተስፋቸውን ታለመልማለች፤ የ12 ህጻናትን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች። መንግሥታዊ በሆኑ ጥሪዎችም እንዲሁ በወረዳዋ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ትታወቃለች፡፡

‹‹ብዙ ሰዎች ሥራን ሲያስቡ ከትልቅ ነገር ለመጀመር ያስባሉ፤ እጃቸው ላይ ስላለው ትንሽ የሚመስል ነገር ትልቅነት ግን ዋጋ ሲሰጡ አይታዩም›› የምትለው ጊዜወርቅ፤ ‹‹የእኔ ተሞክሮ ሌሎችን ያስተምራል በሚል ሁሉም ሰው እጁ ላይ ላለው ትንሽ የሚመስል ነገር ዋጋ ይስጥ፤ ትንሽ የሚባል ሥራ የለም፤ ትንሽ የሚባል ሥራ ሁሉ የእኛን ጥረት ካገኘ ትልቅ ነው›› ትላለች፡፡ ሁሉም ሰው በእጁ ያለውን ማንኛውም ነገር ቢያከብር፣ ዙሪያውን ቢመለከትና ጥረቱን ቢያጠናክር ሥራ ፈጣሪ መሆን ይችላል በማለት ሃሳቧን ቋጭታለች፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You