የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በውጤታማነት ሕዝብ የለመደውን ድል ከማስመዝገብ ይልቅ በውዝግብና ትርምስ መንስዔ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። ከአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ከውድድር ውጤቶች ጋር የተያያዙ ውዝግቦች ስፖርቱን እንዳይረጋጋና በውጤታማነቱ እንዳይቀጥል አድርጓል። ይህም በፓሪስ ኦሊምፒክ በስፋት ሲንጸባረቅ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና የአትሌቲክስ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ ያስረዳሉ። ለዚህም በዋናነት የአመራር ክፍተት ምክንያት ነው ይላሉ።
እንደ ኢንስትራክተር አድማሱ ገለፃ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተደራጀና በራሱ ገቢ የሚተዳደር እንዲሁም እስከ ክልል ድረስ የተዘረጋ የአስተዳደር መዋቅር አለው። መሆኑን በዚህም መዋቅር ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ተቀናጅቶ የአትሌቲክስ ልማት ሥራዎችን ይሠራል። በሂደቱም አትሌቶችን አና አሠልጣኞችን መልምሎ እና አሰልጥኖ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ በማድረግ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም ከባህልና ስፖርት ጋር በመተባበር እስከ መጨረሻው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ከአሠራር ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የመጠላለፍና ሥራዎችን በትክክል ቆጥሮ በማሠራት ክፍተት ምክንያት የችግሮች መንስኤ ሆነዋል።
የአትሌቶችና አሠልጣኞች ምልመላ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ አይደለም። በዚህም የተነሳ ግለሰቦች ከሀገር እና መንግሥት በላይ ሆነው እምቢተኝነት በማስፈን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን አደረጃጀት ይጥሳሉ። የአደረጃጀት ክፍተቱም በአመራሩ ግልጽ ያልሆነ አሠራር በመዘርጋቱና ትክክለኛው አካሄድ ሥራ ላይ ባለመዋሉም ነው። አሠራሩ ግልጽነት የሚጎድለው፣ ያልተናበበ፣ ያልተጣጣመ ነው። ከዚህም የተነሳ አንዳንድ አትሌቶች የአቅም ማነስ ሌሎች ደግሞ አቅም እያላቸው አለማሸነፍ የሚከሰተው ግልጽ የሆነ አመራር እና የአሠራር ክፍተት በመኖሩም ነው። እነዚህን ጉዳዮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ግልጽ አደረጃጀትን፣ አመራርና አሠራርን በማስፈን እንዲሁም በመፈተሽ ስህተቶች እንዳይደገሙ የሚያደርግ ሥራ መሠራት እንዳለበት ይናገራሉ።
በረጅም ርቀቶች የሚታየው የውጤት ማጣት የመጣው ከሥልጠና ክፍተት ነው የሚሉት ኢንስትራክተር አድማሱ፤ ይህም ከአመራርና አሠራር ክፍት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። አትሌቶች በዘመዶቻቸው መሠልጠናቸውና የአንድ አንድ አሠልጣኞች ውጤታማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይም ብቁ ያለመሆናቸውን የሚያመላክት ነው። አትሌቶች በቤተሰብ አማካኝነት የሚሰለጥኑ ከሆነ ከመተዛዘን የተነሳ ተገቢው ሥራና ሥልጠና እንዳይሰጥና የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ምክንያት ይሆናል። የአሠልጣኝነት ሥነምግባር፣ እውቀትና ልምድ ያለው ከሆነ ግን ሥራውን ብቻ መሠረት አድርጎ ትክክለኛ ሥልጠና በመስጠት ውጤት እንዲመጣ ይሠራል። አትሌቶች ለውድድር ዝግጅት የሚያደርጉት ተነጣጥለውና በተለያየ አሠልጣኞች ስር መሆኑ እንዳይተጋገዙ እና አቅማቸውን አውቀው እንዳይሠሩም አድርጓል ይላሉ።
ይህም የጥቅም ግጭት ከመፍጠሩ ባለፈ በአንድ ቡድን ተጠቃለው መሥራታቸው የፌዴሬሽን እና የኦሊምፒክ ቴክኒክ ኮሚቴ አመራሮች ምርጫ ላይ እንዲወዛገቡ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት አንጸባራቂ ድልን ያስመዘገበችው በአንድ ብሔራዊ ቡድን ተሠርቶ እንደሆነ ባለሙያው ያስታውሳሉ። ይህም አዋጭ እንደሆነ ጎረቤት ሀገራት በውድድር መድረኮች ያስመለከቱበት እና በአስደማሚ ውጤት በዓለም አቀፍ አንቱታን ያተረፉ አትሌቶች የተፈጠሩበት ርቀት እንደሆነም ያክላሉ።
የአሠራርና አደረጃጀት ክፍተት አንዱ ማሳያና ለውጤት መጥፋት መንስኤ የሆነው በተበታተነ፤ ለክትትልና ለድጋፍ በማይመች እንዲሁም አንድነትና ህብረትን ለመገንባት በማይመች ሁኔታ ሥልጠና በመሰጠቱ ነው። ሳይንሱን ለመተግበርም በስፖርቱ ውስጥ አልፎ እና አግባብነት ያለውን ሥልጠና ወስደው መሥራት ሲገባቸው፤ በዝምድና እና በታዋቂነት ተጠቅመው የሚሠሩ እንዳሉም ይጠቅሳሉ። ጥብቅ በሆነ ዲሲፕሊን፣ አመራር፣ አሠራር እና ቅንጅት ካልተሠራም ባለሙያዎቹ በሳይንስ ብቻ ስለተመሩ ውጤት ማምጣት አይቻልም ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከተፎካካሪ ሀገራት ጋር በሚገባት ደረጃ ለመፎካከር እና የቀደመውን የድል ታሪክ ለመመለስ ወቅቱን በሚመጥን ሁኔታ መሥራት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ትናንት ጠንካራ የነበረች እና አሁን በብዙ የውጤት መጥፋት ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም፣ የትናንቱን አቅምና ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ወደ ውጤታማነት መመለስ ይቻላል ባይ ናቸው። ‹‹ሌሎች ሀገራት ጠንክረው ስለመጡ እኛ እጃችንን አጣምረን መቀመጥ ሳይሆን እኛ ምን ሥራ ሠራን? ምንስ ዋጋ ከፈልን? ብለን መጠየቅ ይገባል›› ይላሉ። አሜሪካውያን፣ ኖርዌዥያን፣ ጣሊያናውያን እና ሌሎች ሀገሮች በረጅም ርቀት ሩጫ ጠንክረው እንደመጡ ማሳያዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ኢንስትራክተሩ፣ ከፍተኛ የሆነ የአትሌቲክስ ኢንቨስትመንት መደረግ እንዳለበት ያምናሉ። ኢትዮጵያ ካላት የአትሌቲክስ ሀብት አኳያ ሰው ሠራሽ ችግሮችን በመፍታት በጥቂት ጊዜ ወደ ቀደመው ውጤታማነቱ መመለስ እንደሚቻልም ይገልጻሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም