አረንጓዴው ጎርፍ በአረንጓዴ ዐሻራ

የዓለም አትሌቲክስ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 ባካሄደው ጥናት፤ የዓለም አየር ለውጥና ብክለት በቀጥታ የአትሌቶች ጤና እና ብቃት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን አረጋግጧል። ማህበሩ በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ ከነበሩ አትሌቶች መካከል 373 የሚሆኑትን በጥናቱ በማሳተፍም ነው ግኝቱን ይፋ ያደረገው። በዚህም መሰረት 85 ከመቶ የሚሆኑት አትሌቶች በከፍተኛ መጠን እየተቀየረ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ በብቃታቸው እና ጤናቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሰ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ይህ መጠን በቁጥር ሲገለጽም 60 ከመቶ ድርሻ እንዳለው ነው የተመላከተው።

እአአ በ2022 የአየር ንብረት ለውጥና ጤና ላይ በሚያተኩር ጆርናል ላይ የታተመ ጥናትም ይህንኑ ያጠናክራል። በቀጥታ ከትንፋሽ ጋር የሚያያዘው የአትሌቲክስ ስፖርት ልምምድ እና ዝግጅት የሚደረገው ከቤት ውጪ እንደመሆኑ የስፖርቱ ተዋናዮች ለአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቱ ይጠቁማል። ባለፉት ዓመታት ከምንጊዜውም በላይ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እያሳሰበ የሚገኝ ጉዳይ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት የሰው ልጆች በከፍተኛ መጠን እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋ እያስተናገዱ ይገኛሉ። አትሌቶች ደግሞ ከፍተኛዎቹ ተጠቂዎች ሲሆኑ፤ በከፍተኛ ሙቀትና የአየር ብክለት ሳቢያ ውድድሮችን እስከመሰረዝና ወደሌላ ጊዜ ማሸጋገር ተደርሷል።

በቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራትም አትሌቶቻቸው በዚሁ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ ከቤት ውጪ ሊኖር የሚገባውን ጤናማ አየር በቤት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ ልምምድ ይሰራሉ። የውድድር አዘጋጆችም የተሻለ የአየር ሁኔታ የሚኖርበትን ወቅት ከመምረጥ ባለፈ በስታዲየሞች ውስጥ የተመጣጠነ አየር እንዲኖር የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እስከመጠቀም ደርሰዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን አትሌቶችን ለጉንፋን መሰል በሽታዎች እንዲሁም የእጅ እና እግር መገጣጠሚያዎችን ለሚያዳክም ህመም ሊዳርጋቸው ይችላል። ከዚህ አለፍ ሲልም ለሳንባ፣ አስም፣ ልብ፣ ስትሮክ፣ አለርጂ እንዲሁም መሰል ለሆኑ በከፍተኛ ሙቀት የሚከሰቱ በሽታዎች በተጨማሪም ለጉዳት እንደሚያጋልጣቸው ጥናቱ ያትታል።

የትንፋሽና የጥንካሬ ስፖርት ለሆነው አትሌቲክስ የአየር ሁኔታ መሰረታዊው ጉዳይ ነው። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ በአትሌቶቿ በዓለም አቀፍ መድረኮች መልካም ገጽታን ለገነባች ሀገር ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ አሳሳቢ ይሆናል። የኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች፣ ድንቅ ተፈጥሮን የታደሉ አረንጓዴ ስፍራዎች የብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ በመሆናቸው የውጪ ሀገራት አትሌቶች ከዚህ በረከት ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋሉ። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙት እንደ እንጦጦ እና የካን የመሳሰሉ ጫካዎች የበርካታ ውጤታማ አትሌቶች ባለውለታዎች ናቸው። ነገር ግን በከተማ መስፋፋት እንዲሁም ከዘመኑ ጋር በተያያዙ በርካታ ጉዳዮች ቀድሞ ለአትሌቶች ምቹ የነበሩ በዛፎች የተሸፈኑ ስፍራዎች እንደነበሩ አይገኙም። በዚህም የአየር ሁኔታው እየተቀየረ ሞቃታማነቱ እያመዘነ ይገኛል። ይህም ስፖርቱን እንዳደጉት ሀገራት ስጋት ላይ ከመጣሉ በፊት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ሥራ ማከናወን ተገቢ እንደሚሆን ተደጋግሞ ሲጠቆም ቆይተል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ለዓመታት እየተተገበረ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ላይ የአትሌቲክሱ ማህበረሰብ በስፋት ተሳታፊ በመሆን ላይ ይገኛል። በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ልኡክ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አቀባበል በተደረገለት ወቅት አረንጋዴ አሻራውን በማኖር ሀገራዊ ሌጋሲውን በባህር ማዶ ማስቀጠሉ የሚታወስ ነው። ከኦሊምፒኩ መልስም የድል ባለቤት የሆኑት አትሌቶችን ከሌሎች ሙያተኞች ጋር በመሆን በጉለሌ የዕጽዋት ማዕከል ችግኝ ተክለዋል። ይህንንም ተከትሎ በማራቶን ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው አትሌት ታምራት ቶላ፤ ችግኝ መትከል ህይወት መሆኑን አረንጋዴ አሻራውን ሲያሳርፍ የገለጸው። ‹‹ለድል የበቃሁት በደን በተሸፈነው እንጦጦ ተራራ ተለማምጄ ነው። ሁሉም ዜጋ ችግኝ መትከልን ባህል ማድረግ ይገባዋል›› ሲልም የማራቶን ባለድሉ አስተያየቱን ሰጥተል።

ከታምራት በተጨማሪ የማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ትዕግስት አሰፋ፣ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው በሪሁ አረጋዊ፣ በስምንት መቶ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ፅጌ ዱጉማ እንዲሁም የ3ሺ ሜትር መሰናክል የክብረወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ አረንጋዴ አሻራቸውን ያሳረፉ ብርቅዬ አትሌቶች ናቸው።

ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይም በተመሳሳይ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማትን ጨምሮ የሌሎች ስፖርቶች በስፋት ተሳታፊ ለመሆን ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You