ጌዲኦ ብሔረሰብ ጥምር ግብርናና የአረንጓዴ ዐሻራው የችግኝ ተከላ

ኢትዮጵያውያን በዛሬው እለት በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ 600 ሚሊዮን ችግኞችን ይተክላሉ፡፡ ችግኞቹ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሸቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ተተክለው እንደሚጠናቀቁ መረጃዎች አመልክተዋል።

ላለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለመጨመርና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ባደረገችው ርብርብ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በያዝነው ክረምትም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ አብዛኛው ተከላ ተካሂዷል፡፡ የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም የዚሁ ሀገራዊ ንቅናቄ አካል ነው፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ሀገራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከትሎ ርእሰ ጉዳዩን በዚሁ ጉዳይ ላይ ለማድረግ ወድዷል። በተለይ በኢትዮጵያውያን ባሕል ችግኝን የመትከልና የመንከባከብ ባሕል ምን እንደሚመስል ለመመልከት ፈቅደናል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር እና የኑሮ ዘይቤያቸውንና ትስስራቸውን ከመልከዓ ምድሩ ጋር ያደርጋሉ፡፡

በዚህ በኩል እንደ ዋንኛ ምሳሌ ከሚነሱት የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ውስጥ የጌዲኦ ብሔረሰብ ይጠቀሳል። ማህበረሰቡ ለሺህ ዘመናት ጠብቆ ያቆየው መልከዓ ምድርና የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም የትክል ድንጋዮቹ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በዩኔስኮ ተመዝግበዋል። ለዚህም ነው በዛሬው የሀገረኛ አምድ ላይ 600 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ቀን በሚተከሉበት እለት የጌዲኦ ሕዝብ የደን አጠባበቅ ሥርዓት፣ ባሕላዊ እሴት እና ሀገር በቀል እውቀትን ከዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር ለማንሳት የወደድነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጌዲዮን ባሕላዊ መልከዓ ምድርና የትክል ድንጋይ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ኃላፊነቱን ወስዶ ተግባራዊ ሥራ በመሥራቱ ባለፈው መስከረም ወር በይፋ ተመዝግቧል። ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመለክተው፤ የጌዲኦ ሕዝብ ደንን የመንከባከብ ባሕሉ ከ5000 ዓመት በፊትም አንስቶ የነበረ ነው። የጌዲኦ ሕዝብ ባሕላዊ ግብርና ሥራዎች የእጽዋት፣ የፍራፍሬ፣ የሰብል ምርቶችና በጣዕሙ የሚታወቀውን የይርጋጨፌ ቡና በማምረት እንደሚታወቅ ይገልፃል፡፡

ሰነዱ ጌዲኦ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲጠብቀው የቆየ ጥብቅ ደን ያለው መሆኑን ጠቅሶ፤ ጥምር ግብርናም የሚካሄድበት መሆኑ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ገጽታው መሆኑን አመልክቶናል። የጌዲኦ መልክዓ ምድር ቅርስ የማኅበረሰቡን መስተጋብር፣ አኗኗር ከማሳየቱም ባለፈ የበርካታ አእዋፋት፣ እንስሳትና አዝርዕት መገኛ ሲሆን፤ ሰው ከተፈጥሮ ጋር እንዴት መኖር እንደሚችል የሚያሳይ መሆኑ ለምዝገባው ወሳኝነት እንደነበረው ያመለክታል።

ባሌ የተሰኘው የጌዲኦ ብሔረሰብ የሚተዳደርበት የገዳ ሥርዓት፣ በየዓመቱ የሚያከብረው የዘመን መለወጫ በዓል ደራሮ ፣ አባ ገዳዎች ለሁሉም የጌዲኦ ሕዝቦች ስለ አካባቢ ጥበቃ እና ደን እንክብካቤ የሚያስተላልፏቸው የተለያዩ መልዕክቶች የብሔረሰቡ መለያዎች ናቸው። የብሔረሰቡ አባላት ጥብቅ ደኖች ሳይነኩ ጥምር እርሻ እንደሚያካሂዱ በሰነዱ ተጠቁሟል። በጌዲኦ ከባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት የተነሳ ኅብረተሰቡ ዛፍን “እንደ ልጅ” የማየት ባሕል እንዳለውም ይገልፃል።

ይህን የጌዲኦ ብሔረሰብ ባሕላዊ እሴት አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የጌዲኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የጌዲኦ ብሔረሰብ ‹‹ባሆ›› /አሁን አረንጓዴ ዐሻራ/ በሚባለው ሥርዓቱ የተለየ ቁርኝት ያለው ማህበረሰብ ነው። አጠቃላይ የዞኑ የደን ሽፋን እንሰት፣ ቡና እና ዛፍ በተካተቱበት የጥምር ደንና ግብርና (agrofor­estry) ሥራው ይታወቃል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መጀመር ደግሞ የጌዲኦ ብሔረሰብ ያለውን የበለጠ የሚያጠናክርና ሀገር በቀል አያያዝ ሥርዓት በሳይንሳዊ መንገድ እንዲያጎለብት አስችሎታል ሲሉ አስታውቀዋል። ከአካባቢ ጥበቃና ከተፈጥሮ ጋር የመኖር ባሕል ከጥንት ጀምሮ ሲተገብረው የኖረው እሴቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የጌዲኦ ብሔረሰብ ባሕላዊ የደን አያያዝ ሥርዓት (agroforestry) በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቶት በዩኔስኮ የባሕላዊ መልከዓ ምድር ቅርስ ዘርፍ መመዝገብ ችሏል›› የሚሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ ከማህበረሰቡ የሚጠበቀው ይህንን ማስቀጠል መሆኑንም አስታውቀዋል።

በመሆኑም ትውልዱ አባቶቹ ጠብቀው እዚህ ያደረሱትን ሀብት እና በአካባቢው ላይ ያለውን የተለየ ሀብት፣ የመሬት አቀማመጥ ሥርዓት ከዘመናዊውና ሳይንሳዊው የአጠባበቅ ሥርዓት ጋር በማቀናጀት ለመጪው ዘመን ጠብቆ ሊያቆየውና ለልጆቹ ሊያስተላልፍ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። የጌዲኦ ዞን እንደ ሀገር እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ ላይም በልዩ ሁኔታ ተሳታፊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

የጌዲኦ ማህበረሰብ ሌላ ልዩ ባሕልም አለው፡፡ ይህም ዛፍን በዘልማድ መቁረጥ በጥብቅ የተከለከለበት ነው ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰው፣ ነዋሪው አንድን ዛፍ ለመቁረጥ ሲያስብ በምትኩ አስር የሚደርሱ ዛፎችን ለመተካት ማረጋገጫ መስጠት እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡ በመጀመሪያ ለዚህ ማረጋገጫ ሰጥቶ ነው ወደ መቁረጡ የሚገባው ብለዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ከማግባቱና ቤተሰብ ከመመስረቱ በፊት በሽምግልና ጊዜ ‹‹ምን ያህል ሀብት አለው›› ሳይሆን ‹‹በጓሮው አሊያም በማሳው ውስጥ ምን ያህል ዛፍ አለው›› ተብሎ እንደሚጠየቅ ጠቅሰው፣ ቤተሰብ ለመመስረት ዋናው የብሔረሰቡ ባሕላዊ እሴት መሆኑን ያስረዳሉ። ዛፍን መንከባከብ እና ዛፍን መትከል ልማዱ ያደረገ አንድ ወጣት ቤተሰብ ለመመስረት የሚያስችል እውቅናን እና ክብርን እንደሚያገኝም ይገልፃሉ።

‹‹ይህንን ሀገር በቀል ባሕል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት እየተተገበረ ከሚገኘው አረንጓዴ ዐሻራ ጋር በማስተሳሰር እጅግ በጣም በረሃማ የነበሩ አካባቢዎችን የመለወጥ ሥራ እየተሰራ ነው›› የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ባሕላዊ ሥርዓቱም አካባቢን አረንጓዴ አድርጎና መልከዓ ምድሩን ጠብቆ ለመቀጠል ትልቅ ኃይልና እሴት እንደሚሆን አስታውቀዋል። ባሕሉን ጠብቆና ለትውልዱ አስተምሮ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግም የዞኑ አስተዳደር እና ማህበረሰቡ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

‹‹ደራሮ የጌዲኦ የአዲስ ዓመት /ዘመን መለወጫ/ ነው›› የሚሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ ከዚህ ባሻገር ደራሮ በምግብነት እንደሚገለፅም ተናግረዋል። ከገብስ፣ ከቡናና ከማር የሚዘጋጅ ተወዳጅ ባሕላዊ ምግብ ደራሮ እንደሚባልም ይገልፃሉ።

የደራሮ ትሩፋት ከሚባለው ውስጥ የሕዝብ አባት ተብለው የሚታወቁት ‹‹አባገዳ›› አንዱ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ በየዓመቱ የጌዲኦ ዘመን መለወጫ በሚከበርበት ወቅትም አባገዳው ያልተፃፉ ዘጠኝ ሕጎችን(ላላባ) በማውጣት ማህበረሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርጓቸው ትእዛዝ እንደሚያስተላልፉ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዓመት በተቀየረና ዘመን በተለወጠ ቁጥር ከዘጠኙ ሕጎች ውስጥ የማይቀየረውና ሁሌም እንደ ሕግ የሚወጣው ከዛፍ ጋር የተገናኘው ሕግ መሆኑን ይገልፃሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በየዓመቱ ሳይታደስና ሳይቀያየር ማህበረሰቡ እንዲያከበረው የሚወጣው ሕግ ማህበረሰቡን ‹‹ዛፍ ትከሉ፣ ዛፍ ተንከባከቡ፣ ዛፍ አላግባብ የሚቆርጥ ሰው እንዳይኖር›› በማለት በአደባባይ የደራሮን በዓል በሚያከብርበት ወቅት በባሕላዊ ትእዛዝ መልክ የሚተላለፍለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹በሶንጎ›› (ባሕላዊ የሽምግልና) ሥርዓትም አንድ ዛፍን ተገቢ ባልሆነ መንገድ የቆረጠና ደንን የጨፈጨፈ ሰው በባሕላዊ መንገድ በጌዲኦ አባቶችና በሥርዓቱ ጠባቂዎች ጉዳዩ በዳኝነት እንዲታይ ተደርጎ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ቅጣት እንደሚተላለፍበት ይገልፃሉ።

ይህ ባሕላዊ ሥርዓት በጌዲኦ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲተገበር መቆየቱ የደን አያያዝ ሥርዓቱ ሳይዛነፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ይህ የማህበረሰቡ እሴት ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ እንዳስቻለውም ይናገራሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ የመትከል ተግባር እያከናወነ መሆኑን የሚገልፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ ዘንድሮም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ሰፊ ሥራ ተሰርቶ የችግኝ ተከላው እየተገባደደ መሆኑን ይገልፃሉ።

እርሳቸው በሚያስተዳድሩት የጌዲኦ ዞንም የአየር ንብረት ለውጥን የሚከላከሉና የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከልም ዝግጅቱ መጠናቀቁን ያነሳሉ። የጌዲኦ ዞንና ማህበረሰብም የዚህ መርሃ ግብር ዋናው ተሳታፊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት በዞኑ 100 ሚሊዮን የሚደርሱ የቡና፣ የእንሰት፣ ፍራፍሬና የተለያዩ ችግኞችን የመትከል ተግባር መከናወኑን አቶ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ገልፀዋል። ዛሬ በአንድ ጀንበር በመላው ኢትዮጵያ እስከ 12 ሰዓት ድረስ የሚካሄደውን የ600 ሚሊዮን ችግኞች ተከላን በተመለከተም የዞኑ ነዋሪዎች የድርሻቸውን ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

ሕዝቡ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ሙሉ ቀን አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞችን እንደሚተከልም ማረጋገጫቸውን ሰጥተዋል። ለክንውኑም በቂ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ተናግረው፣ የሚተክልበት ቦታም መለየቱን አስታውቀዋል። ዋናው መርሃ ግብርም እንደ ዞን በራጵያ ወረዳ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ እያንዳንዱ የዞኑ ነዋሪ 25 የዛፍ ችግኞችን መትከል እንዲችል እቅድ መውጣቱን አስታውቀዋል።

የዞኑ የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ መረጃ እንዲያመለክተው፤ የጌዲኦ ሕዝብ በአካባቢ ጥበቃ ባሕሉ ደንና አካባቢን እንደ ልጁ በመንከባከብ ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ባሕላዊ እውቀት ያለው ሕዝብ ነው። ይህም እሴቱ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ሕጋዊ ሰርተፍኬት አግኝቷል። ማህበረሰቡ በባሕላዊ መልከዓ ምድሩ ብቻ የሚታወቅ አይደለም፤ እጅግ በርካታ እሴቶችን የያዘ ማህበረሰብ ለመሆኑ አያሌ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ብሔረሰቡ በጥምር የግብርና ሥርዓቱ፣ በሜጋሊቲክ ሀውልቶች፣ በሮክ ጥበብ ቦታዎች እና በባሕላዊ እሴቱ በተጠበቁ ደኖች ልዩ መሆኑን ይህ ባሕላዊ እሴቱ አስመልክቶ የተሰናደ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የጌዲኦ ማህበረሰብ በአካባቢው ከሚኖሩበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር የተጣጣመ የግብርና ባሕል እና በረቀቀ የአግሮ ደን ልማት ሥርዓት ይታወቃል። ይህም መሰል ልምድ ለሌላቸው አካባቢዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ስለመሆኑ መገመት አያዳግትም።

በዞኑ የሚገኘው ወግድ አምባ በዩኔስኮ በሚዳሰስ ቅርስነት “የጌዲኦ ጥብቅ ደን” የሚገኝበት ቀበሌ ነው። ከዲላ እስከ ወግድ አምባ ያለው አካባቢም በጥምር ግብርና ሥርዓት፣ በመልካ ምድሩና በጥቅጥቅ ጥብቅ ደን የታደለ በመሆኑ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አድርጎታል። ሌላው በጌዲኦ የሜጋሊቲክ አርኪኦሎጂካል ስፍራዎች በብዛት ይገኛሉ። ለአብነትም ቱቱ ፈላ ሜጋሊቲክ፤ ጨልባቲቲቲ ሜጋሊቲክ፣ ሴዴ መርካቶ ሜሜጋሊቲክ፣ አዶላ ጋልማ ሮክ ጥበብ እንዲሁም የተቀደሱ ደኖች እና ሌሎችም በርካታ እምቅ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡

ከዞኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የጌዲኦ ብሔረሰቡ በስፋት የሚገኝበት አካባቢ በአብዛኛው ተራራማና ወጣገባነት ያለው ነው፤ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሜዳማ የሆነ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ የለውም ነው። ከብሔረሰቡ ወረዳዎች መካከል ቡሌ፣ ይርጋጨፌ፣ ኮቸሬ እና ገደብ ወረዳዎች ደጋና ወይና ደጋ የሆነ የአየር ንብረት ሲኖራቸው፣ የተቀሩት የወናጐ እና ዲላ ዙሪያ ወረዳዎች ደጋ፣ ወይናደጋ እና ቆላማ የአየር ንብረት ያለባቸው ናቸው። የአረንዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አስመልክቶ ዛሬ በመላው የጌዲኦ ዞን ከአራት ሚሊዮን ችግኝ በላይ እንደሚተከል ይጠበቃል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You