«ተረጂና ተመጽዋች መሆን ከክብር ማሳነስ ባለፈ ደህንነታችንን ስጋት ላይ የሚጥል ነው» – መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ከሊቃውንት ጉባኤ እና ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር

የተወለዱት ደሴ ከተማ ነው፤ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩትም እዚያ ደሴ ውስጥ ነው፡፡ ደሴ ብዙም ሳይቆዩ ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ፡፡ በአዲስ አበባም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቅቃሉ – መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፡፡ የዛሬ የዘመን እንግዳ ያደረግናቸው መምህር ዳንኤል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ የሊቃውንት ጉባዔ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡

እንግዳችን መምህር ዳንኤል፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቤተክርስቲያኒቱን ቱፊታዊ ትምህርት በተለያዩ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ መለኮት የተቀበሉ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የድህረ ምረቃ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

እንግዳችን፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተለያዩ ቦታ ተጉዘዋል፡፡ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ የሥነ መለኮት እና የሥነ ጥበብ እንዲሁም የታሪክ አስተማሪ ናቸው፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደግሞ በተለያዩ መምሪያዎች በኃላፊነት ሠርተዋል፤ በቅርስ መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቴሌቪዥንን በማቋቋም እና የመጀመሪያውም ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በመሆንም ሠርተዋል፡፡

በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥ ደግሞ በሰላም ግንባታ እና መሰል ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በሥነ ጥበብ እና በታሪክ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብረው ይሠራሉ፡፡ በጋዜጣና በመጽሔት ጽሑፎች እና በምርምር ጽሁፎች ዐሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው እንግዳችን በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አስተምህሮቱ ላይ ሰፋ ያለ እውቀት ስላላቸው እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የምትኮራበትና የምታፍርበት የራሷ ታሪክ እንዳላት ይነገራል፤ የምትኮራበትና የምታፍርበት ታሪኳ ነው የሚሉት በእርስዎ አተያይ የትኞቹ ናቸው?

መምህር ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ልትኮራባቸው የሚያስችሏት ብዙ ታሪኮች አሏት፡፡ በእነዚህ ታሪኮች እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንናገራቸው በላይ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ አካላት ብዙ ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት እንደሆነ የማይታበል ሐቅ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ከምንኮራበት አንዱ የሥልጣኔ ታሪክ ያለን መሆናችን ጭምር ነው፡፡ ሥልጣኔ ስንልም በመንግሥት ሥርዓትም፣ በማኅበራዊ መዋቅር፣ በእድገት፣ ራስን በመቻል፣ በሥነ ጥበጥ፣ ኪነ ጥበብ፣ በሕግ የበላይት፣ በሉዓላዊ ማኅበራዊ ሕልውና፣ ተጨባጭ የሆነ የኢኮኖሚ ልዕልና፣ የራስ መገለጫ የሆኑ ክስተቶችን መኖር ሲሆን፣ የሥልጣኔ መለኪያዎች በሚባሉ ቁልፍ መስፈርቶች ቢለካ የማያሳፍሩ፣ በማንኛውም መሥፈርት ገናና የሆኑ የማያልፉ ምልክቶችን፣ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ቅርሶችን ያየዘች፣ በማኅበራዊና ኃይማኖታዊ እንዲሁም እውቀትን መሠረት ባደረጉ ጉዳዮች በጣም ሰፊ ሀብትና ቅርስ ያለን ሀገር ነን፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ አንድ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ነጻነታችንንና ሉዓላዊ ክብራችንን አስጠብቀን የቆየን ሕዝብ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ከሚለው ስማችንን ጎን ለጎን ጀምሮ ጠንካራ የሆነ የነጻነት ታሪክ ያለን ነን፡ የማንም ተገዥ አለመሆን ታሪክ ያለን ነን። እንዲያውም አንዱ ጥንታዊ ስማችን “አግአዝያን” የሚል ነው፡፡ ይህም ስያሜ ትርጉሙ የሚያመልክተው ነጻ፣ የነጻነት ሕዝቦች እንደማለት ነው። እኛ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ሥነ መንግሥት፣ የተሣሠረ ማኅበራዊ መዋቅር፣ ሥነ ምግባር፣ የእምነትና የፍልስፍና መዛግብት፣ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር፣ ከምግብ ጀምሮ በማኅራዊ ፍላጎታችን ራስን የመቻል የሕይወት ጥበብና ልምድ ያለን ሕዝብ እንደመሆናችን ልዩ የሚያደርገን አኩሪ ማንነታችንና መታወቂያችን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ የሆነ የአርበኝነት ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን፡፡ ይህ ደግሞ የሚገለጸው ጠላትን በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉ አቀፍ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል በሌላ አለመገዛት ብቻ አይደለም፤ የሌለሎች ጥገኛ ባለመሆንም ጭምር እንጂ። በኢኮኖሚ፣ በማኅበራም ሆነ በኃይማኖቱ ረገድ ጥገኛ አለመሆናችን የአርበኝነት ታሪካችን ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ሌላው ትልቁና ጠንካራው ለዚህ ሁሉ መሠረት የሆነው ከሰው ጋር የመኖርና ችግርን የመፍታት በየት አቅሙ ያለን ነን፤ በየትኛውም መስክ ራሳችንን ዝቅ አድርገን የኖርን ሀገር አይደለንም፡፡ የትኛውም ሀገር ላይ አሉ የሚባሉ ታሪኮች ውስጥ የእኛ ታሪኮች አብረው አሉ። በዓለም አቀፍ ሥልጣኔ ውስጥ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ታሪክ እኩል አብሮ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሥልጣኔ በራሱ መለኪያ ያለውና ሥልጣኔ የሚያስብሉ ነገሮች ያሉበት ሁኔታ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- አንገት የሚያስደፋ ታሪክ የሚሉትስ የትኛውን ነው?

መምህር ዳንኤል፡- አንድ ሀገርንም ሆነ የዚያ ሀገር ዜጎችን ከፍ የሚያደርጉ ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ ዝቅ የሚያስደርግ ነገር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ከማኅበረሰብ የእርስበእርስ ግጭቶች፣ የረሃብና የድርቅ ታሪኮች፣ ልመናና ጠባቂነት፣ የራስን ችግር የመፍታት ብቃት ማነስ በሰው ፊት አንገት ዝቅ አስደርገው የሚያቆሙ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ አይነቱ ታሪክ የትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ አይኖርም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሲደጋገሙና የዚያ ማኅበረሰብ መገለጫ ሲሆኑ የሚከፋ ይሆናል፡፡ ልክ በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት “famine” ረሃብ ለሚለው የእንግዝኛ ቃል “ኢትዮጵያ”ን ምሳሌ አድርጎ የነበረበት ሁኔታ ቀልድ አልነበረም፤ አድርገውት ነበርና ነው፡፡ በእርግጥ ያንን ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ገናና እና ትልቅ ሀገር ሳትሆን ቀርታ አይደለም፡፡ ከብዙ በጎ ነገሮች ጥቂት መጥፎ ነገሮች ሲነሱ ግን ይጎዳሉ፡፡ በሚያምሩ ታሪኮች ውስጥ ትንሽ ጥፋቶች ገንነው ይታያሉ፡፡ እንዲህ አይነት ታሪክ ላይ ደግሞ ደጋግሞ ሥራ በመሥራት ያንን ታሪክ ለመቀየር መጣር የግድ ነው። ምክንያቱም ችግሩ ደግሞ እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው፡፡

ለምሳሌ በየአስር ዓመቱ ወይም ከዚያ ባነሠ ጊዜ ድርቅ ደጋግሞ ሲመጣ፣ ረሃብም በየተወሰነ ጊዜ ሲከሰት የእርስ በእርስ ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲታዩ ችግሩ ምንድን ነው? በሚል ሰዎች ይወያዩባቸዋል፡፡ ረሃብ ጽድቅ አይደለም፣ ልመና ጌጥ አይደለም፣ ድህነት ጥበብ አይደለም፣ እነዚህ ያሳፍራሉ፣ ያሳንሳሉ፡፡ ከዚያ ችግሮችን ይፈታሉ፡፡ ችግሮችን ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶችን ከስር መሠረታቸው ማኅበረሰብን ሳይጎዱ በጥንቃቄ ነቅለው ይጥላሉ፡፡ የችግሮቹ ምክንያቶች ከጠፉ ችግሮቹ አይመጡም፡፡

እኛ በዚህ መልኩ መስራት ሲገባን ይልቁኑ በተቃራኒው ችግሮቹን የምናፋፋ ስንሆን እሱ ያሳንሰናል። ሌላ አካል ደግሞ ችግሩን ሲፈታልን በፈንታው ለሌላ ነገር ይዘጋጃል፤ ሌላ ሰው ችግሩን በሚፈታልን ጊዜ ደግሞ በዚያ አካል ሀገራችን ዝቅ ተደርጋ ትታያለች፡፡ ችግራችንን መፍታት ካልቻልን የሰው ተረጂ እንሆናለን። የእርስ በእርስ ግጭቶቻችንን መፍታት ካልቻልን ሌላ በመሃል ገብቶ ያሻውን እንዲያደርግ እድል እንሰጠዋለን።

አዲስ ዘመን፡- አሁንም እየተፈታተነን ያለው ርዳታ ጠባቂነታችን ነው፤ ከዚህ የተነሳ ተመጽዋች ለመሆን ተገድደናል፤ በእስርዎ አተያይ ይህንን ማስቀረት የሚቻለው እንዴት ነው? ከማን ምንስ ይጠበቃል?

መምህር ዳንኤል፡- በመጀመሪያ ችግራችንን መፍታት የምንችለው ችግር መኖሩን ማወቅ ስንችል ነው። ርዳታ ጠባቂነትና ተመጽዋችነት ማኅበረሰባችንን ዝቅ አድርጎብናል የሚለውን መረዳት ስንችል ነው፡፡ በጣም ብዙ አኩሪ ታሪኮች እያሉን፣ በጣም አስደናቂ የሆኑ መገለጫዎች እያሉን ማንነታችንን እንዳያቆሽሹብን ለእኛ የተሰጠውን ክብር እንዳያሳንሱብን መሥራት የግድ ይለናል፡፡ ርዳታ መጠበቅም ሆነ ተመጽዋችነት ያጠፋናል፤ ሰዎችን ከቦታቸው ያፈናቅላል፤ ያሰድዳል። ይህ ደግሞ ማኅበረሰብን ያጠፋል። የማኅበረሰብ እሴቶችንም ይበርዛል፡፡ ስለዚህ ለራሳችንም ለክብራችንም ስንል በመጀመሪያ እኛ መኖር ከዚያ ክብራችንንም መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

በእርግጥ ለአጣዳፊ ነገር ሰው ልንለምን እንችላለን። የሚያስገርመው ነገር የራሳችንን ታሪክ ሁሉ የጻፉት ርዳታ እንሰጣችኋለን የሚሉ አካላት ናቸው። የሀገራችንን የረሃብ ታሪክ በጽሑፍ ላይ ያለውን ጠቅሰው በርካቶች ጽፈዋል። የኢትዮጵያን የድርቅ፣ የረሃብና የጦርነት ታሪኮችን የጻፉ በርካታ ሰዎች አሉ። ያንን የሚያደርጉት ደግሞ ታሪካቸው ነው እንዲባል ከመፈለግ የተነሳ ነው። ባሉትና በሚታወቁት እኛ እንኳን ከምናስታውሳቸው ከ1950ዎቹ እስከ 90ዎቹ ድረስ ያለው ሁኔታ በትውልዱ ውስጥ ያለፉ የረሃብና የተመጽዋችነት ታሪኮች ናቸው፡፡

እናም ቁጭ ብለን “ይህ ነገር ደጋገመን እኮ! እየረታንና እያሸነፈን ነው” ብሎ መወያየት ያስፈልጋል። አርበኝነት በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፣ ችግርንም በመፍታት ጭምር ነው፡፡ ለማኝነት እና አርበኝነት አብረው አይሄዱም፣ ጠላት ያልነውን የማሸነፍ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ድህነትን ማሸነፍ ለምን ተሳነን? ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ተመጽዋች ለምን ሆንን? እኛ በእውነት ምርት መስጠት የሚችል መሬት ሳይኖረን ቀርቶ ነው ይህ የተፈጠረብን ስንል መቆጨት ይጠበቅብናል። አምራች ማኅብረሰብ ሳይኖረን ቀርቶም አለመሆኑን ማጤን ይገባናል፡፡ ውሃ፣ ምቹ የአየር ንብረት ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም ይህ ሊፈጠር የቻለው፡፡ ሌሎች ሀገራት ይህ ምቹ ነገር በሌለበት ሁኔታ ሌላው ቀርቶ በረዶ አቅልጠውና በረሃውን ውሃ አጠጥተው ሕዝባቸውን እየመገቡ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያን ከደጋ እስከ ቆላ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ያላት፣ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ገምቦ የምትባል ጠንካራና አምራች የሆነ ማኅበረሰብ አላት የምትባል ሀገር ለምን መሥራት አቃተን? በሚል ሃሳብ ዙሪያ ተቀምጦ ማሰብንና መወያየትን ይጠይቃል፡፡

ስለዚህ ችግራችንን መጋፈጥ የግድ ይለናል፤ ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው አይደለም፡፡ አጭሩን የልመናን መንገድ መምረጥ ሊያበቃ ይገባል፡፡ ይህ አቋራጭ የሆነው መንገድ የሚያጠፋብን ብዙ ነገራችንን ነው፡፡ የሚያጠፋው ርዳታ ሊሰጡን በሚመጡበት ወቅት ርዳታ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች እኛን የሚጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የእኛን ማኅበራዊ ትስስር የሚጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የእኛን ጠንካራ የእምነትና የማኅበራዊ መዋቅሮች የሚጎዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሰው የቱንም ያህል ርህሩህ ቢሆን በነጻ ምንም ነገር ሊሰጥ አይችልም። የሆነ ነገር ከሚያደርግለት ሰው በተራው የሆነ ነገር መፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለጋሾቹ ገመናዎቻችንን ሊያወጡ ይሞክራሉ፡፡ እንዲገቡብን በማንፈልጋቸው ጉዳዮቻችን ውስጥ ከችግራችን የተነሳ እንዲገቡ እድል እንሰጣቸዋለን፡፡ ተረጂና ተመጽዋች መሆን ከክብር ማሳነስ ባለፈ ደህንነታችንን ስጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ችግሩ አንድ ነገር ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ሌሎችም ነገሮች ተያይዘው የሚመጡ ይሆናሉ፡፡

በእርግጥ የረሃብ ታሪክ እኛ ሀገር ላይ ብቻ ያጠነጠነ አይደለም፤ በአውሮፓ ታሪክም ከጽኑ ረሃብ የተነሳ ሰው ሰውን የበላበት ታሪክም የሚታወስ ነው። ነገር ግን እነርሱ ተቀምጠው ውስጣዊና ውጪያዊ ችግራችን ምንድን ነው? በሚል ተወያይተው ችግሮቻቸውን መፍታት ችለዋል፡፡ ዛሬ ሰጪዎች ይሁኑ እንጂ ያለፈ ታሪካቸው የሚያስረዳው በተለያየ ችግር ውስጥ ማለፋቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ የሚፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ችግሩን ለመፍታት የተከተልነው መንገድ የተኛውን ነው የሚለው መጤን አለበት፡፡ ተቸግረንም ይሁን ዘላቂ መፍትሔ የምናገኝበትን መፍትሔ ነው እየፈለግን ያለነው ወይስ ሌላ ችግር መጠበቅን ነው መፍትሔ ያደረግነው የሚለው ሊታሰብበት የተገባ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ልመናን ሊጠየፍ የሚችል ትውልድን ማፍራት የሚቻለው እንዴት ነው? በእርስዎ አተያይ የትውልዱስ የሥራ ባህል ጤነኛ ነው ብለው ያስባሉ? ካልሆነስ መለወጥ የሚቻለው እንዴት ነው?

መምህር ዳንኤል፡– በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልመናን የሚያበረታታ ነገር በየኃማኖታችንም ሆነ በባህላችን ውስጥ የለም፡፡ ሰዎች በየትኛውም መንገድ ሠርቶ ማግኘት በተረትና ምሳሌዎቻችን ሳይቀር የሚበረታታ ነው፡፡ የቃል ተረቶቻችንን ስናስተውል በአብዛኛው የሚያተኮሩት ሰርቶ መብላት ያለው ጥቅም ላይ ነው፡፡ ሰርቶ የማይበላን ሰው በብዙ መንገድ ሸንቆጥ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ የሰው ሸከምም እንዳይሆን በተለያየ መንገድ ይነገረዋል፡፡ እናቶቻችንን እና አባቶቻችን ሰው ሲመርቁ “ሰርተህ/ሽ ለመብላት፣ ወልደህ/ሽ ለመሳም፣ ያብቃህ/ሽ” ይላሉ፤ ለራሳቸው ሲጸልዩ “የሰው እጅ አታሳየኝ” ይላሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያን ደረጃም ሊታገዝ የተገባው ይታገዛል እንጂ እንዲለምኑ አይበረታታም፡፡ እንደ እድር፣ ወንፈል፣ ማኅበር አይነት የጋራ የአኗኗር ባህላችን ሰዎች ለራሳቸው ሥራ ሠርተው በዓላት በሚሆኑበትና በሚያርፉበት ጊዜ የሌሎችን መሥራት ማኅበራዊ ግዴታ እንደሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውና ጉዳተኛ የሆኑ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ በእኛ ሀገር ወስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች በተለያየ ምክንያት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሕጻናት ያላሳዳጊ ሊቀሩ ይችላሉ። አረጋውያንም ያለጧሪ ሊቀሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ወንድ ልጆቻቸውን በጦርነትና ሀገር በመጠበቅ ውስጥ በሚፈጠር ጉዳት ሊያጡ ይችላሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እነዚያን አረጋውያንን የመጠበቅ የማኅበረሰብ ግዴታ ነው፡፡ የምናስተምረው ይህን አይነቱን ነው እንጂ ሰዎች ወጥተው እንዲለምኑ አይደረግም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሥራን በተመለከተ ምን የሚሉን ነገር አለ? ?

መምህር ዳንኤል፡- በእኛ በኩል ሥራን የማያበረታታ ወይም ሥራን የሚነቅፍ ኃይማኖታዊ በዓል የለንም፡፡ ለሥራ በጣም ትልቅ ከብር አለን፡፡ በእኛ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የጀመረው ከእግዚአብሔር ሥራ ነው ብለን የምናምን ነን፡፡ የመጸሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መስመር በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ/ሰራ ነው የሚለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚጀምረው በሥራ ነው፡፡ ከዚያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚተርከው የእግዚአብሔርን ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ ሚስጥረ ሥላሴ እና ሌሎች የኃይማኖት ትምህርቶች ፍልስፍናውን በማስተማር አይደለም የሚጀምረው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በመግለጽ ነውና በቤተ ክርስቲያን ትልቁ ጥቅስ የማይታወቀው አምላክ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይታወቃል፤ በሥራው ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ያዘዘው ፍጥረት እንዲመራ ነው፤ ይህ ሥራ ነው፡፡ አዳምን በገነት ሲያኖረው ገነትን ይጠብቃትና ይንከባከባት ዘንድም ነው፡፡ የእኛን አንዱን አባባል ወስደን ብናይ “ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀድዶ ይሰፋል” የሚል ነው፡፡ ይህ አባባል የሚያሳየው ሥራ መፍታት እንደማይፈቀድ ነው፡፡

ሥራን በተመለከተ በሶስት የኃይማኖት አምዶች ውስጥ እናስተምራለን፡፡ አንደኛ እንደ ኃይማኖት ሥራ የሌለው ኃይማኖት ራሱ የሞተ ነው እንላለን፡፡ ከዚህም የተነሳ ሥራ በኃይማኖቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሥነምግባር ነው፡፡ በሥነ ምግባር ትምህርት ውስጥ የሰው ልጅ የሥራ ሥነ ምግባር አለ። ይህ ውስብስብ የሆነ ፍልስፍና ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ውስጥ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚል አካሄድ አይፈቀድም። ሰውን የምናውቀው ከፍሬው ነው፡፡ እናም ሰው ሰርቆ እና ገድሎ ሀብታም መሆን በጭራሽ የሚወገዝ ጉዳይ ነው፡ ሰው ፍሬ ሲያፈራ ሒደቱም ውጤቱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት ባዮች ነን፡፡

በኦርቶዶክስ ዘንድ ከሥራ ጋር ተያይዞ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱም የሚለካ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ጠንካራ የሆነ የሥነ ምግባር ትምህርት እንዳለ ነው፡፡ ሶስተኛውና ከባዱ የቀኖና ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእርሱ አስራትን፣ በኩራትን እንድናቀርብ ይፈልጋል፡፡ እንዲህም ሲባል ከሠራነው ሁሉ አስር እጁን ለአስራት እንድናስብም ያዝዘናል፡፡ ይህም የሚሆነው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይውል ዘንድም ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን አስራት እንድንሰጥ የሚፈልገው ከሠራነው እንጂ ከሰረቅነው አይደለም። እንድንሰጥ የሚፈለገው ከላባችን ነው፡፡ ከሰረቅነው የምንሰጥ ከሆነ ንብረትነቱ የመጣው በላባችን ሳይሆን የሰረቅነው ሰው ንብረት ነውና የሚባረከው የቱ ነው? ይህ በጣም አጨቃጫቂና ከባድ የሆነው የቀኖና ትምህርት ነው፡፡ ዋናው በኃጢአት የሚቀርበውን መስዋዕት እግዚአብሔር አለመቀበሉ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ጉዳይ ስንፍና ኃጢአት መሆኑን እናስተምራለን፡፡ ሰው ማምረትና መሥራት መጣር መጋር እየቻለ፤ ማስተማር እየቻለ የማያስተምር ከሆነ የጋን መብራት ይባላል፡፡ ጉልበት እያለው በጉልበቱ አምርቶ መጠቀምና መጥቀም እየቻለ ካላከናወነ ልግመኛ ይባላል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጠውን ሀብት እንደማጉደል ነው የሚቆጠረው፡፡ ችሎታ እያለው መክሊት እያለው መክሊቱን ባለመሥራቱ ምክንያት የሚቀብር ሰውን ጌታችን ታማኝ ያልሆነ፣ ከንቱና ክፉ የሆነ አገልጋይ ይለዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ለሥራ ያላት ትምህርት ጠንካራ ነው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍም እንደሚለው ሊሠራ የማይወድ ቢኖር አይብላ ነው፡፡ በእኛ ቤተክርስቲያን የሚነበብ ድርሳነ ሚካኤል አለ፤ እዚህ ድርሳን ውስጥ አንድ ሰው ቅዱስ ሚካኤልን እንዲባርከው ይለምነዋል፤ ቅዱስ ሚካኤልም ሲመልስለት “አንተ በመጀመሪያ ሳትሠራ ምኑን ልባርክልህ? ያልሠራኸውን እንዴት አድርጌ እባርክልሃለሁ?” ሲል ይመልሳል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሰውን እግዚአብሔር የሚባርከው በሠራው ሥራ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚባርከው የነገደውንና የሠራውን ሰው ነው፡፡

ቤተክርስቲያን አለመሥራትንና ደካማነትን አጥብቃ ትኮንናለች፡፡ ሥራን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ሳይሠሩ መብላትን የሚወድን “ሐኬተኛ” ትላለች፡፡ መለመንና መጠበቅ የሚፈቀደው መሥራት ለማይችሉ ሰዎች ነው። ለምሳሌ በተለያየ ምክንያት አልጋ ላይ ያለን ሕመምተኛ ወይም ደግሞ አረጋዊ ይሙት አይባልም፡፡ ሊታገዝ የግድ ነው፡፡ አሳዳጊዎቻቸውን ያጡ ሕጻናትን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡

ቤተክርስቲያን ቸርነትን፣ ለጋስነትን ታስተምራለች፤ እነዚህ በየራሳቸው ትልቅ ትምህርት ናቸው፡፡ ነገር ግን ቸርና ለጋስ መሆን የሚቻለው ሠርቶ ነው፡፡ ቸርነቱ የሚመጣው ከሠራው ላይ ነው፡፡ መጽዋችነቱም የሚመጣው ከነገደው፣ ካመረተው ነው፡፡ ስለዚህ መሥራት ግድ እንደሆነ እንደምናስተምረው ሁሉ ጎን ለጎን ደግሞ ለጋስነትንም ቸርነትንም ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእድገቷ ፊተኛው መስመር ላይ እንድትገኝ ለማድረግ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ ደረጃ መውጣት የምትችለው እንዴት ነው?

መምህር ዳንኤል፡– ትውልድ ግንባታ ላይ መሥራት አለብን፡፡ ስንገነባ ደግሞ በመጀመሪያ የት ላይ እንደተቸገርን ለይተን ልናውቅ ይገባል፡፡ ችግር ያለባቸው መመሪያዎቻችን ናቸው ወይስ ምንድን ነው? የሚለውን መገንዘቡ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ፖሊሲዎቻችን ናቸው ችግር ያለባቸው ወይስ የትውልድ አቅም ላይ ነው? የሚለው መለየት ይኖርበታል፡፡ ትውልዱ መሥራት የሚችልበትን ክህሎት ነው ያጣው? በሚል ችግሩን መለየት መቻል አለብን፡፡

ከዚያ ቀጥሎ ትልቁና ዋናው የተሳሰረ፣ የተናበበ እና እርሱ በእርሱ የተግባባ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ምክንያቱም ይህን ሆነም ቀረ ቤተክርስቲያን እንደተቋም መንግሥትም አንድ ሀገር እንደሚያስተዳደር አካል እና እንደ ትውልድ ተጠያቂነት እንዲሁም ሌሎችም ተቋማት እዚህ ጉዳይ ላይ ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ማስተማር የሚጠበቅብን ማስተማር አለብን፤ በፖሊሲ ቀረጻ ላይ የሚሳተፉ ምሁራንም ሥራቸው ላይ በአግባቡ መሳተፍ አለባቸው፡፡ ይህን ችግር፣ ችግር ነውና የአሀገራችንን መልኳን ያበላሸ፣ ስሟን ያጠፋ፣ ክብሯን ያሳነሰ ነው እስካልን ድረስ መመካከር አለብን፡፡ ይህ ሥራ ደግሞ የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የሁሉም አካል ግዴታ ነው፡፡ የሁሉም ተቋም ኃላፊነት ነው፡፡ የሕዝቡም ግዴታ ጭምር ነው፡፡ በዚህ መልኩ መረባረብ ካልቻልን ልንፈታው አንችልም፡፡

ጠባቂነትን፣ ተረጂነትን የሚያበረታቱ ሃሳቦች የትኞቹ ናቸው? ብለን ከለየን በኋላ በዚያ አመለካከት ላይ መሥራት አለብን፡፡ እንዲያውም ለዚህ ጉዳይ የእኛ ዘመን የተሻለ ዘመን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በመረጃ ልውውጥ ላወቀበት ሰው ብዙ ነገር ማግኘት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው እውቀትን እንዴት ገበያለሁ ብሎ አይጨነቅም። በማንኛውም አይነት የመገናኛ ዘዴ ትምህርቱን ማዳረስ ይቻላል፡፡ ወደየሰው እንዲደርስ ማድረግ በጣም ቀላል የሆነበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ የተመጽዋችነትንም ሆነ ርዳታ የመጠበቅን አመለካከት በእነዚህ መንገዶች ተጠቅመን ከማኅበረሰባችን ውስጥ ማስወገድ ይኖርብናል፡።

ተመጽዋችነትና ርዳታ ጠባቂነት የትውልድ መገለጫ ሊሆን አይገባውም፤ ምክንያቱም ኃይማኖት ባህልም አይደለም፡፡ ስለሆነም እንደትውልድ መሥራት አለብን። ተመጽዋችነትንና ርዳታ ጠባቂነትን ተረካቢዎችም አስተላላፊዎችም መሆን የለብንም። ይህ ተመጽዋችነትና ርዳታ ጠባቂነት የሚያሳንሰው ክብርን ብቻ ሳይሆን የደህንነታችንም ስጋት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ያለን እሴታችንን የሚያጠፋ ነው፡፡ በጀግንነታችን ያስከበርነውን ነጻነታችንን ጭምር የሚፈታተነው ይሆናል፡፡ የማንም ጥገኛ መሆን የለብንም፡፡ አንድ ነገር አምርተን ገበያ ሔደን ያመረትነውን ሸጠን አንዱን ገዝተን ብንመጣ ምንም ችግር አይኖረውም፡፡ ይህ የትም ቦታ የሚደረግ ነው። መግዛት መቻል በራሱ ክብር ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም መግዛት የሚችል አካል አንድ ያመረተው ነገር አለው ነው። ከዚህ የተነሳ በዋጋ ገዝቶ ወሰደ እንጂ ለማኝ አሊያም ጠባቂ አያስብልም፡፡ ነገር ግን በጤናው፣ በግብርናው፣ በትምህርቱና በሁሉም መስክ ጠባቂ ሆነን ከቆምን ትውልድን ተጠያቂ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

መምህር ዳንኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You