ወጣትና ተተኪ አትሌቶች ወደ ትልቅ ደረጃ ከሚሸጋገሩባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች መካከል አንዱ ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው። በቀጣይ ዓመታት በታላላቅ የአትሌቲክስ መድረኮች የሚያንጸባርቁ ከዋክብትን የሚያፎካክረው ይህ ቻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል። ዘንድሮ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ፔሩ ስትሆን በከተማዋ ሊማ ተጠባቂውን ውድድር ከቀናት በኋላ ማስተናገድ ትጀምራለች።
በውድድሩ የሚሳተፉ በርካታ የዓለም ሀገራትም በመድረኩ ውጤታማ ሆነው ለማጠናቀቅ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ወጣትና የመጪዎቹ ዓመታት ከዋክብት የሚሆኑ አትሌቶችን በሚያፎካክረው በዚህ ቻምፒዮና ከሚካፈሉና ተፎካካሪ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
ከቀናት በኋላ በሚጀመረው ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክለው የወጣቶች የአትሌቲክስ ቡድን ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ውድድሩ በሜዳ ተግባራት፣ የመም ሩጫዎች እንዲሁም በእርምጃ የሚደረጉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ6 ውድድሮች ማለትም በ800 ሜትር፣ 1 ሺህ 500 ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ 5ሺህ ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10ሺህ ሜትር ርምጃ በሴቶች ብቻ ትካፈላለች። ለዚህም 11 ሴት እና 9 ወንድ በአጠቃላይ 20 ወጣት አትሌቶች በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ልምምዳቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያሳያል።
አትሌቶቹ በሰኔ ወር በሃዋሳ ከተማ ከተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ቻምፒዮና የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የተመረጡ ናቸው። ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን ከምታስመዘግብባቸው መድረኮች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ቻምፒዮና፣ በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ የቻሉና ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ በርካታ አትሌቶችም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ በ3ሺህ ሜትር መሰናክል 5ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ እና የ5ሺህ ሜትር ተወዳዳሪዋ መዲና ኢሳ በወጣቶቹ ቻምፒዮና ከሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን መካከል እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
የ19 ዓመቷ ሲምቦ ከሁለት ዓመት በፊት ካሊ ላይ በተካሄደው የወጣቶች ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ የዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎዋን የተቀላቀለች ሲሆን፤ ይህም በኦሪጎን እና ቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮናዎች ላይ ሀገሯን እንድትወክል አድርጓታል። ተስፈኛዋ አትሌት በርቀቱ ያላት ሰዓት ለፓሪሱ ኦሊምፒክ እንድትመረጥ ሲያደርጋት በመድረኩ ልምድ ካላቸው አትሌቶች ጋር ተፎካክራ የዲፕሎማ ባለቤት መሆኗ የሚታወቅ ነው። ከቀናት በኋላ ሊማ ላይ ከእድሜ እኩዮቿ ጋር የሚኖራት ውድድር ጎልታ ትወጣለች ተብሎም ተስፋ ተጥሎባታል።
በተመሳሳይ ካሊ ላይ በ5ሺህ ሜትር አሸናፊ የነበረችው ወጣቷ አትሌት መዲና ባትረስ ላይ በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ሀገሯን ወክላ አንድ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። አትሌቷ በአፍሪካ ጨዋታዎችም ወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ በፓሪስ ኦሊምፒክም ተስፋ ሰጪ ብቃት ማሳየት ችላለች። ይህም በወጣቶቹ ቻምፒዮና ለወርቅ ሜዳሊያ እንድትጠበቅ አድርጓታል።
በዚህ ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ተሳትፎ በስኬት የታጀበ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ተሳትፎዋም በደረጃ ሰንጠረዡ ከዓለም ሀገራት 3ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ላይ ተቀምጣለች። ከአሜሪካ እና ጎረቤት ሀገር ኬንያ ቀጥላ የምትገኘው ኢትዮጵያ 46 የወርቅ፣ 51 የብር እና 32 የነሃስ በድምሩ 129 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ከሁለት ዓመታት በፊት የኮሎሚቢያዋ ካሊ አዘጋጅ በነበረችበት ቻምፒዮና ደግሞ 6 የወርቅ፣ 5 የብር እና 1 የነሃስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካን እና ጃማይካን በመከተል 3ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው።
ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች ከብርቱ ተፎካካሪነታቸው ባለፈ በተለያዩ ርቀቶች ክብረወሰኑን በመስበርም ስኬታማ ናቸው። በ3ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ታደሰ ወርቁ፣ በ5ሺህ ሜትር አብርሃም ጨርቆስ እንዲሁም በ20 ኪሎ ሜትር አትሌት መታፈሪያ ዘለቀ ባስመዘገቡት ሰዓት ቀዳሚዎቹ ናቸው። በሴቶች ደግሞ በ1500 ሜትር ብርቄ ኃየሎም፣ በ3ሺህ ሜትር በየኑ ደገፋ እና በ5ሺህ ሜትር ገንዘቤ ዲባባ የቻምፒዮናው ክብረወሰን ባለቤቶች ናቸው።
እአአ ከ1986 ጀምሮ የታዳጊ አትሌቶች ቻምፒዮና በሚል ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር፤ ከቅርብ ዓመታት አንስቶ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሚል መጠሪያ ተተክቶ እየተከናወነ ይገኛል። የዘንድሮው ውድድር ለ20ኛ ጊዜ ሲደረግ ከነሃሴ 21-25/2016ዓም ድረስ ይቆያል። 45 የውድድር ዓይነቶች በሚደረጉበት በዚህ ውድድር 134 ቡድኖች ከ 1 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ አትሌቶቻቸውን እንደሚያሳትፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም