ኢትዮጵያ የብዙ ደማቆች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ይታወቃል፡፡
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ከልጅነታቸው ጀምሮ ወደሚፈልጉት የውትድርና የሙያ መስክ ተሰማርተው ጠንካራ ወታደር ሆነው የሚወዷትን ሀገራቸውን በሙሉ ጀግንነትና ፍቅር በማገልገል የሚታወቁት ብርጋዴር ጄኔራል ዘገየ ልዑልሰገድ አንዱ ናቸው።
ብርጋዴር ጄኔራል ዘገየ ልዑልሰገድ ከአባታቸው ከአቶ ገድለጊዮርጊስ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በለጠች እምሩ በ1934 ዓ.ም በሐረር ክፍለ ሀገር ጅጅጋ ከተማ ተወለዱ፡፡ በጅጅጋ የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር አሰበ ተፈሪ መጥተው ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በአሰበ ተፈሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ካጠናቃቀ በኋላ ሚኒስተሪ ተፈትነው እንዳለፋ ከ9ኛ ክፍል ጀምረው በሐረርጌ መድሃኒዓለም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ፍላጐታቸው ሀገራቸውን በውትድርና ማገልገል በመሆኑ ለእጩ መኮንንነት የሚያበቃቸውን ፈተና አልፈው ጥር 30 ቀን 1954 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በ22ኛ እጩ መኮንኖች ኮርስ ገብተው ኮርሳቸውን በሚገባ ስለፈጸሙ ግንቦት 10 ቀን 1955 ዓ.ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በምክትል የመቶ አለቅነት ተመርቀዋል፡፡ ከዛም በየደረጃው እየተሾሙ ከምክትል መቶ አለቅነት እስከ ብርጋዴር ጀኔራልነት ማዕረግ ደርሰዋል።
ተዘዋውረው የስሩባቸው ክፍሎችና የሥራ ኃላፊነት፦
2ኛ ክፍለ ጦር 12ኛ ብርጌድ 34ኛ ሻለቃ ማይሓባር ኤርትራ በመቶ መሪነት፤ ኤርትራ ምዕራባዊ ቆላ በመቶ መሪነትና ሻምበል አዛዥነት፤ 2ኛ ክፍለ ጦር 12ኛ ብርጌድ በሞርታር በመቶ መሪነት፤ 2ኛ ክፍለ ጦር በአስተዳደር መኮንንነት፤ 2ኛ ክፍለ ጦር በአስተዳደር መመሪያ ረዳት መኮንን፤ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ አዲስ አበባ አስተዳደር መምሪያ ምክትል ኃላፊነት፤ በኤርትራ ክፍለ ሀገር አልጌና በክፍለ ጦር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊነት፤ ወደ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ ተዛውረው የምድረ ጦር አስተዳደር መምሪያ በምክትል መምሪያ ኃላፊነት ስርተዋል።
በአገልግሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ የወሰዱዋቸው ወታደራዊ ትምህርቶችና ስልጠናዎች፦
- የእጩመኮንንነትኮርስበቀደማዊኃይለሥላሴገነትጦርትምህርትቤትሆለታ
- ፀረጐሪላትምህርትበአሜሪካንአስተማሪዎችበቀዳማዊኃይለሥላሴጦርትምህርትቤትሆለታ
- ከፍተኛየአስተዳደርናሎጀስቲክስትምህርትበእስራኤሎችናበኢትዮጵያኖችአስተማሪዎችሆለታቀደማዊኃይለሥላሴጦርትምህርትቤት
- በቀድሞሶቭየትሕብረትሩስያከፍተኛአዛዥነትናስታፍመኮንንነትኮርስ
የተሸለሙዋቸው ሜዲዮችና ኒሻኖች፦
- በኤርትራክፍለሀገርየፀጥታማስከበርተካፋይስለነበሩአብዮታዊዘማችአርማ
- ለሀገራቸውላበረከቱትከፍተኛግዳጅናታማኝነትየቀዳማዊኃይለሥላሴየወርቅሜዳልያ
- ለአኩሪአፈፃፀማቸውከተለያዩየበላይአዛዦቻቸውየተሰጡዋቸውየምስጋናደብዳቤዎችበርካታናቸው፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ዘገየ ልዑልሰገድ ከበላዮቻቸው የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ትዕዛዞች በተለይ በሰሜን ጦር ግንባር በመቶ መሪነትና በሻምበል አዛዥነት በማዕረግ ካደጉ በኋላም በክፍለ ጦር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊነት በጦርነትና በመጥፎ አየር ፀባይ ባለበት ቦታ ከእሳቸው የሚፈለገውን ሁሉ ለሀገራቸው ያበረከቱ ጄኔራል መኮንን እንደነበሩ ታሪካቸው ይነግረናል።
በአገልግሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ በወሰዱዋቸው ትምህርቶችና ስልጠናዎች በነበራቸው ረጅም የሥራ ልምድ ከእሳቸው በታች ለነበሩ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች ልምዳቸውን በማካፈል በተለይ በአስተዳደር ብዙ ተተኪ መኮንኖችና ባለ ሌላ ማዕረግተኞች ማፍራት የቻሉ ነበሩ፡፡ ከ1927 እስከ 1983 ዓ.ም የቀድሞ ሠራዊት መጽሐፍ አዘጋጅ ከሌሎች አዛዦቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር ለመጽሐፉ ዝግጅት ላደረጉት አስተዋጽኦ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
የጄኔራል ዘገየ የረዥም ጊዜ የሥራ ባልደረባና ወዳጃቸው የሆኑት ኮሎኔል አስመላሽ መድሃኔ እንደሚናገሩት፤ በ1954 ዓ.ም ጥር 30 22ኛ ኮርስ ተማሪዎች ሆነን ሆለታ ጦር ትምህርት ቤት በመቀላቀል ግንቦት 10 ቀን 1955ዓ.ም የወታደራዊ ትምህርታችንን በማጠናቀቅ ተመረቅን የሁለታችን ወዳጅነትም የሚጀምረው ከዚህ ነው ይላሉ።
ጄኔራል ዘገየ ከትምህርት በኋላ ለግዳጅ ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ተሰማርቶ በመቶ መሪነት በኋላም በሻምበልነት ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ የክፍለ ጦሩ ረዳት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ እስከመሆን ደርሷል የሚሉት ኮሎኔል አስመላሽ፤ በወታደራዊ ዲስፕሊንና በሥራው ከፍተኛ አፈፃፀም የነበረው በመሆኑ የወቅቱ የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት ሰው ወደ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ አዲስ አበባ ሲመጡ ጄኔራል ዘገየን ይዘው በመምጣት ሥራውን አዲስ አበባ ሆኖ እንዲሰራ አድርገውታል።
በመቀጠል ለአዛዥነትና ስታፍ መኮንንነት ስልጠና ወደ ራሺያ ተጉዞ ስልጠናውን በብቃት በማጠናቀቅ የተመለሱት ጄኔራል ዘገየ፤ ከስልጠና መልስ ወዲያው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመጓዝ በጦር ግንባር ሀገር የሰጠቻቸውን የቃል ኪዳን አደራ በፍፁም ጨዋነት ተወጥተዋል።
በጦር መሪነት ሰፊ ልምድና እውቀት የነበረችው ጄኔራል ዘገየ፤ እርሳቸውን በትምህርት ብቁ ለማድረግ የተጉ በጦር ግንባር በፈፀሙት ከፍተኛ ጀብዱ እስከ ብርጋዴር ጄኔራል ማዕረግ የደረሱ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለነበራቸው ወታደር የመሆን ህልም ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው።
ጄኔራል ዘገየ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ለሀገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነት እንደ ከንቱ ተቆጥሮ እስር ቤት እንደገቡ የሚናገሩት ኮሎኔል አስመላሽ፤ ለሰባት ዓመት በእስር የቆዩ ቢሆንም በግለሰቦች የደረሰባቸው በደል ሀገራቸውን ከመውደድ ያልገደባቸው የመርህ ሰው እንደነበሩ ይናገራሉ።
በወታደራዊ ተቋም ባሕል የወታደር መርሆ አስፈላጊው ምሰሶ ነው። ለተልዕኮውም፣ መሳካት ከተገቢው ወታደራዊ ልምምድ በተጓዳኝ፣ ወታደሮች የሀገርን ጥቅም ከራሳቸው የማስቀደም ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል። ከክፍያም በላይ፣ ጀግንነት፣ ተገዢነት፣ መስዋእትነትና የሀገርን ሕዝብ ከአደጋ መከላከልና መጠበቅ አጓጊና አነሳሽ ናቸው የሚሉት ኮሎኔል አስመላሽ ከዚህ መመዘኛ አንፃር ጄኔራል ዘገየ የሙያዊ ግዴታቸውን በብቃት ተወጥተዋል ይላሉ።
ወታደሮች ለሙያቸው ፍቅር ያላቸው መሆን አለባቸው የሚሉት ኮሎኔል አስመላሽ፤ ከፍተኛ ክህሎት ያለው ወታደር መሆን ማንም ሊሆነው የሚችለው አይደለም። መመሪያና እሴቶች ከፍተኛ ክህሎት ያለው ሠራዊት ለመገንባትና ለማቆየት በጣም አስፈላጊ ናቸው ከዚህ አኳያ ጄኔራል ዘገየ የተመሰከረላቸው ወታደር እንደነበሩ ይናገራሉ።
የጄኔራሉ የሀገር አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚናገሩት ኮሎኔል አስመላሽ፤ ጄኔራል ዘገየ ከወታደራዊ ስልጠናው በኋላ የተመደቡት ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ነበር፤ እሳቸው ወደዚያ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ክፍለ ሀገሩ ላይ ሰላም አልነበረም፡፡ ጦርነትና ግጭት ጠፍቶ አያውቅም በዚህም ጄኔራል ዘገየ ከምክትል መቶ መሪነት ጀምሮ እስከ ሻምበል መሪነት ከአማፅያን ጋር በሚደረገው ውጊያ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተዋድቀዋል።
ጄኔራል ዘገየ ከቤተሰብ ከዘመድ ወዳጅ ተለይቶ አስቸጋሪ የሕይወት ውጣውረድ በመቋቋም ለ20 ዓመታት ግዳጁን እየተወጣ በኤርትራ ሀገር ኖሯል የሚሉት ኮሎኔል አስመላሽ፤ በቆይታውም ለሀገሩ ግዛታዊ አንድነት መጠበቅ ከከፈለው መስዋዕትነት በተጨማሪ የበታች ወታደር የሙያ አጋሮቹን በወታደራዊ ሙያ ክህሎታቸውን ለማሳደግና ተተኪ ለማፍራት በውጭ ሀገር ያገኘውን ትምህርትና ስልጠና በመጠቀም የአቅም ግንባታ ሥራ ስሰራ እንደቆየ ይናገራሉ።
የ22ኛ ኮርስ ተማሪዎች ትምህርታችንን አጠናቀን ስንመራቅ ቁጥራችን 155 ነበር የሚሉት ኮሎኔል አስመላሽ፤ ከእነዚህ ውስጥ የጄኔራልነት ማዕረግ ደረጃ የደረሱበት ስምንት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ጄኔራል ዘገየ አንዱ ነው። ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ጠንካራ ወታደራዊ ባለሙያ እንደነበር ነው ይላሉ።
በጊዜው ይሰጥ የነበረው ወታደራዊ ስልጠና እጅግ ፈታኝ መልከዓ ምድርና የአየር ሁኔታን መቋቋም የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙዎች ስልጠናውን መቋቋም ስለማይችሉ ከሠራዊቱ የሚኮበልሉበት ጊዜ እንደነበር የሚናገሩት ኮሎኔል አስመላሽ፤ በዚህን ወቅት ጄኔራል ዘገየ በጥንካሬ ስልጠናውን በመወጣት ለሌሎች የሠራዊት አባላት ምሳሌ መሆን የቻለ ነው ይላሉ።
ከወታደራዊ ሙያቸው ባሻገር በግል ፀባያቸውም ርህሩህና፣ የተቸገሩትን የሚረዱ የታመመን የሚጠይቁ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄኔራል ዘገየ፤ በሀዘንም ሆነ በደስታ ከወዳጆቻቸው ጎን የማይለዩ ለቤተሰቦቻቸው፤ ለልጆቻቸው፣ ወንድሞችና እህቶቻቸው አለኝታ የሆኑ በጓደኞቻቸው በጣም ተወዳጅ ጄኔራል መኮንን ነበሩ፡፡
በ1964 ዓ.ም ከወይዘሮ ፀሐይ ሣህሌ ጋር ትዳር በመመስረት ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች በአጠቃላይ አራት ልጆች ያፈሩት ጄኔራል ዘገየ፤ የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል። ጄኔራሉ በመኖሪያ ቤታቸው፣ በልዩ ልዩ ሆስፒታሎች፣ በቤተሰባቸው ርዳታ ለረጅም ጊዜ ሕክምና ቢደረግላቸውም ሊሻላቸው ስላልቻሉ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥትም የጄኔራሉን የሀገር አበርክቶ ከግምት በማስገባት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በሣህለተ ምህረት ቤተክርስቲያን ለክብራቸው በሚመጥን መልኩ በሀገር መከላከያ ማርሽ ባንድ ታጅቦ እንዲፈፀም አድርጎል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የተዋደቁትን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባል ብርጋዴር ጄኔራል ዘገየ ልዑልሰገድን ውድ ሕይወታቸውን አስይዘው በሙያቸው ለሀገር ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም